>

ምስጋና እና ክብር ለአምቦ ሕዝብ፤ (ውብሸት ሙላት)

አምቦ ለወደደው ማር ለጠላው ኮሶ ነው፡፡ አምቦ ሲወድህ አቅፎ ሲጠላህ ገርፎ እንጂ እዝሎ አያኖርህም፡፡ አምቦ በመብቱ  ጉዳይ አይደራደርህም፡፡ ለአምቦ መብቱ ያው መብቱ ነው፡፡ አምቦ ይታገሳል እንደሁ እንጂ መልመጥመጥ አያውቅም፡፡ አምቦን በእስራት፣አምቦን በመግደል አምቦ እንዳያይሆን ማድረግ አይቻልም፡፡ አምቦ ምንጊዜም ያው አምቦ ነው፡፡
አምቦ አክብረው ያከብርሃል፡፡ ወደደው ይወድሃል፡፡ ከጠላኸውም ይጠላሃል፡፡ አምቦን እንደ መንግሥት ብትወጋው እንኳን እንደ ሕዝብ ይገጥምሃል፣ ይዋጋሃል፡፡ አምቦ ጥንትም ዛሬም ያኼው ነው፡፡
አምቦ፣ ሁሉንም በየዓይነቱ አስተናግዷል፡፡ በዐጼ ኃይለሥላሴም፣ በደርግም በኢሕአዴግም የመንግሥታትን አገዛዝ በክፉም በደጉም መልኩ አስተናግዷል፡፡ አምቦ የአመነበትን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተለይ በዘመነ ኢሕአዴግ እንደ አምቦ ኢሕአዴግን ፊት ለፊት የተጋፈጠ፣ ለስፍር ቁጥር የሚያዳግት ልጆቹ የተገደሉበት፣የታሠሩበት ማንም የለም፡፡
አምቦ ካልወደደህ ልጁም ቢትሆን አይተውህም፡፡ በሆነ ወቅትና ጊዜ አንዴ ስላልወደድከው ብሎም እሱም ስላልወደደህ በዚያው ግትር ብሎ የሚቆይ አይደለም-አምቦ፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ምሳሌዎቹ ዶ/ር መረራና ኦሕዴድ ናቸው፡፡ ዶ/ር መረራ ወጣት እያሉ (በመጥላት ባይሆንም) ለደርግ አሳልፎ ቢሰጣቸውም ቅሉ መልሶ ግን አቅፎ፣ደግፎ፣መርቆ፣ሸልሞ ተቀብሏቸዋል፡፡ አላግባብ ሲታሠሩም እንዲፈቱ ልጆቹን ገብሮላቸዋል፡፡ የሕይወት መስዋእትነት ሳይቀር ከፍሎላቸዋል፡፡ እስራትና ሌላ ሌላውንማ ማን ቆጥሮት፡፡
አምቦ ላመነበት ግንባሩን ለጥይት፣አንገቱን ለሰይፍ፣ደረቱን ለጦር ይሰጣል እንጂ እግሬ አውጭኝን አያውቅም፡፡ በስንት አፈናና ጭቆና ውስጥ ሆኖ እንኳን በ1997 ዶ/ር መረራን እንዴት እንደ ደገፈ የምናውቀው ነው፡፡የቅርብ ትዝታ ነው፡፡ በቅርቡ ከእስር ሲፈቱም (በቀለ ገርባን ጨምሮ) ልክ እንደዚያው እንደ 97ቱ ተቀበላቸው፡፡
 ኦሕዴድንም ቢሆን አምቦን አምቦን አልሸት ከማለት አልፎ አምቦን የማይወድ ሆኖ ሲያገኘው  አባሮታል፤ በዚህም እነ ደራራን ጨምሮ ስንት ሕወይት ከፍሏል፡፡ አሁን ደግሞ ኦሮሞ ኦሮሞ፣አምቦ አምቦ የሚመስሉ መሪዎችን ሲያገኝ ቂሙን እርግፍ አድርጎ ትቶ እነ ዶ/ር አቢይን፣ለማ መገርሳን እና ሌሎች ባለሥልጣናትን አቅፎ፣ አክብሮ፣ ሸልሞ፣ ዘምሮ ተቀብሏል፡፡
እናም፣ አምቦ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዴሞክራሲ የከፈለው መስዋእትነት መቼም የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡ አሁን ላለው ሁኔታም የአምቦ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለአምቦ ክብርና ምስጋና ይገባል፡፡ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኔያቸውን እንኳን ሳያዋቅሩ አምቦ መሔዳቸው ተገቢ ነው፡፡ ለመስዋእትነቱ ዕውቅናና ምስጋና ይገባዋልና! ከጉብኝት ባለፈ ሌላም ሌላም ይገባዋል አምቦ!
እናም፣  “ምነው አምቦ?”  የምንልበት ቀን ድጋሜ አይምጣ፡፡ በረከት፣ ልማት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እንጂ ድጋሜ ሐዘኔታና ክፋት እንዳይነካት ምኞታችን ነው፡፡
ይህን ዓይነት ምኞት፣ ምንም እንኳን አምቦ ያኔ ያጋጠማት ችግር ሌላ ቢሆንምና በሌላ ዐወድ ቢጻፍም፣ ከአባራኳ ክፋይ  ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በ1960 ዓ.ም. የዛሬ 50 ዓመት ላይ፣ ቢመኙላትም እሳካሁን ያው “ምነው አምቦ?” እንዳልን ነው፡፡

ምነው አምቦ?

ምነው አምቦ….

የደማም አምባዎች ቁንጮ፣ እንዳልነበርሽ የደም ገምቦ፣
እንዳልነበርሽ ንጥረ-ዘቦ፣
ዙሪያሽ በምንጭሽ ታጅቦ፣
በተራሮችሽ ተከብቦ፣
ከጠበልሽ ሲሳይ ታልቦ፣
ከአዝእርትሽ ፍሬ ዘንቦ፣
ከዓመት ዓመት ጤና አብቦ፣
ሕይወት ደርቶ ሰላም ቀርቦ…
የአየር ትፍስሕት እንዳልነበርሽ፣የዘር ሆነ የእሸት አትክልት፣
ከመጫ እስከ አዋሽ አምብርት፣
ምንጭሽ ሲያጥጥ ሲፍለቀለቅ፣ከዳንዲ እስከ ዋንጭ እትብት…
እንዳልነበርሽ የምድር አድባር፣የዘር ድባብ ያገር ችቦ፣
ዛሬ እንደዚህ ምነው አምቦ፣
የቀትር ጥላሽ ተስቦ፣
የጡቶችሽ ወዝ ተሰልቦ፣
ውስጥ አንጀትሽ ተለብልቦ፣
የመዓዛሽ መፍለቅለቂያ፣መንጸባረቅሽ ተሸብሽቦ፣
ተረምርሞ ተተብትቦ…
ምነው?…. ምነው አምቦ?
1960 ዓ.ም. አምቦ ጸጋዬ ገብረመድኅን ቀዌሳ፡፡
Filed in: Amharic