>

ያልተቀየረ ፕሮፓጋንዳ! (ኤርሚያስ ለገሰ)

#አደረጃጀት
የዛሬ አስር አመት ገደማ ነው። አቶ መለስ ከመላው ኢትዬጲያ የተውጣጡ የወጣት ሊግ አባላትን ሙሉ ቀን ለማወያየት ሽር ጉድ እየተባለ ነው። ኮንፍረንሱ ልዩ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ አስተባባሪ ኮሚቴው በየሶስት ቀኑ አመሻሽ ላይ እየተሰበሰበ አፈፃፀሙን ኢህአዴግ ቢሮ ሁለተኛ ፎቅ የምትገኘው ትንሿ አዳራሽ ይገመግም ነበር። የማክሮ ኮሚቴው ሰብሳቢና ምክትሉ ጓድ! በረኸት ስምኦን እና ህላዌ ዬሴፍ ነበሩ። አባላቱ ደግሞ  ታደሰ ካሳ( የስልጠና ክፍል ሃላፊ)፣ ሴኮቱሬ ጌታቸው ( ወጭ ግንኙነት)፣ ህላዌ ዬሴፍ ( አዲስአባ ኢህአዴግ)፣ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ( ወጣቶችና ስፓርት ሚኒስትር)፣ ብርሃን ሐይሉ ( ማስታወቂያ ሚኒስትር)፣ ካሚል አህመድ ( አዲሳባ ኢህአዴግ)፣ ፍሬህይወት አያሌው ( አዲሳባ ኢህአዴግ) ፣ እኔ እና ወጣት ውብሸት ገ/ እግዚአብሔር ( የወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት) ነበርን።
በተመሳሳይ ሁኔታ የአራቱን ድርጅቶች ወጣት ሊግ ፕሬዝዳንቶች፣ የፕሮፐጋንዳና ድርጅት ሐላፊዎች ፣ የወጣት ማህበር ፕሬዝዳንቶች የያዘ ንዑስ ኮሚቴም ተደራጅቶ ነበር።  ይሄን ንዑስ ኮሚቴ የሚመራው ታደሰ ካሳ ( ጥንቅሹ) ሲሆን በየሶስት ቀኑ ለአቢይ ኮሚቴው ሪፓርት ያቀርብ ነበር።
#የኮሚቴው ተግባራት
ለሁለት ወራት የዘለቀው አቢይ ኮሚቴ የኢህአዴግ ወጣት ሊግ አባላት “ከብፃይ!” መለስ ጋር የሚያደርገውን ውይይት በበላይነት የሚመራ ነበር። ሂደቱንም እየመረመረ አዳዲስ ሃሳቦችን በመጨመር ለስኬቱ ይተጋ ነበር። ከወሰናቸው እና ከፈፀማቸው ዋና ዋና ተግባሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል።
• ኮንፍረንሱ ከኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጋር መባሉ አደገኛ ስለሆነ ስያሜው ” ከመላዉ ኢትዬጲያ የተውጣጡ ወጣቶች!” በሚል እንዲስተካከል ተደረገ።
• የኮንፍረንሱ ባለቤትና አዘጋጅ ኢህአዴግ ቢሮ መባሉ ቀርቶ የወጣቶችና ስፓርት ሚኒስትር እንዲሆን ተደረገ። በወቅቱ ” በመንግስት ውስጥ የድርጅት ስራ መስራት” የሚለው የፓርቲው ፓሊሲ በአዲስ መልኩ መስራት የጀመረበት ነበር። በዚህም መሰረት ሚኒስትር አስቴር ማሞ 5 ሚሊዬን ብር ከወጣቶችና ስፓርት ሚኒስትር በጀት ተቀንሶ ስራ ላይ እንዲውል አደረገች። በተመሳሳይ ሚኒስትር ብርሃን ሐይሉ የመንግስታዊ ሚዲያዎችን የማስተባበበርና ከዝግጅቱ በፊት አጫጭር ዶክመንተሪዎችን እንዲዘጋጅ በማድረግ እንዲያቀርብ ተደርጐ ነበር።
• ከመላው ኢትዬጲያ በኮንፍረንሱ የሚሳተፋ የሊግ አባላት መመዘኛ ወጣ። ለድርጅቱ ባላቸው ፍቅርና አብዬታዊነት ግንባር ቀደም የሚሆኑት በወንፊት ተንገዋለው እንዲለዩ ተደረገ። የፓርቲ ኮንፍረንስ እንዳይመስልና የበለጠ ትኩረት ለመሳብ ሌላም ዘዴ ተቀየሰ። የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ታዋቂ ወጣቶች ከአስር በመቶ ሳይበልጡ እንዲመለመሉ ተደረገ። አትሌት ቀነኒሳ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገብረእግዚአብሔር፣ መሰረት ደፋር በዋናነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ናቸው። ወጣት የኪነ ጥበብ ሙያተኞች፣ ወጣት የዩንቨርስቲ መምህራን፣ ወጣት ሙያተኞችና የሲቪክ አደረጃጀት መሪዎች በአስር ከመቶው ውስጥ የተካተቱበት ነበር።
• ቀጣዩ ተግባር “ለብፃይ!” መለስ የሚቀርብለትን ጥያቄ ከወዲሁ ማዘጋጀት ነበር። ይሄን ሃላፊነት የወሰድነው ህላዌ፣ ፍሬህይወት፣ ካሚል እና እኔ ነበርን። ለመነሻ እንዲሆኑ የአቶ መለስ አስተዳደግ፣ የዩንቨርስቲ ቆይታ፣ የወጣትነት ዘመን፣ ወደ ጫካ የገባበት ምክንያት፣ የጫካ ትግሉና ውጤቱ፣ የስልጣን ህይወቱ፣ ከቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት፣ ከባለቤቱ ጋር መቼና በምን ሁኔታ እንደተዋወቁ፣ የወይዘሮዋ ጠባይ፣ የዘመኑ ወጣቶች ጥያቄ፣ ወጣቶች እንዴት ይታገሉ…ወዘተ የሚመለከቱ 150 ጥያቄዎች አዘጋጀን። ጥያቄዎቹ በጓድ በረኸት አማካኝነት በፓስታ ታሽገው ለአቶ መለስ ተላኩለት። አቶ መለስ 60 የሚጠጉ ጥያቄዎችን ሰርዞ የተቀረውን ለበረኸት ላከለት።
• በማስከተል የፀደቁትን ጥያቄዎች ለወጣቶቹ ማከፋፈል ነበር። ይህን ስራ ወጣት ውብሸት ፣ ካሚል አህመድና ሚኒስት አስቴር ማሞ ሀላፊነት እንዲወስዱ ተደረገ። ጥያቄው የደረሳቸው ወጣቶች በአለባበስ፣ በእጅ አወጣጥ እንዲሁም ሌሎች ሊግ አባላት የውስጠ ውክልና የሰጧቸው በሚያስመስል መንገድ ተቀረፀ። የኮንፍረንሱ እለት ለመለየት እንዲረዳ አቀማመጥ በክልል እንዲሆን ተደረገ።
• ኮንፍረንሱ ተጀመረ። ቀድመው የተዘጋጁት ወጣቶች ” ክቡር ጠቅላያችን የልጅነት ህይወቶን ንገሩን፣ በስንት አመቶት ወደ በረሃ ገቡ፣ የበረሃ ህይወቶ ምን ይመስል ነበር፣ ከባለቤትዎ ጋር ያሎት ግንኙነት ምን ይመስላል?” የሚሉ ጥያቄዎች አዥጐደጐዱ። ብፃይ መለስም ለጥያቄዎቹ አዲስ በሚመስል መልኩ ምላሽ መስጠት ጀመረ። ” ወደ በረሃ የገባሁት የኢትዬጲያ ህዝብ ጭቆና ለማስቀረት ነው!” ጭብጨባ። ጭብጨባ። የማያባራ ጭብጨባ። ” ሚስቴ እሳት የሚተፋ መሳሪያ ስለነበራት ተከባብሮ ለመኖር አማራጭ የለኝም!” ።ሳቅ። ጭብጨባ። ሳቅ። ” መውደድ ብቻውን ትርጉም የለውም፣ መከባበር መጨመር አለበት። ፈረንጆቹ ውሾቻቸውን ይወዳሉ ፣ ነገር ግን አያከብሯቸውም!”። ጭብጨባ። አድናቆት። ጭብጨባ።
#ዛሬስ ምን እየሆነ ነው?
አቶ በረከትና ህላዌ ዬሴፍ ” ዲሞክራታይዜሽን ታስክ ፎርስ” አስተባባሪ ሆነዋል። የዚህ ግብረ ሃይል ዋና ተልእኮ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ከተበላሸ ሸክላ የሚወጣ ሙዚቃ የመሰለውን ፕሮፐጋንዳ ከጀርባ ሆኖ ማስቀጠል ነው። ለዚህም እንዲረዳው የቀድሞውን ክላስተር በሚመስል መንገድ ኢህአዴግ ቢሮን፣ በመላው ኢትዬጲያ ያለውን የህዝብ አደረጃጀት ቢሮ፣ ወጣቶችና ስፓርት ሚኒስትርን በአንድ እዝ እንዲጠረነፍ አድርገዋል። እስከ አሁንም በአዲሳአባ አንድ መድረክ አዘጋጅተዋል። ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስት ደግሞ በኢትዬ ሱማሌና መቐለ ከተመረጡ የድርጅት አባላት ጋር ተወያይተዋል። በተለይ የመቐሌው ስብሰባ የዶክተር አቢይን ቁመና በሚያጠራጥር መልኩ ፈተና ውስጥ እንዲገባ አድርጐታል። ዶክተር አቢይ ፌስቡክን፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዬጲያውያንን፣ የወልቃይት ጉዳይን ለማጣጣል የሄዱበት ርቀት ብዙዎችን አሳዝኗል። የመለስን የሙት መንፈስ በመላበስ ቃል በቃል ” በእሳት የተፈተነ ወርቅ ሕዝብ!” የሚለው አግራሞትን ፈጥሯል። ዶክተሩ የፌዴራል በጀት እንዴት እየተመደበ እንደሆነ አለማወቃቸው ትዝብት ውስጥ ጥሎአቸዋል። ኢትዬጲያዊነትን የሰበከ አንደበታቸው ኢትዬጲያን ለማጥፋት እና ትግራይን ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ የሞቱ ሰዎችን ለመዘከር የተሰራ የልዩነት ጉልጥምት ላይ የጉንጉን አበባ ማኖራቸው አሳፋሪ ሆኗል። እንደ እኔ ያለ ሞጋች ደጋፊያቸው አንገታችንን ሰብረናል። ከጥንስሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ደብረጺዬን መሆን አለበት ብለን መከራከራችን ትክክል መሆኑን አረጋግጠናል።
የሆነው ሆኖ አልባሳቱም ሆነ ሰዎቹ ያልተቀየሩበት ድራማ ይዘቱን ሳይቀይር ቀጥሏል። አሮጌው ወይን በአሮጌ አቅማዳ መቅረቡን ቀጥሏል። እነ ጓድ በረኸት የአብዬታዊ ዲሞክራሲ ልብሳቸውን ገጭ አድርገው ከጀርባ በመደበቅ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሕዝቡ እያራራቁት ነው። እነሱ በኢትዬጲያ ህዝብ እንደተጠሉት ሁሉ ይሄም አዲሱ ሰው በአጭር ጊዜ በኢትዬጲያ ህዝብ እንዳይተፋ ብዙዎች ሰግተናል። አሁንም ቢሆን ተስፋ ሳንቆርጥ ለዶክተር አቢይ አጭር መልእክት አለን። የአይቤን ማን ወሰደው ደራሲ ዶክተር ስቴቨን ጆንሰን ” አዲሱን አይብ ለማግኘት ከአሮጌው አይብ በፍጥነት ተላቀቅ!” ይላል።
             …//…
Filed in: Amharic