>

መንግስታቸውን በሚያመልኩ ሰዎች ስንሰቃይ ኖረን ዛሬ አምላኪና አስመላኪ ሆነን እንዳንገኝ!?! (ደረጀ ደስታ)

እነ አይቶ አጣ ቤት ጎመን የተቀቀለ ቀን ሲጨበጨብ ያድራል ይባላል። አገሩንና ሰላሙን የተቀማ የመሰለው ሁሉ ሰሞኑን የተስፋ ጎመን አገኝቶ ሆያ ሆዬ ይዟል። ቆሽቱ በግኖ ድል ጠምቶት ለኖረ ዋይታን ለዘመረ ሁሉ ትንሽ ተስፋ ነፍሱን ታለመልማለች። ቢሆንም ታዲያ የተስፋ ምኞቱ ከእውነታው ቅዥቱ ካልተለየ ተስፋ ለተጣለበትም ሰው ሆነ ለተስፈኛው ህዝብ ችግር መሆኑ አይቀርም። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከሰማይ የወረዱ ልዩ አጋጣሚ እንጂ ልዩ ሰው አይደሉም። አቶ ለማ መገርሣ እንደዱላ ቅብብሎሽ ሯጭ ከመጨረሻዪቱ የድል መስመር የተገኙ ራጭ እንጂ ከእሳቸው በፊት ሚሊዮኖች ሮጠዋል። ኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑን የተናገሩበት አውድ መድረክና አጋጣሚ ነው ልዩ ያደረገው እንጂ አነጋገራቸው ሰበር ዜና ሆኖ አይደለም። ይገነጠላሉ ተብለው ማስፈራራያ የሆኑ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያዊነት ሲያወሩ የኢትዮጵያዊነት መሠረት ነን እያሉ ያቅራሩት እንገነጠላለን ብለው ሲያቅማሙ ማየቱ ግን ያስገርማል። መገንጠልም ወደ እናት ክፍሏ ልትመለስ መንገድ ያዘች ብለን መስጋታችንም አይቀርም። ብሔር ቅዳ ብሔር መልስ ጨዋታ በሞላባት ኢትዮጵያ የትኛው ሀሳብ ወደ ሥልጣን መጣ ማለቱ ቀርቶ የትኛው ብሄር ወደ ሥልጣን መጣ እያሉ አለሁበት ወይስ የለሁበትም ብሎ ማስላቱ ደግ አይደለም። ተረኝነትን መሰረት ያደረገ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ፖለቲካ አንድነትን አያመጣም። የአብይ የነገ ሥራዎች ሳይታዩ ከወዲሁ በቀብድ የማጨብጨብም ሆነ የመቃወም ነገር እየታየ መሆኑ ግልጽ ነው።
አስገራሚው ነገር ትላንት “መንግሥታችን ልማታችን” ያሉ ሰዎች ባንዲት ጀምበር ተገልብጠው መንግሥትን ማጥላላት ሲጀምሩ እኛ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችንንማ አትንኩ ማለት ጀምረናል። ነገ መንግሥታችንን ማለታችን አይቀርም። እንግዲህ ቦታ ተለዋውጠን እነዚህን የልማትና የአንድነትና የዴሞክራሲ ጸሮችን እምንቃወምበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ይልቁንስ ቀልዱን ትተን መንግስት ሁልጊዜም መንግሥት ነው። በባህርዩም ወስላታ ስለሆነ ምንም ይሁን ምን መደገፍ የለሌበት ተቋም ነው። ሊከታተሉት ሊቆጣጠሩት ሊጠረጥሩት እሚያስፈልግ ተቋም መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። በመንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሀሳቦችን አንዳንድ ፕሮግራሞችና አገራዊ አቋሞችን መደገፍ እንችላለን መንግሥትን በጅምላ ከመደገፍ ግን በጅምላ መቃወሙ የተሻለ ይመስለኛል። መንግሥት ራሱን እሚደግፍበትና እሚያስደግፍበት ብዙ አቅም አለው። እንደ አብይ ያሉ ሰዎችን ማስተዋወቅና ህዝብ እንዲገዛቸው መሸጥ ማለፊያ ስራ ነው። እንዲያመልካቸው ማስገደድ ግን እነ አብይንም አገርንም መግደል ይሆናል። ያውም እኮ መንግሥታቸውን ሲያመልኩ በኖሩ ሰዎች ስንሰቃይ ከኖርበት ዘመን ገና አልተላቀቅንም። መንግሥትህ ውስጥ ሆነህ መንግሥትህን ተቃወም ማለትም ሲናገሩት መቅለሉ ጠፍቶን አይደለም። መንግሥት ውስጥ ሁሉ ያሉ ሰዎች መንግሥትን መቃወም ያለባቸው የመሆኑ ረቂት ጥበብ አጓግቶን ነው። ምርጫ ማለት ዋሽንግተንን እሚለወጥ ሰው ወደ ዋሽንግተን የመላክ ጨዋታ ሆኖ እምናየው ለዚህ ይመስለኛል። ሰዎቻችን የተመራረጡበት ምርጫ መሆኑ ቀርቶ ምርጫ በህዝብ እንዲሆን ማድረጉ ግን ገና ያልተፈጸመ መሠረታዊ ጥያቄ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic