>
5:13 pm - Monday April 19, 1593

ሺዎች የሚተላልቁለትን ዙፋን "ለእኔ አይገባኝም" ያሉት ትሁቱና የጦሩ ገበሬ  ራስ ዳርጌ (ከታሪክ አምባ)

ወንደሰን ተክለማሪያም

የአጼ ምኒልክ አጎት የሆኑት ራስ ዳርጌ ከሸዋው ንጉሥ ሳህለሥላሴ እና ከወ/ሮ ወራጌ በ1822 ዓ/ም በሸዋ አውራጃ ተወለዱ፡፡ የልጅነት ጊዜያቸውንም በአንኮበርና በአንጎለላ አሰልፈው ትንሽ ከፍ እንዳሉ ወደ ጎንደር ተጉዘው የአጼ ቴዎድሮስ ባለሟል ሆኑ፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ ዘንድ እያሉም ራስ ዳርጌ በበጎ ሃሳባቸው፤ በጦር ሜዳ ጀግንነታቸው፤ በጉግሥ ጨዋታ ዘንግ አወራወር ብቃታቸው ምክንያት በሁሉ ዘንድ ተወዳጅነትን አገኙ፡፡

አጼ ቴዎድሮስም ከፍቅራቸው የተነሳ ዳርጌ ከማለት ይልቅ ዳሩ ወይም ዳርዬ እያሉ በቁልምጫ ይጠሯቸው ጀመር፡፡ በጊዜውም በሸዋ ላይ ያስተዳድሩ የነበሩት መርዕድ አዝማች ኃይሌ አጼ ቴዎድሮስን በመክዳት ተጠርጥረው ታስረው ነበርና ቴዎድሮስ ዳርጌን በሸዋ ላይ እንደሚሾሙ ተናገሩ፤ ሆኖም ግን አጼ ቴዎድሮስ ከሹመቱ በፊት የራስ ዳርጌን የደመቀ የጦር ሰፈር አይተው በጣም ስለሰጉ ቀጥታ አስጥርተዋቸው “ዳርዬ ፈራሁህ በጥንድ ጦር የሚስተውን ኃይሌን ሽሬ በነጠላ ጦር ደርበህ ሁለት ሰው የምትገለውን አንተን በሸዋ ላይ አልሾምም” ብለው በግልጽ ነገሯቸው፤ ራስ ዳርጌም ሳይከፉ “እሺ” ብለው ቴዎድሮስን በትህትና እጅ ነሱ፡፡ ከጊዜያት በኋላም አጼ ምኒልክ ከመቅደላ አመልጠው ሸዋ ገብተው አጼ ቴዎድሮስም መጨረሻቸው ደርሶ በመቅደላ ሲያርፉ ራስ ዳርጌ ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ሸዋ ተጉዘው ከአጼ ምኒልክ ጋር ተገናኙ፡፡

አጼ ምኒልክም በሸዋ ነግሠው ነበርና ራስ ዳርጌ እንደመጡ “እርስዎ ቀጥታ የሳህለሥላሴ ልጅ ስለሆኑ ንጉሥነቴን ልተውልዎ” አሏቸው ራስ ዳርጌም መልሰው “የለም አባቴ ሳህለሥላሴ አልጋቸውን አውርሰው የሞቱት ቀጥታ ለአንተ አባት ለኃይለመለኮት ነው አሁንም በዚሁ መስመር ነው ነጋሲነቱ መቀጠል ያለበት” ብለው እንቢ አሉ፡፡ ከዚህም ወዲያ ራስ ዳርጌና ምኒልክ እንደአባትና ልጅ ሆነው ለዘመናት ኖሩ፡፡ አጼ ዮሐንስ እና አጼ ምኒልክ በተቀያየሙ ጊዜ እንኳን ወቅሰው እና መክረው የሚያስማሙ ራስ ዳርጌ ነበሩ፡፡ በታላቁ የአድዋ ጦርነት ወቅትም ራስ ዳርጌ በአዲስ አበባ በመሆን በአጼ ምኒልክ ቦታ ሀገሪቱን ሲመሩ ቆይተው ከድሉ በኋላ ሥልጣኑን መልሰው ለምኒልክ አስረክበዋል፡፡ በመጨረሻም ራስ ዳርጌ ለሁሉ እንደአባት ሆነው አሩሲን አቅንተው ሰላሌ እና አካባቢውን ሲያስተዳድሩ ቆይተው መጋቢት 15 ቀን 1892ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ቀብራቸውም በደብረሊባኖስ ተፈጽሟል፡፡

ምንጭ፦ አጤ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተክለጻዲቅ መኩሪያ
– የሕይወት ታሪክ በብላታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ
– ዕለታዊ የታሪክ ድርጊት በመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ

(ምኒልክ ዳግማዊ)

Filed in: Amharic