>

ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ (ያየህ ይራድ) 

ከአዲስ አበባ ጅማ በሚወስደው መንገድ 109 ኪ.ሜ. በምትገኘው በወሊሶ ከተማ በ1905 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ ዱኪ ጉልማና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወርቄ ኤልሞ ተወለዱ።
        በ1927 ዓ.ም. ፋሺስት ጣልያን ሀገራችንን ለሁለተኛ ጊዜ በወረረበት ወቅት የተጠበቀውን ጦርነት መነሻ በማድረግ በየክፍለ ሀገሩ የዘመተው የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት በጦር ሚኒስቴሩ ስር ሆኖ በ1928 ዓ.ም. ከማይጨው እስከ ተንቤና ሰቲት ድረስ ግጥሚያዎች አድርጎ ብዙ ጀግኖቻችን ተሰውተዋል።
በዚህ ጦርነት….
እነ ደጃዝማች በየነ(አባ ሰብስብ)
ቢተወድድ መኮንን ደምሰው
ደጃዝማች መሸሻ ወልዴንና ሌሎችም የጦር መሪዎች ስለ ሀገራቸው ሲሉ ህይወታቸው አልፏል። በዚያን ግጥሚያ ባላንባራስ (በኋላ ደጃዝማች) ገረሱ ዱኪም ይገኙ ነበር፤ እንዲያውም ቃፊር ሆነው በተንቤ የመጀመሪያውን ጥይት የተኮሱት እርሳቸው ነበሩ።
ከዚያም በጦርነቱ ፋሺስት ድል አድርጎ ሁሉም ወደ ትውልድ ሀገሩ ተመልሶ ለጠላት ገብረን አናድርም ካሉ ጀግኖች አርበኞቻችን አንዱ ደጃዝማች ገረሱ ነበሩ፤ ደጃዝማች ገረሱ አምስት ቆራጥ አርበኞችን አስከትለው በጠላት ላይ የመጀመርያ ድላቸውን ተቀዳጁ ከነዚህ አምስቱ አንዱ ልጅ ገነነ በዳኔ ናቸው። ደጃዝማች ገረሱ (አባ ቦራ) ፋሺስት ጣልያንን እሳቸው ባሉበት ከደቡብ ኦሮሚያ እስከ ኦሞ ወንዝ መቀመጫ አሳጡት ገበሬዎችን አሰባስበው በደፈጣ ውጊያ ቁም ስቅሉን አሳዩት። የእርሳቸው ጀግንነት ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ እስከ ጅማ ድረስ ብዙ ሺ ወጣቶችን አነሳስቶ ጫካ አስገባ። ጀግናው አርበኛ ገረሱ(አባ ቦራ) በዛ የሞት ሽረት ውጊያ ላይ ገና ለጦርነት ያልደረሰውን የ15 ዓመት ልጃቸውን ተፈራ ገረሱን በጦርነት አሳትፈዋል፤ ሀገር ከምንም ይቀድማል በማለት ብላቴናው ልጃቸውን ጀግንነት አስተምረውታል፤ ዘመናዊ ጦር የታጠቀውን ፋሺስት እያስበረገጉ ተስፋ አስቆረጡት። እኚህ ስመ ጥር ጀግና ይዋጉና ያዋጉ የነበረው በአዲስ አበባ ከሚገኘው ከዋናው የጦር ሰፈር 90 ኪ.ሜ. ርቀት በማይበልጥ ቦታ ላይ ነበር፤ ይህም የእኚህን አርበኛ ጥንካሬ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር።
የእኚህን ጀግና አርበኛ ታሪክ የሚዘክር ሙዚዬም ከወሊሶ 10 ኪ.ሜ. በሚገኘው ገብርኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ ይገኛል። በጀግንነታቸው የሰሯቸው ሥራዎችና ታላላቅ ሀገራዊ ሽልማቶችን የያዘ ነው።
ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!!!
ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic