>

ከ18 አመታት በኋላ… እናቴን አየኋት! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

አዲስ አበባ ውስጥ ሊኖር ይችላል ተብሎ በማይገመት፤ ከአንድ ትልቅ ቪላ ስር በተሰራ የምድር እስር ቤት ውስጥ  ለአንድ ሳምንት ያህል ቆየሁ። ማንኛውም ሰው ወደዚህ እስር ቤት ውስጥ ሲገባ እንጂ፤ በሰላም ሲወጣ አይታይም። የህወሃት ደህንነት እስር ቤት ነው። እስረኛ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ፤ አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ ይደረግና በለሊት ተወስዶ ይገደላል። እኔ ከዚህ እስር ቤት ልወጣ የቻልኩት፤ “በደህንነቶች ታፍኜ መወሰዴ ስለተጋለጠ፤ ይህም ዜና በሳምንታዊው ጋዜጣችን ላይ ስለወጣ እንጂ፤ ዛሬ ይሄን ታሪክ ለመናገርም ሆነ እናቴን ዳግም የማይበት አጋጣሚ አይፈጠርም ነበር።” የሆኖ ሆኖ ከመፈታቴ በፊት… የደህንነት ሃላፊ የነበረው አቶ ክንፈ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠኝ፤ “ዳዊት ከሚገባው በላይ ታግሰንሃል። ከዚህ በኋላ የፕሬስ ህጉም ሆነ ህገ መንግስቱ አያድንህም!” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ።

ከዚያ አሰቃቂ እና አስቀያሚ እስር ቤት ከወጣሁ በኋላ፤ የህትመት ስራዬን ለማቋረጥ ተገደድኩ። እነዘካርያስ እና ግሩም ተክለሃይማኖት ግን “ስራው መቆም የለበትም” ብለው በነሱ ሃላፊነት ፊያሜታ ጋዜጣን ለተወሰኑ ግዜያት ማሳተማቸውን ቀጠሉ። እኔ እጄን ከፕሬስ ስራ ካወጣሁ ጥቂት ቀናት በኋላ፤ የማዕከላዊ ፖሊስ መርማሪዬ የነበረው ጌታነህ ስልክ ደውሎ፤ “አርብ ከሰአት ማዕከላዊ እንድትመጣ” አለኝ። (በወቅቱ ጋዜጠኛው ላይ ክስ ሲመሰረት፤ በስልክ ነበር የሚጠሩን) ከደህንነቱ እስር ቤት የማዕከላዊ እስር ቤት በብዙ እጥፍ የተሻለ ቢሆንም፤ ከእንግዲህ በኋላ አንድም ቀን ቢሆን፤ በእስር ቤት ውስጥ የማሳለፍ ፍላጎት አልነበረኝም። ሌላው ቀርቶ… በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውስጥ የተከሰስኩባቸው አስራ ሁለት ያህል ክሶች ቢፈረዱብኝ፤ የብይኑ ጠቅላላ ድምር… እኔን ለእድሜ ልክ እስር  የሚያበቁኝ ናቸው። በነዚህ ሁሉ ክሶች ላይ አንድም ተጨማሪ ክስ የመቀበል፤ አቅም የለኝም። በመሆኑም ወደማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ መሄዴን ትቼ፤ አርብ ጠዋት ላይ የምወዳትን አገር ለቅቄ ለመውጣት ተገደድኩ።

ከ18 አመታት በኋላ… እናቴን አየኋት!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

አርብ ጠዋት ላይ ነው። እትብቴ የተቀበረበረበትን ቅጥር ግቢ፤ ተወልጄ ያደግኩበትን የቄራዋን ኬላ በር መንደር የምሰናበትበት ቀን ደረሰ። ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ኢትዮጵያን ለቅቄ ለመውጣት ሻንጣዬን ሸክፌ ጨረስኩ። ለብዙ አመታት አብረውኝ ይሰሩ የነበሩትን፤ ሁለቱን ወንድሞቼን ቦሌ አየር ማረፊያ አስቀድመው እንዲሄዱ ነገርኳቸው።

“እኔ ከጓደኛዬ ጋር እዛው እመጣለሁ” ብዬ ሸኘኋቸውና የጓደኛዬን መምጣት መጠባበቅ ጀመርኩ።

እናም አርቲስቱ ጓደኛዬ በቀጠሯችን መሰረት በጠዋት እቤት ሲመጣ፤ “ይቺ ሚጢጢ መኪናህ ተበላሽታ ጉድ እንዳንሆን” እያልኩ ቀልድ ቢጤ ጣል አደረኩ።

“ቀልዱን ተውና ቶሎ እንውጣ፤ ከቤት ሳትወጣ ሁለታችንም እንዳንታሰር።” ፈርቶ ሳይሆን፤ ለቀልድ ያህል የተናገረው ነው።

“ቁርስ በልተን እንሄዳለን።” ብዬው፤ ዘመዴ በጠዋት መጥታ የሰራችልንን ፍርፍር እየበላን፤ ከግራማፎኑ የሚወጣውን “ትዝ ትዝ እያለኝ” የሚለውን የማህሙድ ዜማ ለስንብት እያዳመጥን፤ ከቁርስ በኋላ የቀረበልንን አቦል ቡና እየጠጣን፤ የስንብት ወግ አወጋን።

“በቃ ከዚህ በኋላ አትመለስም?” ይለኛል እየቀለደ።

“እንዴት አልመለስም?” ትኩር ብዬ እያየሁት፤ “ይሄ መንግስት ዘላለማዊ አይደለም። አንድ ቀን ይቀየራል። ያን ግዜ እመለሳለሁ።” አልኩት።

እንዲህ ተጨዋውተን ልወጣ ስል፤ በረንዳ ላይ ጥቅልል ብሎ ተኝቶ የነበረው የግቢያችን ውሻ፤ ባልተለመደ ሁኔታ እግር እግሬ ስር እየተከተለ፤ ለቅሶ በሚመስል ድምጽ ይከተለኝ ጀመር። ዘመዴ የውሻውን ስንብት አይታ፤ ፊቷን በለበሰችው ነጠላ ቢጤ ጨርቅ ሸፍና ማልቀስ ጀመረች። እታችኛው ቤት ከእናቴ ጋር ቡና ይጠጡ የነበሩት ሴቶች፤ እናቴን ተከትለው ሊሰናበቱኝ መጡ።

የኔና የናቴ ስንብት… ባህር ዳር ለሽርሽር ደርሼ እንደምመጣ አይነት፤ አጭር ስንብት ነበር። ምንም አልመሰላትም። ለነገሩ ታስሬ እያለሁ፤ ሰዎች ለማጽናናት ሲመጡ እንኳን ተቆጥታ ትመልሳቸው ነበር። “ልጄ እኮ ወንጀል ሰርቶ አይደለም የታሰረው። ነገ ይፈታል።” እያለች ነበር ሰውን ታረጋጋ የነበረው። አሁንም ጓደኞቿ የሷን ፊት አይተው፤ እነሱም “በሰላም ተመለስ።” ብለው ከመመረቅ ውጪ ፊታቸው ላይ ሃዘን አይነበብም።

እናቴ “አይዞህ እንደገና አገኝሃለሁ።” አለችኝና በስንብት አይነት ጉንጬን አገላብጣ ሳመችኝ። ሁሉም በተመሳሳይ ሁኔታ ተሰናበቱኝና ቡና ወደሚጠጡበት ክፍል ተከታትለው ተመለሱ። ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ… አብረውኝ ያደጉትን የግቢያችንን ወይን፣ የሮማን እና የኮምጣጤ ዛፎች  ተመለከትኩ። ህይወት እንደሮማን እና የወይን ፍሬ ጣፋጭ ብትሆንም፤ አንዳንዴ ትቆመጥጣለች። ይህ ቆምጣጣነቷ ነው፤ አገር እስከመልቀቅ ያስደረሰን። ግቢውን ከመልቀቄ በፊት አየሩ ቅልል ሲለኝ ተሰማኝ። ከሚጢጢዋ መኪና ሞተር በቀር… ሁሉም ነገር ዝም አለ። ሲያለቅስና ሲያላዝን የነበረው ነጭ ውሻችን ጭምር…  ጭምት ብሎ በሆዱ ተኝቶ፤ በሚያሳዝኑ አይኖቹ እያየ ተሰናበተኝ።  ከዚህ በኋላ የማጠፋው ግዜ የለኝም። ሻንጣዬን ከሚጢጢዋ መኪና ኮፈን ውስጥ አስገብቼ፤ ግቢያችንን ለቀን ወጣን።

“የት እንሂድ?” አለኝ አርቲስቱ ጓደኛዬ።

“መጀመሪያ ፒያሳ እንሂድና ከዚያ ወደ ቦሌ…” ስለው፤ ዞር ብሎ አየኝና “መታሰር አልሰለቸህም አይደል? እስኪ ቢሮ ምን ታደርጋለህ?” አለኝ።

ሰራተኞቼን መሰናበት እንደምፈልግ ስነግረው፤ ሚጢጢዋ መኪና እየተሹለከለከች ሄዳ… ፒያሳ አደረሰችን።

ፒያሳ… ባህረ ነጋሽ የአይን ህክምና ከሚገኝበት ህንጻ ላይ፤ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው ቢሮዬ ስወጣ፤ ከፍቅረማርያም ጋር ደረጃው ላይ ተገናኘን። ወደታች እየወረደ ነበር።

ገና ሲያየኝ ተናደደ። “እብድ ነህ እንዴ? እዚህ ምን ታደርጋለህ?” በድፍረት ጮኸብኝ።

“ልሰናበታችሁ ነው የመጣሁት።”

ጓደኛዬን እያየ “ትላንት እሱን ለመያዝ ግቢውን በመሳሪያ ከበው፤ እዚህ ቢሮ ድረስ ገብተው ሲፈትሹ ነበር” የማላውቀውን ወይም ከኔ የደበቁትን ነገር ነው እየነገረኝ ያለው።

ፍቅረማርያም ቁጣው አልበረደለትም። “ምን ወደዚህ እንዳስመጣህ አላቅም። ዝም ብለህ ወደ ቦሌ አትሄድም?” የጥያቄውን ብዛት እና የሱን ስጋት አልወደድኩለትም።

ቁጣውን ከጀርባዬ ትቼ፤ ደረጃውን ወጥቼ ወደቢሮዬ ስገባ፤ ከጸሃፊዎቼ አንደኛዋ ነገሩን ታውቅ ኖሮ እንባዋ ግጥም አለ፤ ቀና ብላ ልታየኝ እንኳን አልቻለችም።

“ዛሬ እንደምትሄድ ፍቅረማርያም ነገረን” አለችኝ።

“እግዚአብሄር ካለ እንደገና አገኛችኋለሁ።” አልኩና አሁን የማላስታውሰውን የስንብት ወሬ አውርተን፤ ተቃቅፈን ተለያየን።

ቢሮዬን ለቅቄ ስወጣ፤ በረንዳው ላይ ሲጋራ እያጨሰ ለሚጠብቀኝ ጓደኛዬ… “ከዚህ በኋላ የትም እንዳትሄዱ! አብዳችኋል እንዴ?” የሚል ማስጠንቀቂያ ቢጤ እየሰጠው ነበር – ጓደኛዬ ለጓደኛዬ።

ፒያሳ ከኔ ቢሮ ከወጣን በኋላ ከፒያሳ ማዶ ወደሚገኘው፤ ሌሎች ጋዜጠኞች ወዳሉበት ቢሮ ሄጄ ልሰናበታቸው አስቤ ነበር። ነገር ግን ይህ የጋዜጠኞች ቢሮ የሚገኘው ከማዕከላዊ እስር ቤት ጥቂት እርቀት ላይ ነው። እነሲሳይ አጌና፣ እነአክሊሉ ታደሰ፣ እነዘገየ ኃይሌ እና ሌሎችም ጋዜጠኞች ይሄንን ቢሮ በጋራ ይጠቀሙበታል። የዚህ ሰፈር ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ አንዳንዴ ከፖሊሶች ጋር ሲቃለዱ፤ “ለእስር ስትፈልጉን እንዳትደክሙ በማሰብ ነው፤ አፍንጫቹህ ስር የመጣነው…” ይሏቸው ነበር።

ሌሎቹን ጋዜጠኞች ለመሰናበት ግዜና እድል ሳላገኝ፤ ሚጢጢዋ መኪና ወደ ቦሌ ተነዳች።እዚያ ወንድሞቼንና ሌሎች የቅርብ ጓደኞቼን አግኝቻቸው ተሰነባበትን። ሪፖርተርን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጦች በእሁድ እትማቸው ከአገር መውጣቴን ዘገቡ። ወደ ውጪ በኋላ ለማህበራችን ፕሬዘዳንት ክፍሌ ሙላት ስደውልለት፤ “እንዴት ሳትነግረኝ፣ እንዴት ሳትሰናበተኝ ትሄዳለህ?” በሚል የፍቅሩን ወቀሰኝ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መውጣቴን ሲሰማ፤ “ዳዊትስ እንኳንም ወጣ… ይገድሉት ነበር።” ማለቱን በኋላ ላይ ሰርኪ አጫወተችኝ።

እናም ካናዳ ለትምህርት ቆየሁ፣ ቀጥሎም በአሜሪካ “የ’ህል ውሃ” ብቻ ሳይሆን፤ የህይወት ነገር ሆኖ… ቀን ቀንን እየወለደ ብዙ አመታት ተቆጠሩ። በውጭ አገር ከአምስት አመታት በላይ የምቆይ አልመሰለኝም ነበር፤ ግን ብዙ ቆየሁ። ይልቁንም ከአገር ከወጣሁ በኋላ፤ ለማመን የሚያስቸግሩ የግፍ ተግባራት በህዝባችን እና በጋዜጠኞቻችን ላይ መፈጸማቸውን ስንሰማ፤ እውነትም በኔ ግትር እና እልኸኝነት.. ለሞት የሚያበቁኝ ብዙ አጋጣሚዎችን በማሰብ፤ “ኧረ እንኳንም ወጣሁ” ብያለሁ ለራሴ። ሌላው ቀርቶ በ97 ግርግር ወቅት በሌለሁበት መከሰሴ ሲገርመኝ፤ አሜሪካ ሆኜ፤ የትንሳኤ ሬድዮን አቋቁመን ስንሰራ፤ መለስ ዜናዊ እና ሚስቱ አዜብ መስፍን፤ በረከት ስምኦን፣ ስዩም መስፍን፣ ስብሃት ነጋ እና በአጠቃላይ 12 ባለስልጣኖች በቨርጂንያ ክስ መሰረቱብኝ። እኔም በድጋሚ… “ኧረ እንኳንም ከዚያ አገር ወጣሁ!” አልኩኝ። ያን ግዜ ቤተሰቦቼን ለማረጋጋት አዲስ አበባ ስደውል፤ አባቴ… “ይሄ ክስ አንተን ብቻ ነው የሚመለከተው ወይስ ሌሎችም አሉበት?” አለኝ።

“ሌሎችም ሰዎች አብረውኝ ተከሰዋል።” ስለው፤ “ልጄ ብቻህን መጠቃት ጥሩ አይደለም። ሌሎችም ካሉበት ደህና!” አለኝ።

እናቴም፤ “አይዞህ ሻማ እያበራሁ ለእመቤቴ ማርያም እጸልይላታለሁ፤ ምንም አትሆንም። ስለቴንም እሷ ትሰማለት።” አለችኝ።

በእርግጥ በዚያ አስከፊ ግዜ… ብዙዎች ከጎኔ ቆመው፤ “አይዞህ” አሉኝ። በተለይም ጠበቃዬ የነበረው ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ፤ በሚገርም ሁኔታ ክሱን ወደነሱ አዙሮት፤ “በበቃኝ” ተሸንፈው፤ ድምጻቸውን አጥፍተው… ክሳቸውን አንስተው እንዲጠፉ አደረጋቸው።

እናም ሁሉም ነገር አለፈ። እስር ቤት እያለሁ ሊጠይቀኝ ሲመጣ፤ “እውነት ስለተናገርክ ነው የታሰርከው። ጨው አይደለህም አትሟሟም። ነገ ትፈታለህ።” ይለኝ የነበረው አባቴ፤ የመጀመሪያ ልጁን፤ በእህታችን ዶ/ር ፍሬሰላም ከበደን ሞት ጥልቅ ሃዘን ገብቶት፤ በዚያ ላይ ህመም ተጨምሮበት ከዚህ አለም በሞት አለፈ። ከቤተሰብ ተለያይቶ መኖር ከባድ ነበር ነው። ሌላኛው ትንሽ ወንድሜንም በቅርቡ አጣሁት። እናቴም እድሜዋ እየገፋ መጥቶ፤ ሳንተያይ ብዙ አመታት ተቆጠሩ። ወደ አገር ቤት የመመለሱ ነገር የማይታሰብ ሆነ። የመጨረሻውን አማራጭ ለመምረጥ ከራሴ ጋር ለብዙ አመታት ከታገልኩ በኋላ፤ ‘ቢያንስ እናቴን እንኳን ልያት’፤ በሚል የማልፈልገውን ፈለግኩ… ከሁለት አመታት በፊት የአሜሪካ ዜግነቴን ወሰድኩ።

አገሬ የነፈገችኝን ፍቅር እና ነጻነት ያልተወለድኩባት አሜሪካ፤ እንደገና ገጸ-በረከት ለገሰችኝ። እነሆ የአሜሪካ ዜግነቴ… እናቴን አንከብክቦ አመጣልኝ። አትላንታ በሚገኘው ኤርፖርት ተገኝቼ እናቴን ልቀበላት ስሄድ፤ ብዙ ነገር ወደ ኋላ ተመልሼ እንዳስብ አደረገኝ። ብዙ ነገር ተለዋውጧል። በአገራችን ጠቅላይ ሚንስትሮቹ ጭምር ተለዋውጠዋል። ብዙ መስዋዕት የከፈልንበት… “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት” ክፉኛ ተጎድቶ፤ ኮማ ውስጥ ነው ያለው። ብዙ በጣም ብዙ ነገር ተቀያይሯል። ከላይ በታሪኬ ውስጥ ከገለጽኳቸው ሰዎች መካከል፤ የደህንነት ዋና ሃላፊው ክንፈ በሰው እጅ በሽጉጥ ተገድሏል። ብዙ ጋዜጠኞች እንደወጡ ቀርተዋል።

ከአገር ቤት ስወጣ የመጨረሻውን ቁርስ ያበላችን ዘመዴ… “እቤት እጠብቅሃለሁ” ብላ ደወለችልኝና… ሌሎቹን ሴቶች ተቀላቅላ እራት እየሰራች፤ ቡና እያፈሉ ይጠብቁን ጀመር። እኔ ከአገር ቤት ስወጣ ትንሽ ልጅ የነበረው ትንሹ ወንድሜ፤ አበልጁን፣ ባለቤቱንና ሁለት ልጆቹን ይዞ …እናቴን ልንቀበላት አብረን መጥተናል። በታሪኩ ላይ የጠቀስኩላቹህ ቦሌ ድረስ የሸኙኝ ሁለቱ ወንድሞቼ… አሁን ካናዳ ነው ያሉት።

ከላይ በታሪኩ ውስጥ የጠቀስኩላቹህ አርቲስቱ ጓደኛዬ ሚጢጢ መኪናውን ጥሎ ብዙ ግዜ ብዙ ውድ መኪኖችን ገዝቷል። …ወደቢሮዬ ልገባ ስል ደረጃው ላይ ያገኘሁት አብሮ አደግ ጓደኛዬ እና ጸሃፊያችን ተጋብተው… 3 ልጆች ወልደው፤ አንዱን ልጅ ለኔ ክርስትና ሰጥተው፤ አበልጆች ሆነን አሁን ሜሪላንድ ይኖራሉ። ቦሌ ላይ ከተሳናበቱኝ አርቲስቶች መካከል ደረጄና ሃብቴ ይገኙበታል። ሃብቴ በሞት ሲለይ፤ ደረጄን ከጥቂት ወራት በፊት የኮሜዲ ዝግጅት ሊያቀርብ አትላንታ መጥቶ ተገናኘን። እነሲሳይ አጌና በ97 ምርጫ ታሪክ ሰርተው፤ ከዚያም ታስረው… ዛሬ ደግሞ ውጭ አገር መጥተው የኢሳት ዋና ምሰሶ ሆነው ይሰራሉ። እስክንድር ነጋም ከእስር ተፈትቶ ዳግም ወደ አሜሪካ ለመምጣት እየተዘጋጀ ነው። ግሩም ተክለሃይማኖት የመን አገር ስደት ላይ ሆኖ፤ በርካታ መጽሃፎችን ጽፏል። ከላይ በስም የጠቀስኳቸውን ጋዜጠኞች ጨምሮ ከመቶ በላይ የምንሆነው እንደጨው ዘር በመላው አለም ተበታትነናል። እናም በነዚህ አመታት መካከል… ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። የሚያልፉ የማይመስሉን ቀናቶች አልፈዋል። ሁሉም ነገር አላፊ ነው። የኛም ትውልድ እያለፈ… የዘመናችን ጀንበር እየጠለቀች፤ ሌላ የጠዋት ጸሃይ ለአዲሱ ትውልድ እየፈነጠቀች ናት።

እኔም ጋር ትንሽዬ ጸሃይ ፈንጥቃለች። ሻማ እያበራች ለቅድስት ማርያም ጸሎቷን ታቀርብ ለነበረችው እናቴ፤ እግዚአብሔር እድሜ ሰጥቷት፤ ከአስራ ስምንት አመታት በኋላ አይኗን በአይኔ ለማየት በቅቻለሁ። ወደነጭነት የተቀየረው ዞማ ጸጉሯ አሁንም አለ፤ የፊቷ ቆዳ ተሸብሽቧል፤ ውብ አይኖቿ በእርጅና ደጃፍ ላይ ቢሆኑም፤  ዛሬም ጥልቅ የሆነ የፍቅር ጨረር ይረጫሉ። የተቀመጠችበትን ጊዜያዊ ተሽከርካሪ እየገፋሁ ወደ ውጭ ወጣንና የወንድሜን መኪና መምጣት ስንጠብቅ…

“ዳዊትዬ…” አለችና እጇን ወደ ጉልበቴ ዘረጋች።

“ምነው እማ?” አልኳት።

“ስለት አለብኝ” አለብኝ አለችኝ።

“የምን ስለት?”

“ቅድስት ማርያም፤ ልጄን ያገናኘሽኝ ‘ለት፤ ጉልበቱን እስማለሁ ብዬ ተስያለሁ።” አለችና ወደጉልበቴ የላከችውን ቀኝ እጇን ደጋግማ ሳመችው። ሃዘንና ሳቅ፤ ደስታና ሳግ ተናነቀኝ። ከ18 አመታት በኋላ ሳገኘት ስሜቴን ተቆጣጥሬ ዝም ብዬ ነበር። አሁን ግን ወንድነቴን የሚፈታተን ቃል ከእናቴ ሰማሁ። “አሁን ግን ጉልበት አነሰኝ” ስትለኝ፤ የወንድነት እንባዬን ወደ ውስጥ ዋጥኩትና እኔው ራሴ ጎንበስ አልኩ።

“እማዬ! ስለትሽ በኔ ይለፍ!” አልኩና ጎንበስ ብዬ ጉልበቷን ሳምኩ።

በዚያች ቅጽበት ውስጥ እኔና እናቴን፤ እኔና ቤተሰቤን፤ እኔና ጓደኞቼን… እኔና አገሬን ስለለያየው የአገራችን ስርአት አሰብኩ። እንደኔ እድለኛ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ለዚህ እድል ያልበቁ መኖራቸውን አስቤ አዘንኩ። እንደ’ናቴ ተስለውና መልካም ተመኝተው፤ ናፍቆታቸውን ለተወጡት ወገኖቼም ደስ አለኝ። ይህን እድል ያላገኙ ጓደኞቼም፤ እድሉን ያገኙ ዘንድ… መልካሙን ሁሉ ተመኘሁላቸው።

በዝምታ ውስጥ ጥልቅ ትዝታ ውስጥ ገባሁ። ከአየር ማረፊያው ተነስተን፤ ወደቤት ለመሄድ የአትላንታ ጎዳናዎችን እየሰነጠቅን መንገድ ጀመርን። የምሽት ጉዟችን… ስለፕሬስ ነጻነት እየወደቅን የተነሳንበትን የትግል ምዕራፎች አስታወሱኝ። እነሆ የጠቆረውም ሰማይ… ያለፍንባቸውን የጨለማ አመታት እያስታወሰኝ፤  የመንገዱ ዳር መብራቶችም… የወደፊት ተስፋችንን እያመላከቱኝ፤ በደስታ እና በትዝታ… ጥልቅ በሆነ ዝምታ ውስጥ ሆነን… ጉዟችንን ወደ ቤት አደረግን። ከ18 አመታት በፊት አገር ለቆ የወጣው ነፍስ እና ስጋዬ… ለእናት አገሩ ባይበቃም፤ ቢያንስ እናቴን አግኝቶ ደስ አለው። የተቆረጠ የሚመስል ተስፋን የሚቀጥል አምላክ ይመስገን… ስብሐት ለአብ ይሁን!

Filed in: Amharic