>
5:13 pm - Saturday April 19, 4273

ዶ/ር አብይ ከተመረጠ መፈንቅለ መንግስት ማየታችን ነው!!! (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

ሰሞኑን የህወሃት ድረገጾች ዶ/ር አብይን አስመልክቶ የሚያወጧቸውን ጽሁፎች ስመለከት አንድ ነገር ታዘብኩ። ጽሁፎቹን የሚጽፉዋቸው ወታደራዊ አዛዦች ናቸው። ብዙዎቹ ጸሃፊዎች ከዶ/ር አብይ ጋር ኢንሳ ውስጥ አብረው ስለመስራታቸው ይገልጻሉ። ዶ/ር አብይ በሲቪል አስተዳደር ውስጥ ስለሰሩት ስራ አንድም ሰው ትችት ጽፎ አላነበብኩም። እንግዲህ የጸሃፊዎችን ማንነት ስመለከት የዶ/ር አብይ ዋና ተቃዋሚዎች ወታደራዊ አዛዦች ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል። አዛዦቹ ዶ/ር አብይን ወይም ኦህዴድን በ 3 ምክንያቶች ሊቃወሟቸው እንደሚችሉ እገምታለሁ፦
አንደኛው፣ በኢትዮ ሶማሊና በኦሮምያ ክልል ድንበር አካባቢ የሚካሄደውን የኮንትሮባንድ ንግድ ማስቆማቸው ነው። የዚህ ንግድ ዋና ተዋናዮቹ ወታደራዊ አዛዠች መሆናቸው የተባለ ነገር ነው።
ሁለተኛው ምክንያት በሜቴክ ስም ኦሮምያ ውስጥ የሚዘርፉትን ማእድን፣ መሬትና ሃብት በማስቆማቸው ነው። ሜቴክ በማን እንደሚመራም የሚታወቅ ነው።
ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ ስነልቦናዊ ይመስለኛል። አብይ መከላከያ ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ከአምሳለቅነት እስከ ሻለቃነት በነበረው ማዕረጉ ለአለቆቹ ወታደራዊ ሰላምታ እየሰጠ እየታዘዘ የኖረ ሰው ነው። በወታደራዊ ስነስርዓት ከበላይህ ቀድመህ ስልጣን ልትይዝ አትችልም። “ሲኒየርቲ” ወሳኝ ነው። ከበላይህ ቀድመህ ስልጣን ለመያዝ ወይ እንደ መንግስቱ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ አለብህ አልያም ስልጣኑን ለያዘው ሰው ታማኝ መሆን አለብህ። አብይ ጠ/ሚኒስትር ከሆነ እነሳሞራ በአደባባይ ወታደራዊ ሰላምታ ሊሰጡት እና ሊታዘዙለ ግድ ነው ። ትናንት ሰላምታ ሲሰጥ የነበረ ሰው ዛሬ ሰላምታ ተቀባይ ሊሆን ነው ማለት ነው። ሳሞራ ትናንት ሲያዘው ለነበረው ሰው ነገ በአደባባይ ወታደራዊ ሰላምታ ሲሰጠው አይታየኝም፤ ሌሎቹም እንዲሁ።
እንግዲህ አብይ በታምር ጠ/ሚኒስትር ቢሆን፣ አንድ የህወሃት ጸሃፊ እንደገለጸው፣ አገሩ በሙሉ ይተራመሳል። ትርምሱን የሚያስነሱት ደግሞ እነሳሞራ ይሆናሉ። ከዚያም “አብይ አገር ማረጋጋት አልቻለም” ይሉና ከስልጣን አንስተው የዝምባብዌ ወታደሮች እንዳደረጉት የሚፈልጉትን ሰው ሾመው ከጀርባ ይገዛሉ። አብይ ጠ/ሚኒስትር ካልሆነ ደግሞ የሚመጣ ሌላ መዘዝ አለ። ነገሩ በጣም ውስብስብ ነው።
በመጨረሻም የእነሱን ጉዳይ በደንብ እየተከታተልን፣ ሁሌም እንደምለው፣ ነጻ የምንወጣው በራሳችን ጡንቻ እንጅ በእነሱ ምርቃት ስላልሆነ ትግላችንን አጠንክረን እንቀጥል!
(በነገራችን ላይ ደመቀ ጠ/ሚኒስትር፣ ሽፈራው ምክትል ይሆናል በሚል የተለቀቀው ወሬ ህወሃት የህዝቡን ስሜት ( reaction) ለማወቅ ሆን ብሎ ያስለቀቀው እንደሆነ እጠረጥራለሁ።) (It’s to test the water)
Filed in: Amharic