>
5:13 pm - Monday April 20, 1609

ተከሳሾችን ተጠያቂ ለማድረግ የተሰራው አሳፋሪው የቂሊንጦ ቃጠሎ ሟቾች የሕክምና ማስረጃ (ጌታቸው ሽፈራው)

~”አስከሬኖቹ በሙሉ ለዘመዶቻቸው ሲሰጥ የሬሳ ሳጥን እንጂ ዘመዶች እሬሳቸውን እንዲያዩ አልተፈቀደም፡፡ ሲቀበሩም ፖሊስና የደህንነት ሰዎች ቆመው አስቀብረዋል፡፡ እንግዲህ በሬሳ ሳጥን ውስጥ የማን አስክሬን እንዳለ ማንም አያውቅም፡፡ ከሬሳ ውጭ ድንጋይም አፈርም ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ እንዲሁም አንዲት እናት ልጅሽ ሞቷል ተብሎ እሬሳ ከቀበረች በኋላ ልጇ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በህይወት አግኘተውታል፡፡”
~”አስከሬኖቹን መረመርኩ ብለው ያቀረቡት የማያወላዳ መንገድ ተከሳሾቹን ተጠያቂ እንዲሆኑ ከከሳሾች ጋር በመተባበር ሙያን ስነምግባርንና ህሊናን የሚንድ መንገድ የቀረበ መሆኑን ያስረዳል፡፡”
(ከ38ቱ  ተከሳሾች የተላከ)
 በነሐሴ 27 2008ዓ.ም. በተፈፀመው ቃጠሎ 21 ታራሚዎች በእሳት እንደተቃጠሉ 2 ሰዎች በወታደሮች ጥይት እንደሞቱ ተገልፆአል፡፡ ይህ መንግስ ያመነው ስለሆነ ይህም ዘገባ ይህንን ብቻ ያካተተ ይሆናል፡፡ ቀሪውን ድግሞ በሌላ ግዜ በማስረጃ ተደግፎ ይወጣል፡፡
አስክሬኖቹ ሁሉም ምርመራ የተደረገው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊንየም ሜዲካል ኮሌጅ ሲሆን የአስከሬን ምርመራውን በብቸኝነት የአንዲት ደቂቃ እንኳን እርፍት ሳያደርጉ ያከናወኑት ፕሮፌሰር ደሃርማርያ ኢንገሉ (Dr. Dharmarya Ingale) ናቸው፡፡
የምርመራው ውጤት በእንግሊዘኛ ስለተፃፈ ወደ አማረኛ የተረጎሙት ዶ/ር ጌታሁን ካሳ ይባላሉ፡፡
የአስክሬኑ ምርመራ ሳይንሳዊና አለም አቀፋዊ እውነታዎች፡-
ሀ. አንድ አስከሬንን መርምሮ የሞተበትን ምክንያት ለማወቅ ከሁለት እስከ አራት ሰዓታት ይፈጃል፡፡
ለ. የሞተው ሰው ምክንያት ከጀርባው ወንጀል ተፈፅሞበት ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ካል ፎሬንዚክ የአስክሬን ምርመራ (Forensic autopsy)  ይደረጋል፡፡ ይህ ደግ ከተራው (normal) የአስከሬን ምርመራ እጥፍ ማለት ከአራት እስከ ስምንት ሰአታት ይወስዳል፡፡
ሐ. የምርመራውን ውጤት በእርግጠኝነት ለማሳወቅ ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ይፈጃል፡፡
መ. አንድ አስከሬን የተመረመረባቸው የቀዶ ጥገና መሳሪያዎች በምንም አይነት sterilize ሳይደረጉ በሌላ አስከሬን ለመመርመር ፈፅሞ መጠቀም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ያንዱን ወደ ሌላው ማስተላለፍ ስለሚቻልና የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ስለሚደረስ፡
ሰ. ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ ላይ የተፃፉት አለም አቀፍ የጤና ድርጅት (WHO)ያወጣው እውነታ ስለሆነ በድህረ ገፁ ላይ ማንም ሰው ገብቶ መመልከት ይችላል፡፡
እነኝህ ከላይ የተጠቀሱትን ሳይንሳዊና አለም አቀፋዊ እውነታዎች እና ፕሮፌሰር ዳሃርማርያ ኢንገሌ ምን ያህለል ተከትለዋል ተጠቅመውባቸዋል?
ሀ) ፕሮፌሰር ዳሃርማርያ እንደ (Forensic autopsy)የወንጀል አስከሬን ምርመራ የወሰዱዋቸው ለሁለት አስክሬኖች አንድ አንድ ሰዓት፣ ለ 17 አስክሬኖች ለእያንዳንዳቸው 30 ደቂቃ፣ ለ 4 አስክሬኖች 15 ደቂቃ ያውም ሁለት እረሳዎችን አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ እጃቸው ማለተትም ሁለት እራሳዎችን በተመሳሳይ ደቂቃ ጀምረው በተመሳሳይ አጠናቅቄያለሁ ማለታቸው ነው። ለማረጋገጥ የመረጃ ቁጥር 90 እና 91 የምርመሩበት ሰዓት የጀመሩበት በ12፡30 የጨረሱበት 1፡00PM እንደሚያሳይ የሌላ መረጃ ቁጥር  94 እና 95 የጀመሩበት በ 2፡30 PM የጨረሱበት 3፡00 PM፡፡ ይህ አይነት ስራ የመለኮታዊ እድል ያለው ካልሆነ በሰው እውቀት አይሰራም፡፡
ለ)እኝህ ፕሮፌሰር የሌላ ምርመራን የጀመሩት ቃጠሎው በተደረገበት በማግስቱ እሁድ በነሀሴ 28 2008 ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት (8፡00 AM)  ሲሆን የጨረሱት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል (7:30PM) ነው፡፡ በጠቅላላው የፈጀባቸው 23 አሰስሬኖችን ለመመርመር 9 ሰአት ከ30 ደቂቃዎች ነው፡፡ በምርመራው መካከል የአንዲት ደቂቃ እንኳን እርፍት አላደረጉም፡፡ ሌላ እፁብ ድንቅ የሚያሰኝ ክስተት ነው!
ሐ) የምርመራው ውጤት ከመቅስበት በምን እንደሞቱ ፅፈዋል፡፡ አብዛኛዎቹ እሬሳዎች ከአጥንት በስተቀር ምንም ማንነታቸውን የሚገልፅ የተገኘ ወይም የተባለው ነገር ሳይሆን በጥርስ x-ray ወይም በ DNA ምርመራና ማንነቱን መግለፅ ሲገባ ፖሊስ በሰጣቸው ስም ብቻ ፕሮፌሰሩ ፊርማቸውን አሳርፈዋል፡፡
መ)የ21 ምርምራ ውጤት ሲመለከቱት ለአንድ እሬሳ የተፃፈው በአብዛኛው ቦታ የቀናት እንኳን ለውጥ ሳይደረግ ተመሳሳይ የምርመራ ውጤት ተፅፏል፡፡ በጭሩ copy and paste ነው የተደረገው እንድ ምሳሌ የገለፀው
የሰው ልጆች ከእናት መሃፀን ጀምሮ ያለእሱ መኖር የማያስችላቸው የሰውነት ክፍል ቆሽት Pancreas ይባላል፡፡ ፕሮፌሰሩ ሁሉንም የሰውነት አካላት (organs) መርምሬያለሁ ብለው ነገር  ግን እንድም ሬሳ ላይ ይህ ቆሽት (Pancreas) የሚባለው አልተገለፀም፡፡ ሌሎች copy- paste ሪፖርቱን መመልከት ይቻላል፡፡
አስደናቂ የማይታመኑ ውጤቶች
ለምሳሌ፡- 15 አስክሬኖች በአንድ የእስር ቤት (ዞን ሁለነት 7ኛ ቤት) ሸንት ቤት በአንድ ላይ ታጉረው መለየት የማይቻልበት ሁኔታ ከአጥንት በስተቀር ሌላ የሰውነት ክፍል ያልተገኘባቸው በእሳት ተቃጥለዋል ተብሏል፡፡ የሌሎችንም አስከሬኖች በፎቶግራፍ እንደሚታየው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ታዲያ ይህንን ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ለፕሮፌሰሩ የሚቀጥለውን ጥያቄ አቀረቡ “ከዚህ ድብዳቤ ጋር የላክናቸው አስከሬኖች አምስቱም የሞቱት ሌሎቹ በሞቱበት አኳኃን ነው ብለዋል፡፡ ፎቶግራፉ የሚያሳየው አስከሬኖቹ ልብሳቸውን እንደለበሱ የመቃጠል ምክልት የሌለባቸው ስለሆነ አጥንታቸው ብቻ በሚታየው አስከሬኖች ጋር እንዴት አንድ ሊሆን ይችላል” ፕሮፌሰሩ ባጭሩ ሲመቱ የቃጠሎ ዘይቤ ይህንን ስለሚገልፅ ሳይንሳዊ ክስተት ስለሆነ ተቀበሉ አሏቸው፡፡ ይህንን በቃላት ለመግለፅ ስለማይቻለ የሁለት አስከሬኖችን ፎቶግራፍ አያይዘናል፡፡
አንድ ወንጀል የተፈፀመበትን ቦታ በተለይ የሰው ህይወት ከጠፋ (the crime seen) የወንጀሉን ቦታ መርማሪ ፖሊሶች ካልመጡ ማንም ተራ ፖሊስ እንኳን ቢሆን ማንሳት የለበትም፡፡: ይህንን አስገራሚ ሁኔታ የመርማሪ ፖሊሶቹ ወደ ስፍራው በመሄድ ምርመራ ለማካሄድ እሬሳ የት ሄደ ብለው ሲጠይቁ የማረሚያ ፖሊሶች “የአዲስ አበባ ፖሊስ ፌደራል ፖሊስ ተወስደዋል” አሉን ብለው በአቃቤ ህግ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል፡፡  የፎረንሲክ (forensic) የምርመራ ፖሊስ ከወንጀሉ ቦታ ተነስቶ በሆስፒታል ያለው እሬሳ ነው ማለት ያየው፡፡
አስከሬኖቹ በሙሉ ለዘመዶቻቸው ሲሰጥ የሬሳ ሳጥን እንጂ ዘመዶች እሬሳቸውን እንዲያዩ አልተፈቀደም፡፡ ሲቀበሩም ፖሊስና የደህንነት ሰዎች ቆመው አስቀብረዋል፡፡ እንግዲህ በሬሳ ሳጥን ውስጥ የማን አስክሬን እንዳለ ማንም አያውቅም፡፡ ከሬሳ ውጭ ድንጋይም አፈርም ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡
እንዲሁም አንዲት እናት ልጅሽ ሞቷል ተብሎ እሬሳ ከቀበረች በኋላ ልጇ ዝዋይ ማረሚያ ቤት በህይወት አግኘተውታል፡፡
የማረሚያ ቤቱ በወቅቱ ምክትል አዛዥ የሰው ህይወት ለመጥፋት ዋናው ተጠያቂ የሆኑት ኦፊሰር ገብረማሪያም ለአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው ሲመሰክሩ መረጃ የሰጣቸው ሰው ስም ማነው ሲባሉ ቴድሮሰ ይባላል አሉ፡፡ አሁን “የት ነው?” ሲሏቸው በቃጠሎው ሞቶአል አለ፡፡ ይህ ሰው ግን ከሞቱት 23 ታራሚዎቹ ውስጥ የለም። ይህም የሚያሳየው ያልተቆጠሩ ሌሎች ታራሚዎች እንደተገደሉ ነው፡፡
የእንግሊዘኛን ወደ አማረኛ የተረጎመው ዶ/ር ጌታሁን ካሳ አያሌ ግድፈቶችና ሆን ተብሎ የማረሚያ ቤቱን ሃላፊዎች በሃላፊነት ለማፅዳት የተደረገ ለመሆኑ አንድ ማስረጃ ብቻ ይጥቀሱ፡
በምርመራው ውጤት ሪፖርቱ ላይ “history : found dead in prison yesterday cause of death not known” ይላል፡፡ የዚህ ቀጥተኛ ትርጉሙ ታሪክ በእስር ቤት ውስጥ ትናንት ሞቶ የተገኘ የሞተበት ምክንያት ያልታወቀ መሆን ይገባዋል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው ሲተረጉመው ግን “ ታሪክ በቀን 28/12/2008 እስር ቤት ውስጥ ባልታወቀ ምክንያት በደረሰ ቃጠሎ ህይወቱ አልፋል“
ይህ ትርጉም የቋንቋ ችሎታ ማነስ ወይም ስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ አማረኛውን የሚያነቡ ዳኞች አቃቤ ህጎችና ሌሎች ገና ከመጀመሪያ በእሳት ተቃጥሎ ሞተ የሚለው ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ bias ማደናገሪያ ለመፍጠር ሆነ ተብሎ የከሳሽ ወገንተኝነት ለማረጋገጥ የተደረገ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በነገራችል ላይ copy- paste መሆኑ ዳግም የ21 አስከሬኖች Coma, ኮማ እንኳን ሳይቀር አንድ አይነት መሆኑ ነው፡፡
በጥይት ተመተው የሞቱትን ሳያውቁ ወይም መዘዙን ሳይገነዘቡ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነታውን አስቀምጠዋል፡፡
ሁለቱም የተመቱት ከፊት ለፊት በአጭር እርቀት ላይ በሽሽታቸው ላይና ጥይቱ ወደ ላይ ሆዳቸውና አንጀታቸውን በመብሰት የደም ስሮች Femoral and iliaca Arteries ) ስለበጣጠሰው ብዙ ደም ፈሷቸው ነው ይላል፡፡
በማረሚያ ቤት ውስጥ እስረኛ ሲያመልጥ በጥይት የሚመታው እግሩን ለዚያው ከአጥሮቹ ሁሉ ውጪ ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ እነዚህ ወታደሮቹ ያመኗቸው  ሁለት ተራሚዎች የተመቱት ከአራት የእስር ቤት አጥሮች አንዱን እንኳን ሳይጥሱ እዚያው አስር ቤት ውስጥ ከእሳት ለማምለጥ ሲሮጡ ከፊት ለፊት የነበሩ ወታደሮች ተኩሰው ነው የገደሏቸው፡፡
መደምደሚያ
ከላይ የተጠቀሱት ዝርዝር ጉዳዬች ከየትም የመጡ ሳይሆን ከሳሽ አቃቤ ሀግ በሰነድ ማስረጃነት ለፍርድ ቤት ለተከሳሾቸ ከሰጠው ውስጥ  ስለሆነ ማንም አግኝቶ ማረጋገጥ ይችላል፡፡
አስደንጋጭና ለማመን የሚያስቸግረው በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሰት ተቋም በጤና ጥበቃ ስር ያሉ ብዙ የጤና ባለሙያዎችን እያስተማረ የሚያስመርቅ ቅዱስ ጳውሎስ          ተቀጥረው የሚሰሩ ባለሙያዎች በቀጥታ የወንጀል ተባባሪ ሲሆኑና ተቋሙ ዝም ብሎ ማየቱ እነኝህ ሁለት የሕክምና ዶክተሮች የሂፖክራተስን (hypocratus) መሃላ ፈፅመው ለሰው ልጅ አገልጋይነት ለህይወት መታደግ እንሰራለን ያሉ 38 ታራሚዎች በሃሰትና በተቀነባበረ ወንጀል እስከ ሞት ቅጣት ድረስ የሚያሰወስነውን  አንቀፅ ተጠቅሶባቸው የተከሰሱ ሰዎች ላይ ይህ ፍርድ እንዲፈፀምባቸው ያለምንም ማመንታት ከከሳሹ ጋር ተባባሪ መሆናቸው ነው፡፡
ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር EMA (Ethiopian Medical Association) እንዲህ አይነት የህክምና ሙያ የሚያጎድፉ አስወቃሽ አሳፋሪ ነገር ሲሰራ ዝም ብሎ መመልከቱ ነው፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያውያን የሙያ ክብር ዋጋ የሚያሳጣ ታማኝነትን የሚያሳጣ የህክምናው ባለሙያዎች ከጨካኙ መንግስት ተቋሞች ጋር በመተባበር መሳሪያ መሆንን እንዴት ልተቀበሉት ትችላላችሁ ( ይህንን አሳፋሪ የብዙ ንፁሃንና በዲሲፕሊን የታነፁ ለሙያቸው ክብርና ሃላፊነት (integrity) የቆሙ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞችን ስም ክብር ለመጠበቅ ያለምንም ማመንታት በአስቸኳይ ምርመራና ማጣሪያ እንዲደረግ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ፤
በተጨማሪም ይህ የአስከሬን ምርመራ ውጤት በየትኛውም መስፈርት ሙያዊ ጥራትና ቅንነትና እውነተኛነት የጎደለው ስለሆነ ተቀባይነት እንዳይኖረው ግልፅ አቋም ወስዶ ማሳወቅ፤
ይህ ካልተደረገ ግን በዚህ ሪፖርት መሰረት ንጹሃን ተከሳሾች ተከሰው ቢፈረድባቸው ተቋማቱ የወንጀሉ ተባባሪ መሆናቸው በታሪክም ተጠያቂ እንደሚያሰደርግ መታወቅ አለበት፡፡
መግቢያ፡_ዝቅ በሎ እንደሚዘረዘረው በነሃሴ 27 2008ዓ.ም. በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በተከሰተው የቃጠሎ እና የረብሻ ሁኔታ መንግስት 23 ታራሚዎች ሞተዋል ብሎ ለዚህም 38 ተከሳሾች በሽብር የሞት ቅጣት ድረስ የሚያበቃ አንቀፅ ከፍቶ አቃቤ ህግ ምስክሮቹን አስምቶ ለብይን ለሚያዚያ 16 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ በዚህ ክስ ላይ የፎረንዚክ መርማሪ ፕሮፌሰር አስከሬኖቹን መረመርኩ ብለው ያቀረቡት የማያወላዳ መንገድ ተከሳሾቹን ተጠያቂ እንዲሆኑ ከከሳሾች ጋር በመተባበር ሙያን ስነምግባርንና ህሊናን የሚንድ መንገድ የቀረበ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ይህ ድርጊት በአሜሪካ ኮንግረስ HR128 ላይ በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ጠይቋል፡፡ በጥይት 2 በእሳት 21 ሞቱ ይባል እንጂ በጥይት የሞቱት ታራሚዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ እንደውም የጅምላ መቃብር በዚያው በማረሚያ ቤት ውስጥ እንዳለና አሁን ቤት እንደተሰራበት ይወራል፡፡
በተጨማሪ የሞቱት ሰዎች በጥይት እንደሞቱ ብዙ ማስረጃዎች ስላሉ አስከሬኖቹ ወጥተው በትክክለኛው ባለሙያ ገለልተኛ  በሆነ እንዲመረመሩ ይጠየቃል፡፡ ይህ የአስከሬኑ ምርምራ ውጤትና ሌሎችም የአቃቤ ህግ ሰነዶች የሃገራችንም ሆነ አለም አቀፋዊ ተቋማትና ባለሙያዎች  እንዲያዩዋቸው ራሱን በቻለ ድህረ ገጽ website ይወጣል፡፡
በሚያዚያ 16 ፍርድ ቤት ውሳኔ ስለሚሰጥ ማንኛውም ሰው ክትትል ማደረግ ስለሚችል መጥታችሁ እንድትከታተሉ እንጠይቃለን። እሰካሁን የአገሪቷ ከፊል የግል ሚዲያዎች እስካሁን የሚዘግቡ ሰዎች ሲከሰሱ ሲፈረድባቸው እንጂ ተከሳሶች ነፃ ሲወጡ ስላልሆነ ቢያንስ አሁን የነፃነት ጭላንጭል  መጥታችሁ በሚያዚያ 16 ብይን ሁኔታ ብትዘግቡ እውነታውን ማውጣት ትችላላችሁ!
ግልባጭ
ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር
ለአዲስ ጳውሎሰ ሚሊኒየም ኮሌጅ
ለሃኪሞች ማህበር / Ethiopia Medical Association/
ለጠቅላይ አቃቤ ህግ
ለአዲ አበባ የወንጀል (ፎረንሲክ) ምርመራ ፖሊስ ኮሚሽን
አቤት ሆሰፒታል ዳይሬክተር
Filed in: Amharic