>

ኦህዴድም  እንደ ቅንጅት (ሀይሌ ማሞ)

ዛሬ ባለንበት ሆነን ስናስበው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁሉ ነገሩ በህወሀት የሚዘወርበት ደረጃ ላይ አይደለም። ህወሀት የፖለቲካ መጫወቻዎቹን በሙሉ አጥቶ የቀረው የሀይል ካርዱ ብቻ ነው። የጠመንጃ አቅሙን ተጠቅሞ የፖለቲካውን መዘውር መልሶ እንደቀድሞው ለመቆጣጠር የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም። የህዝቡ የለውጥ ፍላጎትና ፍርሀትን ማሸነፍ የህወሀትን ግብአተመሬት አይቀሬ ቢያደርገውም ጊዜ መግዛትና ‘ዛሬን ካለፉ ለነገ መፍትሄ አይጠፋም’ የሚሏት ብሂል በህወሀት ዘንድ የጭንቅ ቀን መሹለኪያ ናት። በህዝቡ ትግል መበርታት የተበረታታው ኦህዴድ እንደቀድሞው አጋሰስ ሆኜ አልቀጥልም በሚል ከህዝብ ጎን ለመቆም የወሰነበት ቅፅበትም ለህወሀት ሳይታሰብ የፈነዳ ፈንጅ ነበር። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ወታደራዊ አገዛዝ ለማስፈንና ለመተግበር የተኬደበት ርቀትም ዋናው ምክንያት እግር ያወጣውን ኦህዴድ እግር ለመቁረጥ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ በኦሮሞው ወጣትና ተራማጅ ባለስልጣናት ላይ ያረፈውን ውርጅብኝ በማየት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወጥቶና ስራ ላይ ውሎም ቢሆን ህወሀት የነበረውን የሀይልና የፖለቲካ ቁጥጥር መልሶ ለማግኘት የቻለበት ሁኔታ የለም። በአስቸኳይ ጊዜው ወታደራዊ ሁኔታ ምናልባት ህወሀት ያገኘው ትልቁ ትርፍ በየመድረኩና ማህበራዊ መገናኛው ለምን በግድያ ልክ አናስገባም ብለው ዋይ ዋይ ለሚሉት ደጋፊዎቹ የደም ጎርፍ አሳይቶ ለጊዜውም ቢሆን እርካታን መስጠቱ ነው። ትናንት ዛሬ አይደለምና ሁሉን እንደወትሮው መቆጣጠር ግን የህልም እንጀራ ሆኗል። የህወሀት ግብ ላለፉት 27 ዓመታት የመጣንበትን አይነት የጥቂት ቡድኖች የበላይነት የነገሰበት ስርዓቱን ማስመለስና ከገዙት በላይ መግዛት ነው። የነለማና የነገዱ ፍላጎት ደግሞ የህወሀት ፈረስነት በቃን የሚል ነው። በብአዴን ውስጥ የብአዴንን ካባ የለበሱ ህወሀቶች እነገዱን ሊያፈናፍኗቸው አልቻሉም። በኦህዴድም ውስጥ እንደነ አባዱላ ገመዳ፣ ወርቅነህ ገበየሁ፣ ግርማ ብሩና የመሳሰሉት የነለማን የለውጥ ጉዞ አደናቅፈው ተጋላቢነታቸውን ማስቀጠል በዚህም የህወሀት ታማኝነታቸውን ማሳየት ዋና ግባቸው ነው። በህወሀቶች ዘንድ ለጊዜው የተለዩ ሊመቱ የሚገባቸው ሁለት  ኃይላት አሉ። እነሱም ኦህዴድ እንደ ድርጅትና ቀጥሎም የነፃነት ታጋዮች ናቸው።በወታደራዊ እዝ ነገሮችን ተቆጣጥሮ ቅድሚያ የሚሰጠው ተመቺ ኦህዴድ ይሆናል። በኦህዴድ በኩል ያለው ስጋት ተደምስሶ ካበቃም ትኩረቱ የህዝቡን ትግል ወደማክሸፍ ይሆናል። የኦህዴድን ቡድን ፀጥ ለማሰኘት ሲሆን ሲሆን የነለማን ቅስም መስበርና ለህወሀት እንዲገብሩ ማድረግ ያ ካልሆነም እነለማ ከጨዋታው የሚወጡበትን መንገድ መቀየስ ነው። ይህም ዛሬ ላይ እነለማ የበለጠ ጠንክረው ከህወሀት በላይ እንጂ በታች እንዳይደሉ ባገኙት ቀዳዳ ለህዝቡ ካላሳዩ እጣ ፈንታቸው ከጨዋታው መውጣት ይሆናል። ዛሬ ቅንጅት የሚባል የፖለቲካ ድርጅት ስለመኖሩ ብዙው የኢትዮጵያ ህዝብ አያውቅም። ምክንያቱም እውነተኛው ቅንጅት ከሽፎ ፎርጂዱ ቅንጅት በአየለ ጫመሶ እጅ አለ ስለተባለ የኢትዮጵያ ህዝብ መኖሩን ሊያውቀው አይችልም። ኦህዴድ ትናንት በህወሀት ተጠፍጥፎ የተፈጠረ ድርጅት ነው። ለዚያውም በምርኮኞች። ከ27 ዓመታት በኋላ እነለማ ከምርኮኛ ድርጅትነት ወደ ህዝብ ድርጅትነት ለመቀየር ሞክረዋል። ህወሀት ደግሞ በቁም እያለ የፈጠረው ድርጅት በራሱ ህያው ሆኖ እንዲንቀሳቀስና ፈጣሪውን ዝቅ ብሎ ከማመስገን ነፃ እንዲሆን አይሻም። በመሆኑም እጣ ፈንታው እንደቅንጅት ይሆናል። ኦህዴድ ከእነለማ ወጥቶ ለነአባዱላ ይሰጣል – ልክ ቅንጅት ለአየለ ጫሚሶ እንደተሰጠው።
አሁን እነለማ ትንፋሹን ሰብስቦ ጥሪያቸውን የሚጠባበቅ ብዙ ህዝብ አላቸው። የህዝብ ሀይል ደግሞ በጠመንጃ ሀይል አይሸነፍም። ይህን ትልቅ ሀይል ደግሞ በወቅቱ ካልተጠቀሙት ነገ ላይ አይኖርም። ህወሀት ኦህዴድን መቀጣጫ ማድረግ ከተሳካለት ቀጥሎ በትሩ እነገዱ ላይ ያርፋል። ከዚያም የለውጥ ፈላጊው ህዝብ ላይ ሁሉ። ለማንኛውም ጊዜን መጠቀም ትልቅ ብልሀት ነው። ቆይ ነገ፣ ቆይ ነገ ሲባል ብዙ ነገር ያልፋል። ዋናው ሀይል ግን ኦዴዳድም ብአዴንም አይደለም። ህዝብ ነው። እነለማንም ሆነ እነገዱን የህዝብ አካል ናቸው ያስባለን የህዝቡን ትግል ሲደግፉ ስላየን እንጂ ትግል ፈጣሪዎች ሆነው አይደለም። ስለዚህ ዋናው የተጀመረው ትግል እስከስርዓት ለውጥ መቀጠል አለበት።
ድል የህዝብ ነው!!
ኃ.ማ.
Filed in: Amharic