>
5:13 pm - Saturday April 19, 8966

ያልታሰበው H.Res 128 ውሳኔ እና የህወሃት መብረክረክ (ክንፉ አሰፋ)

ያልታሰበ ነው። ፈጽሞ ያልተገመተ። አገዛዙን እንደ ቀትር መብረቅ ያስደነገጠ ውሳኔ። በጸረ-ሽብር ስም በሚተውኑት የፖለቲካ ድራማ ሳብያ አሜሪካ ይህን አይነት ውሳኔ አጋር በሆነ አካል ላይ ትፈጽማለች ብለው ለአፍታ እንኳን አስበውት አያውቁም። በዚያ ላይ ደግሞ በሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው ሎቢስቶች ጉዳዩን ይዘውልናል ብለው ተዘናግተዋል። “ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አሕመድ እድል እንስጥ” የሚለው የኦክሎሃማው ሴናተር ጄምስ ኢንሆፍ ሃሳብ ያሸንፋል የሚል ግምትም ነበራቸው። ንቀታቸው እና ትዕቢታቸው የት እንደደረሰ የተመለከትነው፤  ሰነዱ ምክር ቤት ሊቀርብ ቀናት ሲቀረው እንኳ ዜጎችን ከእኩይ ተግባራቸው ያልመቆጠባቸው ነው። በሽብር የወነጀሏቸውን የዋልድባ መነኮሳት አሁንም እያሰቃዩዋቸው ይገኛሉ። ሰነዱ ሊጸድቅ አንዲት ቀን ሲቀረው በምስራቅ ሀረርጌ፤ ቆቦ ከተማ ነፍሰጡርዋን በጥይት ደበደቧት። በመጀመርያ አስገድደው ደፈሯት። ከዚያ ገደሏት።

 ለሰብዓዊ ክብር የቆመ እና ሁሉን አቀፍ አስተዳድርን የሚደግፍ ሰነድ፤  ውሳኔ H.Res 128።  በዩናይትድ ስቴይትስ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ፊት ቀርቦ ያለ አንዳች ተቃውሞ ጸድቋል።  ይህ አስደንጋጭ ውሳኔ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነትን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ይመስላል።

ይህ ሰነድ አያሌ መሰናክሎችን አልፎ ለውሳኔ በቀረበበት ቅጽበት አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን፤ ለአሜሪካ ኮንግረስ አንድ የተማጽኖ ደብዳቤ ልከው ነበር። እኚህ ሰው ከተለመደው የጸረ-ሽብር ማስፈራረያ ወጣ ብለው፤ መንግስታቸው ለለውጥ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት ተናግረዋል።   በነገሩ ላይ በግልጽ ለመምከር፤  ለጋራ ውይይትም ጋብዘዋል።  “ውሳኔ ከማስተላለፍ ተቆጠቡ”  ብለው የሕግ መምሪያ ምክር ቤቱን ቢጠይቁም፤ ጅብ ካለፈ… ሆነና አልተሳካም።

 “በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ይቁም፤ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያ እውን ትሁን!” የሚል ሰነድ ማውጣይ፤  ከፋቱ ምኑ ላይ እንደሆነ የሚረዱት የአገዛዙ ተጠቃሚዎች ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ “አልሻባብምስራቅ አፍሪካን ይወርራታል” የሚለው የዘወትር የህወሃት ነተላ ዜማ አሁን ስለተበላ ጨዋታቸውን የቀየሩ ይመስላል።

የእነ ስብሃት ነጋ “አይጋ ፎረም”፤  እንደ ደብተራ ክታብ በቀይ እና በጥቁር ቀለም አሸብርቆ አሜሪካን መሳደብ ጀምሯል።ውሳኔው አስገዳጅ ያልሆነ እና ተፈጻሚነትም እንደማይኖረው አይጋ ነግሮናል።  በዚህ አላበዋም።  በሃገር ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ ሲልም የአሜሪካ ኤምባሲን ያስጠነቅቃ። የአሜሪካው አምባሳደር በኢትዮጵያ የጀመሩትን “የብተና ተልዕኮ” አስመልክቶ ጠ/ሚንስትር አብይ አህመድ ተንካራ መልዕክት እንዲያስተላልፉም ያሳስባል።

የነ አባይ ጸሃይ “ትግራይ ኦንላይን” ድረ-ገጽም፤  የተለመደው የኒዮ ሊብራል ትርክት ይዞ ታላቋ አሜሪካን ለመሳደብ አፉን ከፍቷል። የሰብአዊ መብቱን ጉዳይ ሳይሆን የቻይና ጣልቃ ገብነት አሜሪካን እንዳላስደሰተ ሊነግረን ሞክሯል።

የወያኔ ብሎገሮችም ዝም አላሉም። የአንዳንዶቹ ሃሳብ እንደ ፔንዱለም መዋዠቁ ግን የተስፋ መቁረጡ እና የፍርሃቱን መጠን ይገልጸዋል። አንዱ ብሎገር “ውሳኔውን የሀዘን መግለጫ ነገር ነው። ለዛ ነው ድምጽ ራሱ ያልተሰጠበት።” ሲል ጽፏል።

“የሃዘን መግለጫ” ያሉት ይህ ውሳኔ እንዳያልፍ ከ80 ሚልዮን ብር በላይ ለምን እንዳወጡበት ግን ሊነግረን አይደፍርም። ውሳኔው “ምንም አያመጣም” ካሉን ታዲያ አሁን ሲጸድቅ ለምን ብርክ ያዛቸው?

ይህ ሰነድ ውሳኔ ሊሰጥበት የነበረው ባለፈው አመት ኦክቶበር 2 / 2017 ነበር።  በወቅቱ በገጠመው የታሰበ እክል እንዲራዘም ተደረገ።  የተራዘመበት ምክንያትም ግልጽ ነው። “ይህ ሕግ ካለፈ ከአሜሪካ ጋራ የሚኖረን ጸረ-ሽብርተኝነትን ድጋፍ እናቆማለን” በማለት የወያኔ መንግስት በይፋ ተናግሮ ነበር። ምክንያቱን ልብ በሉ! በንግድ ልውውጥ አይደለም።  በባህልና ቱሪዝም ጉዳዮችም አይደለም። በጸረ-ሽብር ላይ አብሬ አልሰራም ነው ያሉት። የአሜሪካን ጦርነት የኢትዮጵያ ልጆች እንዲወጡት፤ ሁለቱ አካላት በፊት ለፊት ሳይሆን በጓሮ በር የተፈራረሙትን ሰነድ እንቀድደዋለን ሲሉ ነበር ያስፈራሩት። አንድ የአሜሪካ ዜጋ በሶማሊያ ምድር ላይ ከሚሞት ብለው፤ አንድ ሺህ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስንገብር ነበር።

ሰነዱ እንዲሞት አገዛዙ ከፍተኛ  የማባበል(ሎቢ) እና የማስፈራራት ስራ አየሰራ እንደነበር የተከበሩ እንደራሴ ማይክ ኮፍማን ተናግረዋል።  ሾልኮ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመን አገዛዙ ይህን ለሚሰሩ ሎቢስቶች በወር 150ሺህ ዶላር ይከፍላል።ይህ ረቂቅ እዚህ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ሃገሪቱ ካላት ውስን የውጭ ምንዛሪ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏል።   እየገደሉ መኖርን መብታቸው ካላደረጉት በስተቀር ይህንን ያህል ገንዘብ ለባዕድ ደላሎች ከማዋል ይልቅ በገንዘቡ በርካታ ትምህርት ቤቶችን እና ክሊኒኮችን ይገነቡበት ነበር።

“በኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ክብር የቆመ ሁሉን አቀፍ አስተዳድር እንዲኖር”፤  በማለት የሚጀምረው ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉትን የመብት ጥሰቶችና በደሎች ያወግዛል። የአገዛዙ አካል ከልክ ያለፈ ሃይል መጠቀም እንዲያቆም።  በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተካሀደው ግድያ እና ስቃይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ገዳዮቹ/አስገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ። የሚሉ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ጠንካራ ድንጋገጌዎችን ይዟል። ድንጋገዎቹ ተፈጻሚ ካልሆኑ የሚወሰዱ እርምጃዎችም በአፈጻሰሙ ላይ ተገልሰዋል።

አሜሪካ እና አውሮፓውያን ላለፉት ሶስት አስርተ-ዓመታት ለራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ሲሉ፤ የኢትዮጵያ ችግር ችላ ብለው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። የኢትዮጵያ ችግር አሁን ካለበት ጫፍ ደርሶ፤ ስርዓቱ ህዝባዊ እንቢተኝነት መንገዳገድ ሲጀምር የአሜሪካ የፖሊሲ ማሻሻል ለማደእግ መሞከርዋ፤ እንደተለመደው ሃይል ሚዛኑን ተከትሎ ቢሆንም አሁንም አልረፈደም። ህወሃት ሕዝባዊ መሰረት የሌለው፤ በመሳርያ ሃይል ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተቀመጠ ደካማ ድርጅት ነው። የአሜሪካ የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ባይኖረው ኖሮ እስካሁን በስልጣን ላይ ሊቆይ እንደማይችል ሁሉም ይገነዘባል።

በአሜሪካ ሳንባ የሚተነፍሱት የአውሮፓ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ከዚህ በኋላ ዝምታቸውን ይሰብራሉ። የዚህን ሰነድ መጽደቅ ተከትለው ለጋሽ ሃገሮች ተመሳሳይ እርምጃ በወያኔ ላይ መውሰዳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ከአመታዊ በጀቱ አንድ ሶስተኛው ገንዘብ የሚመታው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ህብረት ነው። የሰራዊቱን እና የደህንነቱን ደሞዝ እየፈሉ ያኖሩት ሃይሎች ፊታቸውን ሲያዞሩበት በኒዮ-ሪበራል ዜማ አሲዮ ቤሌማን ቢዘፍን አይደንቀንም።

Filed in: Amharic