>

"በእኔ እምነት አብይ ከፖለቲካ አንፃር ትልቅ ድልድይ ተሻግሯል" (ቬሮኒካ መላኩ)

    የአለም አቀፍ ፖለቲካ እጅግ ተለዋዋጭ ነው። የአገራችንም ፖለቲካ ተለዋዋጭነቱ  ከአይን እርግብግቢት የበለጠ እየፈጠነ ነው። ይሄ የፖለቲካ ባህሪ ነው። በዚህ ጥቅምንና የሀይል ሚዛንን እየለካ በሚለዋወጥ ፖለቲካ ውስጥ እኛም ቅኝቱን ተከትለን ካልተጫወትን ፖለቲካ አልገባንም ማለት ነው። በብርሃን ፍጥነት በሚቀያየር ፖለቲካ ውስጥ እንደ የዛገ ቀዝቃዛ ብረት የጠነከረ ግትርነት እና መንቻካነት አያዋጣም። ውጤቱም አክሳሪ ነው።  ከእኛ የሚጠበቀው ጥቅማችንን ብቻ ካልኩሌት እያደረግን ፖለቲካው ሲቀያየር እኛም መቀያየር ነው። ይሄ ካልገባን በጊዜ ጡረታ መውጣት ነው።
የእኛን ጥቅም በተመለከተ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ሲያራምድ ከነበረው ፀረ አማራ አቋም ፈፅሞ የተለየ ነው። ለማነፃፀር ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ላቅርብ።
1ኛ~ የሱዳንን መሬት ወረራ በተመለከተ። 
ሀይለማሪያ ደሳለኝ በጎንደር በኩል ስላለው በሱዳኑ ጦር  ሰራዊት የተወረረ መሬት በፓርላማ ሲጠየቅ  እጅግ በሚያሳዝንና በሚያናድድ ሁኔታ << የበጠበጡትና የሱዳንን መሬት የወረሩት የጎንደር ሽፍቶች ናቸው> > ብሎ እንደነበር መርሳት የለብንም። በፓርላማ ላይ ለአገሩ እየሞተና መሬቱን ላለማስነካት መስዋእት የሆነን ህዝብ “ሽፍታ ” ብሎ መጥራት እጅግ አሳፋሪና በታሪክም ሆነ በሞራል ይቅር የማይባል ወንጀል ነው።
በአንፃሩ አቢይ አህመድ ስለዚሁ የድንበር ጉዳይ ሲጠየቅ የኢትዮጵያን ጥቅም ባስከበረ መልኩ በአስቸኳይ እንደሚፈታው አስረግጦ ተናግሯል።
2ኛ~ የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ። 
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ስለወልቃይት ሲጠየቅ በፓርላማም ሆነ በጋዜጣዊ መግለጫ ” ኢትዮጵያ ውስጥ የማንነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መልስ አግኝቷል ። በዚህም መሰረት የወልቃይትም ጉዳይ ቀድሞ የተመለሰ ስለሆነ የማንነት ጥያቄ ሊቀርብ አይገባም ።”” በማለት ተናግሯል።
አብይ አህመድ ይሄን የሀይለማሪያምን አይን ጋርዶት የነበረ አሻጥር በመግፈፍ ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ እውቅና ሰጥቷል ። በወልቃይት ጉዳይ አብይ ትልቅ ድልድይ ተሻግሯል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ የወልቃይት ማንነት ጥያቄ  በህገመንግስቱ መሰረት መልስ ያገኛል ሲል በህገመንግስቱ መሰረት የወልቃይት ጉዳይ የወልቃይቴውች እንጂ  አረም ለማረም የመጡ የሰፋሪዎችን ድምጽ እንደማያካትት መታወቅ አለበት ።
 ከ20 አመታት በፊት የስልጤዎች የማንነት ጥያቄ በህገመንግስቱ መሰረት ሲመለስ ስልጤ  ማንነት ብቻ ያላቸው ሰዎች በተሳተፉበት ሁኔታ ብቻ ነው። ስለሆነም የወልቃይቴዎች የማንነት ጥያቄ የሚስተናገደው Exclusively በወልቃይቴዎች ብቻና በወልቃያቴዎች ብቻ ነው ። ይሄ መታወቅም መሰመርም አለበት።
በእኔ እምነት አብይ ከፖለቲካ አንፃር ትልቅ ድልድይ ተሻግሯል ። መርህ አልባና ሳይንሳዊ ያልሆነ ትችት የትም አያደርሰንም ።  አብይ  ነገ ጧት ወልቃይትን በስጦታ ወረቀት ጠቅልሎ  እንድሰጠን የምንጠብቅ ከሆነ ተሳስተናል። ከአብይ የሚጠበቀው የመጫዎቻ ሜዳውን Fair  እንዳደርግልን ብቻ ነው ። መጫዎቻው ፌይር ከሆነ በወልቃይት ጉዳይ አማራ በታሪክም ፣ በህግም ሆነ በጉልበት ተጋጣሚውን  60 ለ 0 በሆነ ውጤት የሚያሸንበት እንደሆነ አምናለሁኝ።
Filed in: Amharic