>

ከወልቃይት ወጣቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ  አቤቱታ (ጌታቸው ሽፈራው)

~”የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ሪፖብሊክ  መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር  በማንነት ጥያቄ  ምክንያት እስካሁን  የተፈፀመብንን ግፍ አልበቃ ብሎ አሁን በአዲስ መልክ  የተጀመረውን  የማንነት ጠያቂ ኮሚቴዎችን የማጥቃት ዘመቻ  ከእኛ ከተከሳሾቹ አልፎ  የወልቃይት አማራ ሕዝብ ስነ ልቦና በከፍተኛ ሁኔታ  የሚጎዳ  እና ሕገ መንግስታዊ  መብቱን  የሚያፍን  ኢ_ዲሞክራዊያዊ  አካሄድ  መሆኑን  ተገንዝቦልን አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ  እንዲወስድልን በአክብሮት እንጠይቃለን።”
~”የወልቃይት ህዝብ በሰበብ አስባቡ ተበትኖ  ከተወለደበት ሀገር  ወጥተን ስደተኛ እንድንሆን፣ እኛን እያሰሩ  እና እያባረሩ  የትግራይን ሕዝብ  በእኛ እርሻና ቤት እየተኩ  የወልቃይትን ሕዝብ ከስር መሰረቱ  ለመንቀል እንደሆነ  ከግምት አልፎ እውነትነት እየታየበት ያለ ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ይህም በማስረጃ የምናረጋግጠው  እውነታ እንጅ አሉባልታ አይደለም።”
አዲስ ክስ የቀረበባቸው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ የአዲረመጥ ወረዳ አስተባባሪዎች
ሚያዝያ 3/2010 ዓም
ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
ለፌደራል  ጠቅላይ አቃቤ ሕግ
አዲስ አበባ
 አመልካቾች:_
1ኛ አቶ ፈረደ እሸቱ አበጋዝ፣  ወረዳ አዲረመጥ፣  ስራ ነጋዴ
2ኛ አቶ አባይ ማማዬ እጅጉ፣ ወረዳ አዲረመጥ፣  ነጋዴ
3ኛ  አቶ ደሞዝ መልኬ ሰጣርገው፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ ገበሬ
4ኛ አቶ ክብረአብ ስማቸው የሽወንድም፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ ሾፌር
5ኛ  አቶ ፈረደ በሪሁን  ባርጎ፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ መምህር
6ኛ አቶ ታምራት ደሳለኝ ደረሰ፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ስራ ተቋርጧል
 7ኛ አቶ እንዳለው ብርሃን ፣ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ መምህር
8ኛ አቶ ሞላ አበላይ በላይ፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ መምህር
9ኛ ልዑል ሐጎስ ገ/ር፣ ወረዳ አዲረመጥ፣ ስራ መምህር
 ጉዳዩ:_ የማንነት ጥያቄ በማንሳታችን ብቻ የተመሰረተብን ክስ እንዲቋረጥልን
 እኛ  ከላይ ስማችን  የተጠቀሰው  አመልካቾች  ሁላችንም የወልቃይት ተወላጆች ስንሆን የወልቃይት  አማራ ሕዝብ ለበርካታ አመታት  ከፍላጎቱ ውጭ  የተነጠቀውን የአማራ ማንነቱን ለማስመለስ በሕግ አግባብ መሰረት ጉዳዩ ይመለከተዋል ለተባለው  የመንግስት አካል  አቤቱታ ማቅረብ ከጀመረ  በርካታ አመታት አልፈዋል።  እኛም የማንነት አስመላሽ  አስተባባሪዎች ነን።
ነገር ግን  ሕዝቡ  ለሚያቀርበው ጥያቄ  ሕጋዊ መልስ ከመስጠት ይልቅ  የሌለ ነገር  እየተፈጠረ የወልቃይትን ሕዝብ ማሰር፣ ማሳደድና ሰውሮ ማጥፋት እየተባባሰ በመሄዱ ወደመንግስት ተቋማት  አቤቱታ በየደረጃው   ከቀበሌ ጀምሮ   እስከ ዞን   እና ሀገር አቀፍ ደረጃ  አቤቱታውን  በሕገ መንግስቱ  መሰረት በማቅረብ ላይ  እንዳሉ ከሐምሌ  5/2008 ዓም  ከፍተኛ  የኮሚቴ አባላትን  ጎንደር  ላይ ከፊሎቹን በሌሊት አፍነው  ሲይዙ  ከፊሎቹን ደግሞ  በሌሊት አንያዝም በማለታቸው  ከፍተኛ ጥቃት የደረሰ ቢሆንም በሕዝብ ድጋፍ  በሕጋዊ መንገድ ወደ ሕግ ቀርበው  የተከሰሱበት የሽብር ክስ  አግባብ እንዳልሆነ ታምኖበት  ክሳቸው  ተቋርጦ ተለቅቀዋል።
መንግስት ክሱን ሲያቋርጥም  ከፍተኛውን የፖለቲካ እና የመንግስት ስልጣን የያዙት  አካላት ሁኔታውን ገምግመው  የአማራን ሕዝብ ለግጭት የዳረገው  የመንግስትና የፖለቲካ ድርጅቶች አሰራር ስህተት  መሆኑን፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በአግባቡ፣ በሕጉ መሰረት መመለስ ባለመቻሉ  ችግሩ ሊከሰት መቻሉን  ታምኖበት  ክሱ እንዲቋረጥ  መደረጉን የመንግስት ስልጣን የያዘውፓርቲ የአራቱ ድርጅቶች  መሪዎችና  የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር  በመገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ከላይ በተገለፀው መሰረት  በሀገሪቱ ሰላምን ለማምጣት  መንግስት ማንኛውም ነገር  በሕግ አግባብ መመለስ እንዳለበት  እምኖ ተገቢውን ሰላማዊ እርምጃ እየወሰደ  ባለበት ወቅት  ከላይ ስማችን የተጠቀሰው  አመልካቾች  በ2008  ዓም እና በ2009 ዓም  መጀመርያ ላይ  ከጎንደር ከተማ  እና ወልቃይት ውስጥ  ተፈፀሙ የተባሉ   ነገሮችን ተጠቅሰው  የወንጀል ሕግ አንቀፅ 241 እና  የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001  አንቀፅ  4 ተጠቅሶ “የሕዝቦችን አንድነት መንካት” በሚል  ሕዳር 21 ቀን 2010 ዓም  የተፃፈ ክስ ለከፊሎቻችን ተሰጥቶናል። ከፊሎቻችን የመንግስት ሰራተኛ ሆነን በስራ ላይ ያለን ሲሆን ከፊሎቻችን በግብርና እና ንግድ ስራ ተሰማርተን ግብር እየከፈልን በመንግስት የሚሰጡንን ሌሎች ስራዎች ሁሉ እያከናወንን እንገኛለን።
ይልቁንም እኛ በምንኖርበት ወረዳ የወልቃይት አማራ ሕዝብ ማንነት ጥያቄው  አስተባባሪ ኮሚቴዎች  በመሆናችን  የወልቃይት ሕዝብ አማራ ማንነት ጥያቄውን በህጋዊ መንገድ  ብቻ  ለሚመለከተው አካል  በማቅረብ  ሕጋዊ ምላሽ ማግኘት የሚችል መሆኑን እና መልሱ  ዘገየ ብሎ  ከሕግ ውጭ መሄድ ለማንም እንደማይጠቅም ምክር የምንሰጥ  መሆናችን ሕዝብ ያውቃል። በወልቃይት ጠገዴ በየትኛውም ወረደና ዞን ደረጃ ላይ ያሉ የትግራ ክልል ባለስልጣናትም  ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ።
በክሱ ላይ ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ  እኛ ከሕዝብ እና  ከመንግስት ጋር ይህን ጥያቄ በምናቀርብበት ሰዓት  ድረስ በሰላም ያለ ምንም ችግር  እንደምንኖር እየታወቀ  ማንነት ጠያቂ ስለሆንን ብቻ  የማንነት ጥያቄያችን እንድናቆም  የሀሰት ክስ የቀረበብን  መሆኑን  ተገንዝበናል። በትግራይ ክልል  የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ወኪል ይኖራል ብለን ብንገምትም  ዋናው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ  የማያውቀውን ጉዳይ በውክልና  የተቀመጠ ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመስረት የሚያስችል የሕግ ስልጣን አለው ብለንም አናምንም።
 በተለይ በመንግስት ደረጃ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ድርጊቱ ተፈፀመ በተባለበት ወቅት  አሁን እኛ ፈፅማችሁታል የተባልነው  ድርጊት  ከወንጀል ሕግ አልፎ በሽብርተኝነት ተከሰው  የነበሩ ሰዎች ክሳቸው በተቋረጠበት ሁኔታ  በእኛ ላይ አዲስ ክስ መመስረቱ  የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄውን  እንዲያነሳ በእኛ ለማስፈራራት  እና እኛንም ለመበቀል፣ በተለይም የወልቃይት ህዝብ በሰበብ አስባቡ ተበትኖ  ከተወለደበት ሀገር  ወጥተን ስደተኛ እንዲንሆን፣ እኛን እያሰሩ  እና እያባረሩ  የትግራይን ሕዝብ  በእኛ እርሻና ቤት እየተኩ  የወልቃይትን ሕዝብ ከስር መሰረቱ  ለመንቀል እንደሆነ  ከግምት አልፎ እውነትነት እየታየበት ያለ ሁኔታ ላይ ደርሰናል። ይህም በማስረጃ የምናረጋግጠው  እውነታ እንጅ አሉባልታ አይደለም።
የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ቅርንጫፍ ነኝ በማለት ክሱን የመሰረተብን አካል  በክሱ ላይ  የገለፃቸው ድርጊቶች  በእኛ የተፈፀሙ ባይሆንም  ጎንደር  ላይ  ተከሰተ ለተባለው  ነገር እኛ ገበሬዎች እና ነጋዴዎች  የጎንደርን ሕዝብ  ለተቃውሞ የምናነሳሳበት አቅም እንደሌለን እየታወቀ  በእኛ ላይ የተፈጠር  ምክንያት በቂ ካለመሆኑ  በላይ ጎንደር ከተማ ላይ ተፈፀመ ለተባለው ድርጊት የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን የሚያይበት ስልጣን ሳይሆረው  ሆን ተብሎ በእኛ እና በቤተሰቦቻችን ላይ  ከዚህም አልፎ በወልቃይት ሕዝብ ስለማንነቱ ትንፍስ  እንደይል እኛ ማስፈራሪያ እንድንሆን ታስቦ የቀረበ ክስ መሆኑን ተገንዝበናል።
ለዚህ በቂ ምክንያት  ያለን ሲሆን እኛ አሁን በተከሰስንበት ድርጊት  ወደ ሽብርተኝነት ወንጀፅ ተቀይሮ  ቀደም ብሎ  የተከሰሱት  የኮሚቴ አባላት  ክስ ተቋርጦ  መለቀቃቸውን ዓለም አውቆት እያለ አዲስ ምክንያት  በመፍጠር “የሕዝብ አንድነት መንካት” በሚል ሌላ ምክንያት መከሰሳችን  አንድም ከላይ እንደገለፅነው  የወልቃይት ተወላጆችን በሰበብ አስባቡ  ከትውልድ ቀያቸው  የማስለቀቅ አላማ  ነው። ወይንም ደግሞ አሁን  እየተፈጠረ ያለውን  ሰላም የማይፈልግ አካል አለ ወደሚል መደምደሚያ  ሊያደርሰን ይችላል።
ስለዚህ “የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ትግራይ ቅርንጫፍ” የካቲት 2 ቀን 2010 ዓም  ተሰጠ  በተባለ ትዕዛዝ  በፖሊስ በኩል ለከፊሎቻችን የተሰጠ ክስ  የትግርኛ ቅጅ  እና የአማርኛ ትርጉም ፎቶ ኮፒ 11 ገፅ አያይዘን እያቀረብም  ዐቃቤ ሕግ ሰላማዊ መፍትሄ  እየተፈለገለት ባለ ነገር  አዲስ  ምክንያት ተፈጥሮ የቀረበው ክስ  እንዲቋረጥ ክሱን ለመሰረተው አካል መመሪያ እንዲያስተላልፍልን።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ሪፖብሊክ  መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር  በማንነት ጥያቄ  ምክንያት እስካሁን  የተፈፀመብንን ግፍ አልበቃ ብሎ አሁን በአዲስ መልክ  የተጀመረውን  የማንነት ጠያቂ ኮሚቴዎችን የማጥቃት ዘመቻ  ከእኛ ከተከሳሾቹ አልፎ  የወልቃይት አማራ ሕዝብ ስነ ልቦና በከፍተኛ ሁኔታ  የሚጎዳ  እና ሕገ መንግስታዊ  መብቱን  የሚያፍን  ኢዲሞክራዊያዊ  አካሄድ  መሆኑን  ተገንዝቦልን አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ  እንዲወስድልን በአክብሮት እንጠይቃለን።
Filed in: Amharic