>
5:14 pm - Friday April 20, 1421

በፍጥጫ ና በውጥረት የታጀበው ስብሰባ (ሀብታሙ ኪቲባ)

“…. ከደም ለሚወፍረው ዘላለማዊ ትስስር ያለመታከት በመልፋት አንድነትን ይንከባከባል- ይሞሽራልም!!!” ዶ/ር አብይ
[በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ከተንጸባረቁ ሃሳቦች እና ንግግሮች ከፊሉን]
[አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ አገላለጾች እና ምልልሶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸውን በማመዛዘን ከመረጃ ምንጬ ጽሁፍ ቆርጬ አውጥቼያቸዋለሁ፡፡]
ከኢህአዴግ አክራሞት (በከፊል)
መቼም ጊዜ ያልፍና ስለእዚህ ዘመን ታሪካዊ የኢህአዴግ ሰዎች ስብሰባ ወደፊት በዝርዝር በመጽሐፍ እናነብ ይሆናል፡፡ አንድቀን እነርሱም እንደ ደርግ ስለአለፉበት ዘመን; በየስብሰባው ስለነበረው ሁኔታ; ማን ምን እንዳለ; አንድ ውሳኔ እንዴት እንደተወሰነ; ወዘተ ያስነብቡን ይሆናል፡፡
እነርሱ ከፓርቲ ስርዓት ተፋተው በነጻነት እስኪነግሩን ድረስ እኛም የምናገኘውን ሽርፍራፊ መረጃ እየገጣጠምን ሁኔታዎችን ለማጤን እንሞክራለን፡፡ ይህ እኮ ኢትዮጵያ ነው በቲውተር ሳይሆን በቃለጉባኤ ውሳኔ የሚጻፍበት፡፡ ቲውተር ፌስቡክማ … ተውኩት፡፡ ወደ ተነሳሁበት ልቀጥል፡፡
በሰሞኑ የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ የተባሉ እና የሆኑ ተብሎ የተጻፉትን አንብበናል እንዲሁም ሰምተናል፡፡ እስኪ እቺን ጨምሩባት እና ስብሰባው ውስጥ የነበረውን መፋጠጥ ሆነ መሳሳቅ ለመሳል ሞክሩ ልላችሁ ወደድኩና ሞባይሌን ነካካሁ፡፡ አንዳንዴ ከባድ ውጥረት; አንዳንዴ የቃላት መወራወር; አንዳንዴ ደግሞ ሳቅ፡፡ የቃላት መወራወሩን ሁሉ እዚህላይ አምጥቶ ማስጣት የሃሳብ ልዩነትን በጨዋ ደንብ ከማስተናገድ ይልቅ የስድብ ሰይፉን ፈጥኖ ለሚመዝ የፌስቡክ ማህበረሰብ የሚጎዳ ነውና በተመረጡ ጥቂት ሃሳቦች ላይ አተኩሬአለሁ፡፡
ከሁሉ በፊት ከልቤ ለፖለቲከኞች እንደማዝን ይታወቅልኝ፡፡ ከማዘንም ባሻገር የጸሎት ርእሶቼም ናቸው፡፡ አይ ፖለቲካ! በእውነት የፖለቲከኛን ሰው የስራ ዋጋ በተለይም የሃቀኛ ፖለቲከኛን “የላብ ወዝ እንጀራ” እራሱ እግዚአብሔር ካልከፈለ ማን ከፍሎ ይጨርሰዋል? ከስራዎች ሁሉ ከባዱ ስራ የፖለቲካ መሪነት ስራነው፡፡ ረጃጅም ስብሰባ;  ክርክር; ጭቅጭቅ; ከተለያዩ ሃሳቦች ጋር ፍጥጫ; የደህንነት ስጋትና በጠባቂ ታጅቦ መንቀሳቀስ; የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማስታረቅ መጨነቅ ወዘተ
ይኸው የሰሞኑ ስብሰባ ገጽታ በከፊል
የኢህአዴግ ታሪካዊው ስብሰባ ሊጠናቀቅ እና ህዝብን በተለያየ ጎራ የከፈለ የመሰለው የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫ ውጤት ሊሰጥ ሰዓታት የቀሩት ይመስላል፡፡
ልዩ ትኩረት የተሰጠው የጠቅላዩ ምርጫ ጉዳይ ላይ የተደረጉት የቃላት መወራወሮችን እና የስብሰባ አዳራሹን ያሰሳቀውን የዶክተር አቢይን ንግግር እነሆ ብዬአለሁ፡፡
ከእዚህ በፊት የኦህዴድ ሰው እና የደኢህዴን ሰው እንዲህ አሉ ተብሎ የተዘገበውን ዘገባ ምንው ህውሓት ያለውስ አብሮ አልተዘገበ ስል መጠየቄ ይታወሳል፡፡ ስለሆነም በሕውሓት ሰዎች በተነሱ ሃሳቦች እና በህዝብ ዘንድ ተጠባቂው ጠቅላይ አብይ አህመድ የተናገራቸው ንግግሮች ላይ አተኩሬ ይህን አስነብባለሁ፡፡
እስኪ ከህወሓት ሰዎች አቋም እንጀምር፡-
ዶክተር አቢይ አህመድ (የኦህዴድ ሊቀመንበርና ተጠባቂው ጠቅላይ) “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” እያሉ የሚደጋግሙት ነገር ለህወሓቶች አልተዋጠላቸውም ይላል የመረጃ ምንጬ፤ ይሄንን የሰውየውን ፍቅረ ኢትዮጵያ አቋም ሁለት የህወሓት ሰዎች መረዳታቸውን የገለጹበት መንገድ የተለየ ነበረ፡፡
ለመሆኑ እኒህ ሁለት የሕወሓት ሰዎች የዶ/ር አቢይን “ኢትዮጵያ; ኢትዮጵያ” ማለት እንዴት የሚረዱት ይመስላችኀል?
እንደ ሰዎቹ እምነት ከሆነ የዶክተር አብይ ኢትዮጵያ ላይ መጣበቅ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ወደሌሎቹም ክልሎች እንዲዛመት ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡ አዎን ነገርዬው ቶሎ የሚገባ አይደለም፡፡ ኦሮሚያን ከኢህአዴግ እውቅና ውጪ ከሌሎች ክልሎች ጋር ለማቀራረብ ከተደረገው ሙከራ ለመገንዘብ እንደቻሉት አማራም አንጻራዊ መነቀቃት የፈጠረው (የማፈንገጥ አዝማሚያ) ከኦህዴድ የተጋባበት ነው፡፡ ኦህዴድ በክልሉ የፈጠረው ነጻነት ጦስ ነው ወደ አማራ የተሻገረው እንደማለት፡፡
እንደ ህወህት የፊትለፊት ሰዎች የመከራከርያ ነጥብ ይሄ ህዝብ ዴሞክራሲ ቀስ እየለ እንጂ በአንድ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም የሚል ነው፡፡
እኔ በበኩሌ ሰዎች ለምን የተለየ ነገር አሰቡ ሊባሉ አይገባም ባይ ነኝ፡፡ ማንኛውም ሰው የፈለገውን የማሰብ; ሃሳቡን የሚከተሉት ለማግኘት መስራት (በህጋዊነት); የሌላውን ሃሳብ እንዲሁ ለመስማት ጥረት ማድረግ ወዘተ ይገባዋል እላለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ይህንን ሃሳብ ማን ደገፈው ማንስ ተቃወመው ማለታችን አይቀርም፡፡
ይሄ ሃሳብ በስብሀት ነጋ፣ በአባይ ጸሀዬ እና በተወሰነ መልኩም በበረከት ስምኦን ተደግፎ የቀረበ ሀሳብ ሲሆን በርካታ የብአዴን እና የኦህዴድ ሰዎች የተቃወሙት ሀሳብ ነበረ፡፡ ሃሳቡን አምርረው ከተቹት መካከል አቢይ አህመድ፣ ፍቃዱ ተሰማ እና ገዱ አንዳርጋቸው ግንባርቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዶክተር አቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሰጠው አስተያየት “የኢትዮጵያን ህዝብ ለዲሞክራሲ ባእድ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ አላዋቂነት ነው” የሚለው ይገኝበታል፡፡
[አንዳንድ አላስፈላጊ የሆኑ አገላለጾች እና ምልልሶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸውን በማመዛዘን ከመረጃ ምንጬ ጽሁፍ ቆርጬ አውጥቼዋለሁ፡፡]
• በጦፈው ክርክር መሃል ሌላው የዶክተር አቢይ ንግግር “እናንተ በወረዳቸሁበት ደረጃ ወርደን አንነጋገር ከተባለ ህዝቡ ዲሞክራሲ ትንሽ ትንሽ ሰጥተነው ከሚወቅሰን አብዝተን ሰጥተነው በዛብኝ ብሎን ለምን ታሪክ አንሰራም፡፡ ትንሸ ትንሽ የሚባል ዲሞክራሲ የለም ግድየለም አስቲ እኛ ያለገደብ እንስጠውና ትን ይበለው” ሲል ተሰብሳቢዎች ስቀዋል፡፡
• ኦህዴድ የራሱን ክልል ስልጣን ብቻ ይዞ በነበረበት ወቅት ውጪ ካሉ ተቃዋሚ ሀይሎች ጋር እንደራደር የሚል ድፍረት የተሞላበት ግብዣ ያቀረበው የአቢይ እና የለማ ቡድን የፌዴራሉን ስልጣን ከያዘ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለስም የሚል ብርቱ ስጋት ህወሓቶች ዘንድ መፈጠሩ ታይቷል፡፡ ኦህዴድ የተሸራረፈ ስልጣን እንዲወስድ ለቀረበለት ሃሳብ ሊቀመንበሩ ዶክተር አቢይ የሰጠው ምላሽ “እኔ የማንም ፍላጎት እና ሀሳብ ማስተላለፍያ ቧንቧ መሆን አልፈልግም፡፡ በቀደዱልኝ ቦይ የምፈስ ጎርፍ ሳልሆን የራሴን ፈለግ የምተልም ሰው ነኝ፡” በማለት ተናግሯል፡፡
• በስብሰባው ላይ በዶክተር አቢይ ላይ ከተመዘዙት ሰይፎች መካከል “ዶክተር አቢይ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በነበረ ጊዜ አገራዊ እርቅ እና ከልብ የሆነ የሰላም ኮንፈረንስ ሊደረግ ይገባል እንዳላቸውና ይህም ጸብ ስለሌለ እርቅ አያስፈልግም ከሚለው የግንባሩ አቋም ጋር የሚጋጭ ነው” በማለት ከፓርቲው መስመር ውጪ እንደሚሄድ ለማንሳት ተሞክሯል፡፡
• ብዙዎችን ያስጨበጨበ ነገርግን በህወሓት መንደር ያልተወደደው የአቢይ ንግግር:- “ከዚህ በኋላ ለሀገራዊ አንድነት እና ለብሄራዊ ስሜት ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን፡፡ ስለሚያለያዩን ነገሮች 27 አመታት ሙሉ ስንጮህ ብንቆይም አንድ ስለሚያደርጉን ነገሮች ለመናገር ግን ሰከንዶቸ ክፍለዘመን ሆነውብን ኖረናል አሁን የሄ መቀየር አለበት፡፡ ፓርቲዬ ኦህዴድም የኦሮሞ ህዝብ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ከነፍስ የተሰናሰለ ልባዊ ወንድማማችነቱ እንዲጠናከር ይሰራል፤ ከደም ለሚወፍረው ዘላለማዊ ትስስሩም ያለመታከት በመልፋት አንድነቱን ይንከባከባል- ይሞሽራል፡፡”
ከፍጥጪያውም ከአስቂኝ ንግግሩም
ከሚስጥራዊ ድምጽ መስጫ ሰዓት በኀላ ምናልባትም በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ለአጭር ጊዜ ስልጣን የሚይዘው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ይመረጣል፡፡ ይህ ሰው በመንታ መንገድ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ወይ #በፍቅር ወይ #በጠመንጃ ሊገዛት ይነሳል፡፡ #በጠመንጃ_እና_በአምባገነንነት ካልሆነ መረን የወጣውን መመለስ አልችልም የሚል ጠቅላይ በሆነ ጊዜ እስርቤቶች የለቀቁትን ሁሉ መልሰው ያስሩ ይሆናል፡፡ በስተመጨረሻ ወደ ማይቀርበት ወደ ሚመስለው #የሽግግር_መንግሥት!!!
ሰላሙን ለኢትዮጵያ!
መጋቢት 17  
ወንድማችሁ!
ሐብታሙ ኪታባ
Filed in: Amharic