>

ከሃገር እንዳይወጣ ተከልክሎ የነበረው እስክንድር ነጋ እገዳው ተነሳለት

ቢቢሲ አማርኛ

ከ 39 ደቂቃዎች በፊት ጋዜጠኛና የዲሞክራሲ አቀንቃኝ እስክንድር ነጋ ከሃገር እንዳይወጣ መከልከሉን ለቢቢሲ ገልፆ የነበረ ሲሆን እንደገና ፓስፖርቱ ተመልሶለት እንዲጓዝ እንደተፈቀደለት ተናግሯል።

እስክንድር እንደሚለው ወደ ሆላንድ ጉዞ ሊያደርግ ትናንት ለሊት ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኘቶ የነበረ ቢሆንም ጉዞ እንዳያደርግ ተከልክሎ ፓስፖርቱን ተነጥቆ ወደ መኖሪያ ቤቱ ተመልሷል።

”አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ተጋብዤ ወደ ሆላንድ ልሄድ ነበር ይሁን እንጂ ፓስፖርቴን ተቀምቼ ለመመለስ ተገድጃለው” ብሏል።

ወደ ሆላንድ የሚያደርገውን ጉዞ ሃሙስ ምሸት ለመጀመር ፤ እስክንድር ለሊት 7፡30 ገደማ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሰ ይናገራል። ”ሻንጣዎቼን በሙሉ አስገብቼ ቦርዲንግ ፓስ (አውሮፕላን መሳፈሪያ ወረቀት) ተቀብዬ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ወዳለው ኢሚግሬሸን ተመራሁ።

እዛ ከደረስኩ በኋላ ኢሚግሬሽን ኦፊሰሯ ፓስፖርቴን ከተመለከተች በኋላ ቆሜ እንደጠብቃት ነግራኝ ወደ ውስጥ ገባች። ለግማሽ ሰዓት ካስጠበቀችኝ በኋላ ሌላ ሰው መጥቶ መጓዝ እንደማልችል እና የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ቢሮ ቁጥር 9 ሄጄ እንዳነጋግር ተነገረኝ” በማለት የተፈጠረውን ነገር ያስረዳል።

የሚሄድበትን ጉዳይ በማስረዳት ፓስፖርቱን መልሰውለት እንዲጓዝ እንዲፈቅዱለት ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ገልጿል። ‘ትዕዛዙ ከአለቆቻችን የመጣ ነው’ የሚል መልስ ሲሰጠው ምንም ማድረግ አለመቻሉን ይናገራል።

ለምን ከአገር መውጣት እንደተከለከለ እስካሁን እርግጠኛ ባይሆንም እስክንድር በሶስት ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።

የመጀመሪያው ምክንያት ወደ ሆለንድ የሚሄደው ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል የ50ኛ ዓመት ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ ከመሆኑ ጋር ይገናኛል።

እስክንድር እንዳለው ከሰዓታት በኋላ እዚያው ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚገኘው ኢሚግሬሽን ቢሮ ተደውሎለት ፓስፖርቱ ሲመለስለት ጉዞውን ማድረግ እንደሚችልም ተገልፆለታል።

”ይህ ድርጅት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት ስለማይወደድ በዝግጅቱ ላይ እንዳልሳተፍ ሊሆን ይችላል። ሌላው በሆለንድ በሚገኙ የኢትዮጵያ ማህብረሰብ አባላት ለእኔ የተዘጋጀ የእራት ግብዣ ነበር እዛ ላይም እንዳልሳተፍ ታስቦ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ሌላው ግምቴ ከእስር መፈታታችንን የማይደግፉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት አሉ እና የእነሱም ትዕዛዝ ሊሆን ይችላል”የሚለው እስክንድር እንደተባለው ከተባለው ቢሮ ሄዶ ምክንያቱን በርግጠኝነት ከማጣራት ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌለው ይናገራል።

ባለፉት ቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት ከሃገር እንዳይወጡ ከታገዱት መካከል የዞን 9 አባላት ይገኙበታል። የዞን 9 አባል የሆነው ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ አራት የዞን 9 አባላት ጓደኞቹ በተደጋገሚ ከሃገር እንዳይወጡ ተደርገዋል ይላል።

”በአየር መንገድ በሚገኘው ኢሚግሬሽን ከሃገር እንዳይወጡ ተብሎ የስም ዝርዝራቸው ከተቀመጠ ሰዎች መካከል የጓደኞቼም መኖሩን ለተለያዩ ጉዳዮች ከአገር ሊወጡ ሞክረው ሲከለከሉ አረጋግጠናል”ይላል።

የአምንስቲ ኢንተርናሸናል የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተክሌ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሆላንድ 50ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር እስክንድርን የክብር እንግዳ አድርጎ ሊጋብዘው እቅድ እንደነበረው ይናገራሉ።

“ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም ቃል በገባ ማግስት ይህ መሆኑ ያሳዝናል። አምነስቲም እገዳው ቶሎ ተነስቶለት እስክንድር ለቅዳሜው ዝግጅት መጓዝ እንዲችል እንጠይቃለን ” ብለው ነበር አቶ ፍስሃ።

እስክንድር ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ”የዲሞክራሲ ጥማት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተመልክቻለሁ” ብሎ ነበር

Filed in: Amharic