>

ለ"ሰሜናዊት ኮከቦቹ" አልጋ ለሌላው ቀጋ የሆነችው ኢትዮጵያ !?! (ቶሎሳ ኢብራሂም)

ባንድ ወቅት ብዙ መሬት በመቀማት ይታወቅ የነበረ አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ የተባለ ትግራዊ ከጌቶቹ ጋር በነበረው የግል ግጭት ታስሮ ከቆየ በኋላ ሰሞኑን ከእስር ተለቆዋል። ይህ ሰው መሬት መቀማት ብቻ አይደለም ለገጣፎ የተባለው ከተማ መሬቱ ሁሉ የሱ ነበር አሉ። ከተማው ራሱ ለምን ለገጣፎ ከሚባል ገብረዋህድ ከተማ ተብሎ አይሰይምም ተብሎ እስከ መቀለድ ተደርሶ ነበር።
የዚህ ሰው ቤቱ ሲፈተሽ ሳሎኑና ክፍሎቹ ሁሉ  በብርና በጠመንጃ የተሞሉ ነበሩ። ሰውየው ብር ላይ ተራምዶ፣ ብር ላይ ተቀምጦ፣ ብር ተንተርሶ፣ ብር ላይ ይተኛ እንደነበር ራሳቸው ጌቶቹ  አሳዩን።
አሁን ታዲያ ሰሞኑን ከእስር ተፈቶዋል። ሌላው ከእሱ ጋር በተመሳሳይ ወንጀል የታሰረው መላኩ ፈንታ የተባለው ምስኪኑ የሕወሐት የእንጀራ ልጅ እዚያው እንዲቀር ሲደረግ ገብረዋሕድ ተፈቶዋል። “ጌታውን የተማመነ በግ ላቱን ውጭ ያሳድራል” ይባል የለም።
በሌላ በኩል፣ዶር ፍቅሩ ማሩ በሙያቸው አገሬንና አህጉሬን አገለግላለሁ ብለው ከአውሮፓ ጓዛቸውን ይዘው የተመለሱትና በአገራቸው ላይ ሙያዊ አገልግሎታቸውን እንዳይሰጡ እጃቸው በሰንሰለት ታስሮ የገራፊዎች መጫወቻ እየሆኑ ነው። አገራቸውን ዘርፈው ሳይሆን አገራቸውን በማገልገላቸው፣ ወስደው ሳይሆን በመስጠታቸው፣ ደማቸው እንደሌሎቹ ሁሉ ቀይ ቢሆንም የ”ኦሮሞ ደም” ተብለው ወንጀለኛ ሆነው እየተሰቃዩ ናቸው። ታዬ ደንደአ የተባለ ወንድማችንም አንዳች ውሃ ሳያፈስ ሰው አትግደሉ በማለቱ ሰንሰለት ገብቶለታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትግራይ ነበሩ። እዚያ የሰሜኑዋ ኮከብ ከተማ መቐሌ ላይ ሕዝብ ሰብስበው እያወያዩ ነበር። ታዲያ ከስብሰባው እየተነሳ የነበረው አስተያየት የሚገርም ነው። ትግሬ እየተገደለ ነው፤ እየተፈናቀለ ነው፤ ንብረት እየተቀማ ነው፤ ትዕግስት ፍርሃት አይደለም፤  ታግሰን እንጂ በትግሬ ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ግፍ ብዙ ነው እያሉ ናቸው የመቀሌ ነዋሪዎች። ዲሞክራሲንና ነፃነትን ባጎናፀፍናችሁ ይህ ይገባናል እያሉ ናቸው። የመሀል አገሩንም ሰው በውለታ ቢስነት የመፈርጁ ዓይነት ንግግሮች እየታዩ ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ትግራዊያን አሁንም አልጠገብንም እያሉ ናቸው። አሁንም ትላልቅ ግድቦች ይሰሩልን እያሉ ናቸው። አስመጪና ላኪ እየተጉላላ ስለሆነ የብሔራዊ ባንክ ቅርንጫፍ ይኑረን እያሉ ናቸው። ከመቀሌ አሮጌ ታክሲ ይውጣልንና ዘመናዊ ታክሲ ይግባልን እያሉ ናቸው። ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ ክልሉ ልዩ ትኩረት (affirmative action) ያስፈልገዋል እያሉ ናቸው።
ታዲያ የሚያሳዝነውና የሚያስተዛዝበው አንዳቸውም ኦሮሞን ስለሚጨፍጭፉ ልጆቹ አላነሱም። አንድም በተኛበት፣ በቆመበትና በሚሰራበት በትግራይ ልጆች እስናይፐር እየተለቀመ ስላለው ኦሮሞና አማረ አባከና ብሎ ያነሰ ማንም ሰው አልነበረም። አንድም የኦሮሞን ሴቶች ጠመንጃ ደግነውባቸው እየደፈሩ ስላሉ የትግራይ ልጆች ያነሰ የስብሰባው ተሳታፊ አልነበረም። ብዙ እናቶች ስብሰባ ላይ ይናገሩ ነበር። ግን ልጁዋን ገድለውባት ሬሳ ላይ ቀጭ በይ ስለተባለች የኦሮሚያ እናት አንዲትም የትግራይ እናት ምንም አላለችም። ባንድ ጊዜ በፊት ለፊቱዋ አጋዚዎች ሶስት ልጆቹዋን ስለደፉባት እናት አስታውሳ ያነሰች የትግራይ እናት አልነበረችም። እውነት ለመናገር እኔ በበኩሌ ቢያነሱ ይገርመኝ ነበር።
Filed in: Amharic