>

ዶ/ር አብይ አህመድ በለውጥ ጎዳና እየተምዘገዘገ ነው "ታላቁ መሪ" እኔ ነኝ - እያለህ ነው። (ሞሀመድ አሊ ሞሀመድ)

ዶ/ር አብይ አህመድ በጀመሩት የለውጥ ጉዞ “ከሀዲዱ” የሚወጡ ስለመሆናቸው የዛሬውን የመቀሌ ጉዟቸውን መጠበቅና ማየት ነበረብን። ለኔ የለውጡ ሀድድ የምለው ኢትዮጵያዊነትን ነው። በዘመነ-ወያኔ ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን ባለፈ ሥርዓት ናፋቂነት; አሊያም በትምክህተኝነት ያስፈርጅ ነበር። ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን የብሔር/ብሔረሰቦችን ህልውና እንደመካድና መብቶቻቸውን እንደመደፍጠጥ ይቆጠር ነበር። ስለኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና መቆርቆር በብሔር/ብሔረሰቦች ጥቅሞች እንደመደራደር የሚታይ ነበር። “ኢትዮጵያ” የሚለው ገናና ሥም ከጭቆና; ከጠቅላይነትና ለብዝሃነት ዕውቅና ከማይሰጥ አሮጌ  አስተሳሰብ ጋር  ተሳስሮና አስፈሪ ጥላ ተደርጎ ተስሎ ነበር።
ብዙዎች ከዚህ አስፈሪ ተደርጎ ከተሳለው ጥላ ለማምለጥ ለዓመታት ዳክረዋል። ኢትዮጵያዊነት ግን ሲሸሹት ይከተላል። ሲሸሹት እንደሚከተላቸው አስፈሪ ጥላ አድርገው ስለሳሉት ገና ስሙን ሲጠሩ ያስደነብራቸዋል። ስለሆነም ደፍረው አይጠሩትም። ግድ ሲሆንባቸው “ሀገሪቱ” ብለው ሲያልፉት ታዝበናል። እንዲያም ሆኖ “ታላቁ መሪ” ያሏቸው ነበሩ።
ዶ/ር አብይ ግን “ታላቁ መሪ” እያለ ማላዘንን አልመረጠም። ከጠባብ የመንደርተኝነት አስተሳሰብ ያልወጣ ሰው ለሱ “ታላቅ መሪ” አይደለም። ለዶ/ር አብይ “ታላቅ መሪ” ማለት የአንዲት ሥመ-ገናና ሀገር መሪ መሆኑን በኩራት መናገር ነው። ለእሱ “ታላቅ መሪ” ማለት ስለጋራ እሴቶቻችንና አንድነታችን የሚሰብክ ነው። በሌላ አነጋገር “ታላቁ መሪ እኔ ነኝ” እያለህ ነው። አዎ; የጀመረውን የለውጥ ጉዞ እስካላቆመ;  ከሀድዱ እስካልወጣ ድረስ ዶ/ር አብይ የዘመኔ “ታላቅ መሪ” ነው።
ዶ/ር አብይ ጅጅጋ ላይ የተናገረውን ሰማነው። አምቦ ሄዶም ደገመው። መቀሌ ላይ ሰለሰው። ስለኢዮጵያዊነት; ስለጋራ እሴቶቻችን; በጠንካራ መሠረት ላይ ስለተገነባው አንድነታችን አበክሮ ተናገረ። ለንግግሩ ዋቢ ይሆኑት ዘንድም በርካታ ማሳያዎችን አቀረበ። ህዝብን በስሜት አስጨበጨበ. ..
እነሆ ዶ/ር አብይ በለውጥ ጎዳና እየተምዘገዘገ ነው። መንበረ-ሥልጣኑን ከቆናጠጠ በኋላ የታሠሩ ወገኖች እየተፈቱ ነው። “ፀረ-ህዝብ” “ፀረ-ልማት” “የጥፋት ኃይሎች ተላላኪዎች ”  እና ሌላም ሌላም. .. ሲባሉ የነበሩ ወገኖችን በቤተ-መንግሥት ጋብዞ “ከእንግዲህ መቆዘሙ ይብቃና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላችንን እናበርክት” እያለ ነው።
በርግጥ ዶ/ር አብይ የተናገረውና የተመኘው ሁሉ ይፈፀማል ብሎ ማሰብ ፖለቲካዊ የዋህነት ነው። ከውስጥም ከውጭም ፈርጀ-ብዙ ፈተናዎችና እንቅፋቶች ሊያጋጥሙት እንደሚችሉ መገመትና መጠበቅ አስተዋይነት ነው። ለዚህም ራስን ማዘጋጀትና ዶ/ር አብይ የጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍ ተገቢውን ድጋፍ መስጠት የግድ ነው።
ዶ/ር አብይን ለመደገፍ የግድ የኦህዴድ/ኢህአዴግ አባል መሆን አያስፈልግም። እሱማ እንዴት ተደርጎ? ትልቁ መዳረሻ ግባችን እንጅ መንገዳችን ለየቅል ነው። ስለሆነም በየራሳችን መንገድ በመደራጀት ሰፊ ህዝባዊ መሠረት ያለው; ግልፅ የፖለቲካ አጀንዳዎችን መቅረፅ; ውጤታማ የትግል ስልትና ስትራቴጅ መቀየስ; ብሎም በሁሉም ወገን ዘንድ እምነት የሚጣልበት አማራጭ ኃይል ይዞ መውጣት መቻል ዶ/ር አብይን ማገዝ ይመስለኛል።
ይህም ሆኖ ሁኔታዎች ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሊያመሩ ይችላሉ። ቢሆንስ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ተደራጅቶ መጠበቅ ምን ይጎዳል? ደግሞስ ሁሉን ነገር በጥርጣሬ በማየት የት መድረስ ይቻላል? ሴራ ትንተናን በተንተራሰ አስተሳሰብ ላይ ተቸክሎ የለውጥ እንቅፋት መሆን ለማንም አይበጅም።
እነዶ/ር አብይኮ ዐይናችን እያዬ በለውጥ መንፈስ ወደ ከፍታው መጥተዋል። ኢትዮጵያዊነትን በትውልዱ ፊት ከማቀንቀን; የጋራ እሴቶቻችንን ነቅሶ ከማውጣትና አጉልቶ ከማሳየት;  ኢትዮጵያን ከመውደድ; ህዝብን ከማክበርና የተስፋ ብርሃን ከመፈንጠቅ በላይ ምን ከፍታ አለ?
መሪዬን አግኝቻለሁ፣ ሩጫዬን አጋምሻለሁ
በአቢይ ጉዳይ ላይ መናገር ጉንጭ ማልፋት ነው ።
ያሬድ ጥበቡ
ቀጣዩንም አቅጣጫ አመላክተሃል ። ተጠባባቂነት ቆሞ፣ የልመና እጅን ሰብስቦ፣ ከዜግነት የሚመነጩትን ሃላፊነቶች ተቀብሎ፣ መንግስትንና ኢህአዴግን አንጋጦ በመጠበቅ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያዊ ሃላፊነት በሚመነጭ ስሜት የመፍትሄው አካል መሆን ከሁላችን ይጠበቃል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያደርጉት የሚችሉት ለኢትዮጵያ ለመሥራትና የመፍትሄው አካል ለመሆን ያገዱ ፖሊሲዎችን፣ አሠራሮችን፣ ግትር ባለሥልጣናትን በማስወገድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ በጋራ ያለፍርሃትና ያለሃፍረት፣ ያለመሸማቀቅና ያለመጠራጠር በሙሉ ልብ የምንሳተፍበትን መስክ ማደላደል ነው። በወርቅ ሳህን እንዲያጎርሱን መጠበቅ የለብንም ።
ከዛሬው የመቀሌ ንግግር በኋላ ያለጥርጥር ሃገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ተስፋ በርግጠኝነት ገብታለች። ይህን ተስፋ ዜጎች በድፍረትና በመከባበር፣ በዜጋዊ ቁርጠኝነትና በጨዋነት ከታለመው ያደርሱታል ወይ? የሚለው ህዝቡን የሚመለከት ጥያቄ ነው። ለብዙ መቶ አመታት ከመንግስት እጅ ስንጠብቅ ዜግነታችንን ከምር ሳንቀበል ኖረናል ። አሁንም ዜግነታችንን ከምር ካልተቀበልን የቲም ለማ ትንሽ ጀልባ ብቻውን ከታለመለው ሊያደርሰን አይችልም። ዛሬ የኢትዮጵያ እጣ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመኖርና ባለመኖር ጉዳይ ላይ ተንጠልጥሏል። ከህዝብነት ወደ ዜግነት መሸጋገር ከቻልን፣ የአቢይ ሰናይ ቃላት ሁሉ ህይወት  ይዘራሉ። በተጠራጣሪነት የዳር ተመልካች ሆነን መቀጠሉን ከመረጥን ግን የአቢይ ተስፋ ባዶ የቃላት ክምችት ከመሆን አያልፍም ። ለዜግነታችን ዘብ እንቁም! መሪነቱን ከምር ተቀብለን ዙሪያ መለስ እርዳታችንን እናድርግለት። እኔ በግሌ ለመጀመሪያ ጊዜ መሪዬን አግኝቻለሁ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዜግነቱን ከምር ሲቀበል ደግሞ ሩጫዬን እጨርሳለሁ ። የነገ ሰው ይበለን ። ።መሪያችንን ከፖለቲካ ቡዳዎች ዓይን ይጠብቅልን ። እስቲ እንወቅበት ።
Filed in: Amharic