>

አፋን ኦሮሞን በግእዝ ፊደል ...(ያሬድ ጥበቡ)

አፋን ኦሮሞን በግእዝ ፊደል እንዲፃፍ ወስኑና፣ እኛም አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በጋራ እንታገል!!!
ለማ መገርሳን አድምጡት ።  የተባረከ አእምሮ ያለው ሰው ነው። የፖለቲካ ቃላት ስለማይገልጡት ነው ወደ አባቶቻችን ቋንቋ መሄድ የተገደድኩት ። ለማ በሁለቱም ቋንቋዎች ሲናገር ስሰማው፣ ምን ታሰበኝ መሰላችሁ? ምንም እንኳ አማርኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋችን ቢሆንም፣ ዶክተር አቢይ አህመድ ሥልጣኑን በሚረከቡበት ቀን በሚያደርጉት ንግግር ላይ አማርኛንና ሳይበዛም በመጠኑም አፋን ኦሮሞን ቀላቅለው ቢናገሩ፣ በደሙ እየከፈለ ለዚህ ቀን ያበቃቸውን የኦሮሞ ቄሮና ህዝብ እጅግ ያስደስተው ይመስለኛል ። ይመጥነዋልም ። በተለይ አማርኛ ለማይሰሙት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኦሮሞዎች በጉጉት የሚጠብቁት ንግግር ስለሚሆን በቋንቋቸው ሲሰሙት እጅግ ያስደስታቸዋል፣ ሃገርም ያረጋጋል ብዬ አምናለሁ ።
አቦ ይህን ኦነግ ከኢትዮጵያ የተለየ ሃገራዊ ማንነት ለመፍጠር ይረዳል በሚል የጫነብንን የላቲን ቁቤ እርግፍ አድርጋችሁ ተዉና፣ አፋን ኦሮሞን በግእዝ ፊደል እንዲፃፍ ወስኑና፣ እኛም አፋን ኦሮሞ ተጨማሪ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እንርዳችሁ ። ግእዙን ከኛም አልፈን ወደተቀረው አፍሪካ ይዘን መሄድ የሚገባን ብቸኛው አፍሪካዊ ፊደል ስለሆነ፣ እስቲ ከቤታችን እንጀምረው ። ኦሮሞ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ክብርን የሚጠይቀውን ያህል፣ እርሱም ኢትዮጵያን ማክበር አለበት። ቀዳሚው፣ እንደ ሃገር በአንድ ፊደል በመጠቀም እስቲ መከባበሩን በጋራ እንጀምረው። አድዋ  ላይ ጣሊያንን የመከቱና ስል የነሱ የኦሮሞ አባ ፈርዳ ልጆች፣ በላቲን ሲፅፉ አያመርባቸውም ። የፈረንጅ ባርነትም ይመስላል ። ቢያንስ ቀሽም ነው። እስቲ እዩት በሞቴ ቄሮ ማለት ይቀላል ወይስ QUEEERROOO? አይዞን!
Filed in: Amharic