>

"ቲም ለማ"ቀስ በቀስ በወያኔ አዝጋሚ ሞት ተፈርዶበት እያጣጣረ ነው  (ግርማ ካሳ)

የኢሕአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ነው የሚሉት። ግን ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውጭ ያሉ እንደ ስብሀት ነጋ፣ በረከት ስምኦንም  ያሉ ከበስተጀርባ ሆነው አገሪቷን እንደ ፈለጉ ሲያደርጉ የነበሩም በስብሰባው ተገኝተተዋል። በእነዚህ ሰዎች “ሽማግሌዎች” ተብለው ነው የገቡት። ግን ከነለማና ገዱ ጋር የሚከራከሩት እነርሱ ናቸው። እነርሱ ባይኖሩ ስብሰባው የነለማን አቋም ይዞ ይወጣ ነበር። በአጭሩ ይሄ ስብሰባ የኢሕአዴግ የስራ አስፈጻሚ ሕጋዊ ስብሰባ አይደለም። በስብሰባ መገነኘት የሌለባቸው ሰዎች የተገኙበት ሕገ ወጥ ስብሰባ ነው።
ስብሰባው ይኸው ካለፈው እሁድ ጀምሮ  እየተደረገ ነው። እነ ለማ በስብሰባ ተወጥረው፣ ሕወሃት ከስብሰባው ዉጭ በኮማንድ ፖስት አማካኝነት እነ ለማን የሚደገፉ የመካከለኛና ታችኛው የኦህዴድ አመራሮችን እየለቀመ በማሰር ላይ ነው።  በኦሮሚያ የፍትህ ቢሮ ሃላፊ ሆኑት አቶ ታዬ ደንዳእ ጨምሮ ወደ አራት የሚሆኑ የኦህዴድ አመራሮች ታስረዋል። ባለፈው የኢሕአዴግ ስብሰባ በተወሰነው መሰረት የተፈቱ እስረኞች ቦታ በመተካት ብዙ ወጣቶችና አክቲቪስቶች ወደ ወህኒ ወርደዋል። ጦማሪ ስዩም ተሾመ በአሁኑ ሰ’ዓት ይፈርሳል የተባለው ማእከላዊ ነው። ከአምቦ ብቻ በዚህ ሳምንት ውስጥ ከሶስት መቶ በላይ ዜጎች ታስረዋል። ብዙዎች እየተገደሉ ነው።
የነለማ ቡድን ስብሰባዉን ረግጦ እንዲወጣ አንዳንድ ወገኖች ይጠይቃሉ። ኦህዴድ ከብአዴን ጋር ሆኖ ስብሰባዉን ረግጦ መዉጣት ብቻ ሳይሆን ከኢሕአዴግ ከግንባሩ ቢወጣ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን በጣም የተሻለ አማራጭ ነው። ሁለቱ በፓርላማ አብላጫ ድምጽ ስላላቸው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ቢያንስ ለሽግግር ጊዜ የመንግስት ስልጣን ተረክበው መቀጠል ይችላሉ።
ሆኖም ግን ኦህዴድ ለብቻው ቢወጣ ፣ ሌሎቹ እንደ ኢሕአዴግ ይቀጥላሉ። ኦህዴድ ከፌዴራል መንግስት ዉጭ ከሆነ ደግሞ ሊያደረግ የሚችለው ነገር የተወሰነ ነው። Isolated  የሆነ ኦህዴድ በቀላሉ ይመታል። በመሆኑም ዕ ለማ ስሜታዊ ምክር ሰምተው ትልቅ ስህተት አይፈጽሙም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ትግል በስሜት አይደለም። ትግል በጥበብና በእውቀት ነው።
የኦሮሞ ነጻነትን የተራበ ወጣት – ቄሮ እንዲሁም በእዚሁ ድርጅት የተገኘው ወደር የሌለው ድጋፍ ያስደነገጠው የዲያስፖራው የኦሮሞ አክቲቪስቶች በተለያየ መልኩ እያራመዱ ባሉት ጥንቃቄ የጎደለው ትግል “ቲም ለማ”ቀስ በቀስ በወያኔ የዝምታ ሞት እየተራመደበት ይመስላል።ወደድንም ጠላንም እየተደረገ ያለው ከእዚህ የራቀ አይደለም!።
በኔ እይታ አሁንም ቁልፉ ያለው ብአዴን እጅ ውስጥ ነው። ብአዴን ላይ መሰራት አለበት ብለን ስንመክር፣ በብዴን ውስጥ ያሉ የለዉጥ ሃይሎችን፣ እነ ገዱን እንደገፍ ብለን ስንመከር ብዙዎች አልሰማ እያሉ ሲሞግቱን ነበር። “ለማ ፣ ለማ ” ይላሉ። ተገቢ ነው ያን ማለታቸው። ግን ያለ ገዱ ለማ ምንም ማድረግ አይችልም። እነ ገዱ በአንድ በኩል እነ በረከተን በውስጥ እየተጋሉ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚ ነን የሚሉትን ይታገላሉ።ለነርሱ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ እያዳከምናቸው ነው።
Filed in: Amharic