>
5:13 pm - Tuesday April 18, 7747

አቢይ ኢትዮጵያን ሳይሆን ኢህአዴግን ለማዘመን የተላከ መሲህ ነው!?! (ዮናስ ሀጎስ)

ኢህአዴግ ሌላኛውን «ታላቁን መሪ» ማግኘቱን ዛሬ በደንብ ያረጋገጠ ይመስለኛል። ታላቁ መሪ በየሄዱበት ምን መናገር እንዳለባቸው የሚያውቁ ማንን ለማስደሰት ምን ማለት እንዳለባቸው ጠንቅቀው የተረዱ የኢህአዴግ አዲሱ ገፅታ ናቸው።
•°•
ናምቺ ዛሬ በጃኖ ተለብደው ባለፈው የገመትናትን «የጎንደር ፋሲለደስ ሕንፃ የላሊበላ ቅኔ…» ምናምን የተሰኘ ንግግራቸውን በጎንደር ስታድየም ተገኝተው ለሕዝቡ አሰምተዋል። ወደ ደቡብ ክልል የሚያስኬድ ጉዳይ ያላቸው አይመስለኝም እንጂ እዛ ከሄዱ ደግሞ ንጉስ ጦና መነሳቱ አይቀርም በንግግራቸው መሐከል።
•°•
ከስታድየሙ ንግግር በመለስ በአዳራሽ ደግሞ ከጎንደር «ሽማግሌዎች» ጋር ውይይት አድርገው ወልቃይትን በተመለከተ የማፅናኛ መልስ አሰምተዋል። «እዛ (መቐለ) ስለ ወልቃይት የጠየቀኝ ሰው የለም። ስለ ዳያስፖራ ሳወራ ነው በዛው ያመለጠኝ። የወልቃይት ጉዳይ በሕግ አግባብ እንደሚታይ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁኝ!» ብለውም አዳራሹ እስኪነቃነቅ ድረስ ጭብጨባ ጠግበው ማምሻውን ወደ ባህር ዳር አምርተዋል።
•°•
በሕግ አግባብ…
•°•
እንግዲህ አዲስ ሕግ ካልመጣ በቀረ አሁን ባለው ሕግ ይህ የወልቃይት ጥያቄ ፌደራል መንግስቱ የፌደሬሽን ምክር ቤት ደርሶ «በሕጉ መሰረት የሚመለከተው የትግራይ ክልል ነው» ተብሎ ወደዛ ተመርቶ የትግራይ ክልል ደግሞ «እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ የማስተናግድበት ጊዜውም የለኝም…» ብሎ ፋይሉን ከዘጋው ቆይቷል። ጠ/ሚ/ሩ ይህ ሁሉ ሲሆን የፓርላማ አባል ነበሩና ይህንን አያውቁም ለማለት ይከብዳል። እንግዲህ በሕጉ አግባብ ለማለት የፈለጉት «ሳያነጋግሩ ተመለሱ…» ምናምን እንዳይባል ይሁን ሌላ አዲስ ሕግ ሊፃፍ እየተረቀቀ ይሁን ለጊዜው ማወቅ ባንችልም ናምቺ (ሰውዬው) እንደተለመደው የጎንደር አስተናጋጆቻቸውን አስፈንድቀው አንድ ጃኖ ተሸልመው መመለሳቸው እርግጥ ሆኗል።
•°•
አንድ ጓደኛዬ እንደሚለው ዶክተር አቢይ ኢህአዴግን ወደ ዘመናዊነት እያመጡ ያሉ የኢህአዴግ እድሜ ማራዘምያ ናቸው። ኢህአዴግ ለዘመናት ሲጠቀምባቸው ከቆዩት የካድሬ እንጨት እንጨት የሚሉ ቃላቶች የፀዱ፣ ለዘመናት ኢህአዴግ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የምርመራ ስልቶች (ግርፊያ፣ ብልት ማንጠልጠል፣ ሰውነትን በጋለ ብረት በእሳት መተኮስ…) ምናምን ቀርተው በአዳዲስ የማሰቃያ ስልቶች (የአሜሪካን ፊልሞች ላይ እንደምናያቸው በመድሐኒት በመጠቀም፣ ውኃ ላይ በመዘፍዘፍና ሌሎች ዘመናዊ ስልቶች) እንዲቀየሩ በማድረግ እንዲሁም በቀደመው የኢህአዴግ አሰራር የማይደፈረውን ኢትዮጵያዊነት ስሜት በየሄዱበት በማንፀባረቅ ከርሳቸውም አልፎ በጌቶቻቸው ጭራ መከተል የሚወዱ የመንግስት ሚድያዎችም ደርሰው ስለ ኢትዮጵያዊነት አስተማሪ እንዲሆኑ በማድረግ ኢህአዴግን ከ19ኛው ክፍለዘመን አስተሳሰብ ወደ 21ኛው ክፍለዘመን አስተሳሰብ እያራመዱ ያሉ ብርቅዬ መሪ ናቸው።
•°•
ይህንን ስንል ግን አንዳንድ የማይቀየሩ ነገሮች መኖራቸው ግልፅ ነው። ኢህአዴግ የፈለገ ዘመናዊ ቢሆን የማይተዋቸው ጉዳዮች አሉ። የእስክንድር ጉዳይ እንግዲህ አንደኛው መሆኑ ነው። እስክንድር ነገ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የክብር እንግዳ አድርጎ ሰይሞታል። የክብር እንግዳ ደግሞ ንግግር ማድረጉ አይቀሬ ነው። አስቡት እንግዲህ ባለፈው ሰሞን ኤች አር 128 ፀድቆ የርሱን ተፅዕኖ ለማስተካከል ታላቁ መሪያቸው እየተሯሯጠ ባለበት ሰዓት እስክንድር ዓለማቀፍ መድረክ ላይ ቆሞ ማዕከላዊና ቃሊቲ ቂሊንጦ ስለደረሰበት ግፍ ለታዳሚዎች ሲናገር ምን ያህል ኪሰራ እንደሚገጥማቸው? ያንን አስቀድመው ስለተገነዘቡም እስክንድር ልክ የመጓዣው ጊዜ ደርሶ ኤርፖርት ሲደርስ ፓስፖርቱን ተቀብለው «ነገ ኢሚግሬሽን ብቅ በልና ውሰድ ጌታው…» ብለው አሰናበቱት። እነርሱ ከፓስፖርቱ ጉዳይ የላቸውም። ፍላጎታቸው ለነገው ስብሰባ እንደማይደርስ ማረጋገጥ ብቻ ነው። በዛውም የኛ በትንሽ በትልቁ እሪታ የሚወደው ሕዝባችን ነገ ፓስፖርቱን «በስህተት ስለሆነ እናዝናለን። ከሌላ ሰው ጋር ተመሳስሎብን ነው…» ብለው ሲመልሱለት አዳሜ እዚህ መጥቶ «አቢይ ነው ያስመለሰለት!» ብሎ እንደሚፈነድቅም ጥርት አድርገው ያውቃሉ።
•°•
እናልህ ወዳጄ ሆይ…
አቢይ ኢህአዴግን ለማዘመን የተላከ መሲህ ነው። (ሙሴ፣ ኢያሱ እያሉ ስራውን ለማኮሰስ የሚሞክሩትን በፅኑ እቃወማለሁኝ!) ይህ መሲህ ኢህአደግን ወደ ክፍለዘመኑ አስተሳሰብ በማምጣት ኢህአዴግን መታደግ ዋንኛ ስራው ሲሆን እስካሁንም በተሳካ መንገድ እየከወነ ይገኛል። ከዛ ውጭ ግን ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ለመምራት የተላከ ሙሴ ምናምን የሚሉ እንቶ ፈንቶዎች መቼም የማይሆኑ መሆናቸውን ስንገልፅ በታላቅ ሐዘን ውስጥ ሆነን ነው። ኢህአዴግ በእኛ ለውጥ ፈላጊዎች «ጊዜ ይሰጠው» ጩኸት ፋታ አግኝቶ የወደፊቱን አቢይ አህመድ ከጭቃ ጠፍጥፎ እየሰራ ይሆናል ይሄን ጊዜ…
•°•
ገና ነገ ዶክተራችን ስለ እምቦጭ ብዙ ይደሰኩራልና ደስታችሁን እንዳያልቅባችሁ እየቆጠባችሁ…
ዶ/ር አብይ በወልቃይት ጉዳይ የሰጡት ምላሽ 

Filed in: Amharic