>

ለኢትዮጵያ ምን ይሻላል? እና የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት? (ተመስገን ደሳለኝ ክፍል 3)

ጠያቂ፡ ውይይት መፅሄት 
መላሽ፡ ተመስገን ደሳለኝ፡- 
.
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የመከራ ዘመን እንደ አንድ ነፃ ጋዜጠኛ ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦችን አነሳለሁ፡፡ የመጀመሪያው የመፍትሔ ሀሳብ በግንባሩ አባል ድርጅቶች ትከሻ ላይ የሚያድር ይሆናል ይኸም ኢሕአዴግ ራሱ የሚመራው የጊዜያዊ መንግስት ማቋቋም ይሆናል፡፡ እስከዛሬ ከተለመደው የማታለል፣ጊዜ የመግዣና ደራሽ እሳትን የማጥፊያ ፖለቲካዊ ስልቱ ወጥቶ በዋናነት ግንባሩ ከራሱ ጋር ታርቆና አምኖበት ከሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ተደራድሮ የጊዜያዊ መንግስት በማቋቋም አገሪቱንና ሥልጣኑን ለሕዝብ የሚያስረክብበት መንገድ ራሱ ኢሕአዴግ መፍጠር አለበት፡፡
የጊዜያዊ መንግስት ሲመሰረት በራሱ በኢሕአዴግ መሪነት መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ምክንያቱም ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ሥልጣን ላይ የነበረው ይኸው አገዛዝ መከላከያ ሰራዊቱን፣ የመረጃ ደህንነት ቢሮውንና የፌደራል ፖሊስ ብሎም በየደረጃው ያለውን የፀጥታ መዋቅር በራሱ ሰዎች ጠቅልሎ የያዘ በመሆኑ፤ከዚህም አልፎ እነዚህ የፀጥታና የደህንነት ቁልፍ መዋቅሮች የሚታወቁት የአገር ዳር ድንበርንና ሉዓላዊነትን ከመጠበቅና ከመከላከል ይልቅ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን በኃይል በማፈን ይታወቃሉ፡፡እነዚህን ኃይሎች የሚያዙት የሕውሓት /ኢሕአዴግ አመራሮች የጋዳፊ ዕጣ ሳይደርስባቸው የተዘጋውን የፖለቲካ በር እውነተኛ የጊዜያዊ መንግስት በማቋቋም እና የእርስ በርስ ዘውጋዊ መቃቃሮችን በይቅርታ ዘይት በማራስ ራሳቸውን የችግሩ መፍትሄ አካል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ይሄ በዋናነት የሚጠቅመውና የሚያድነው የግንባሩ የፖለቲካ መሐንዲሶችና የጥቅም ተጋሪ አባላቶቻቸውን ነው፡፡ለዚህ መፍትሄ ሐሳብ ጀርባን መስጠት የጋዳፊን እጣ በራስ ላይ የመጥራት ያህል አደጋ አለው፡፡ይኼ ለነገ የማይባል አማራጭ ነው፡፡
ሁለተኛው የመፍትሄ ሀሳብ በዋናነት የሕውሓትንና የጥቅም ትስስሩ ኃይል በይበልጥ የችግሩ መፍትሄ አካል እንዲሆን ማድረግን ይመለከታል፡፡ምንም በማያከራክር መልኩ በሥልጣንና በበዛ የጥቅም ተሸሚነት አገሪቱን ወርሮ የያዘው ኃይል ሕወሓት ነው፡፡ይኽ ኃይል ከነጥቅም ትስስሩ በየአቅጣጫው በዘረጋው የዘርፍ መዋቅር ኢትዮጵያን አብዝቶ አድምቷታል፡፡እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ሕወሓትንና የትግራይን ሕዝብ ለያይቼ የማይ ጋዜጠኛ መሆኔን እገልጻለሁ፡፡ ይሁንና ከሕወሓት አመራሮች ጋር በጋብቻም ሆነ በአካባቢያዊ ስሜት የጥቅም ትስስር በመፍጠር የማይገባውን ጥቅም ያገኘ በመሆኑ ከሥርዓቱ እኩል ተጠያቂ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡የፖለቲካ ስልጣንን መነሻ በማድረግ በአንድ ጀንበር ሚሊየነር እየተሆነባት ባለችው ኢትዮጵያዊ በዘረፋ በተገኘው ገንዘብ በአንድ ጀንበር ሕንጻ እንደ ዛፍ ማብቀል የኩራት ምንጭ ሲሆን ታይቷል፡፡በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ባለሀብቶች ነበሩ፡፡ የብዙዎቹ የሃብት ምንጭ በዓመታት ድካምና ጥረት የተገኘ ስለመሆኑ ምስክር የሚሰጡት ያልተማሩ እናትና አባቶቻችን ናቸው፡፡ዛሬ ላይ እየታየ ያለው የሀብት ክምችት ግን የፖለቲካ ስልጣንን ፍፁም መነሻ ያደረገ የጥቅመኝነት ትስስር ውጤት ነው፡፡ስለእነዚህ ባለሃብቶች ምስክርነት የሚሰጥ ወገን ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይደለም፡፡ይኼ ሁሉ ቅጥ-ያጣ ዘረፋና ወንጀል በተፈፀመበት አገር ዋናው ተጠያቂና ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው አካል ሕወሓት በመሆኑ እርሱም ሆነ ያልተገባ ጥቅም ተጋሪዎች ከሕዝብ ሰይፍ ሊድኑ የሚችሉት ራሳቸውን የመፍትሔው አካል ማድረግ ሲችሉ ነው፡፡
በታሪካዊው የፈረንሳይ አብዮት ጊዜ አንገት የሚቀላ ማሽን (guillotine) መሠራቱን ታሪክ ያስታውሰናል፡፡እኛም አገር ሕዝቡ አንገት የሚቀላ ጊሎቲን ማሽን እንዳያመጣ ከተፈለገ ሕውሓት በሙሉ የኃላፊነት ስሜት የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና አጋር ፓርቲዎችን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በማጣመር የጊዜያዊ መንግስቱን ማቋቋም ግድ ይለዋል፡፡ ይህ አካሄድ “የለም አይሆንም ከርዕዮተ-ዓላማችንና ከድርጅታዊ መርሆዎቻችን ጋር ይቃረናል” የሚሉ ከሆነ ተከታዩና ብቸኛው አማራጭ የባለአደራ መንግስት እንዲመሰረት አረንጓዴ መብራት ማሳየት ይገባል፡፡
የባለአደራ መንግስት ሲቋቋም፤የሚያቋቁሙት ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን የአገር ሽማግሌዎች (ምናልባትም ዘውጋዊ ተወካዮች)፤የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (የአካዳሚው ክንፍ)፣ተወካዮች የሙያ ማህበራት ተወካዮችን፤የንግዱ ማህበረሰብ ወኪሎችን፣ የሴቶችና የወጣቶች ወኪሎች፣ ወዘተ… ዘርፈ ብዙ የልሂቃን ወኪሎችን ባካተተ መልኩ እንዲቋቋም በማድረግ የኢትዮጵያን የመከራ ዘመን ማሳጠር ይቻላል፡፡ሁለቱን የመፍትሄ አማራጮች እንደአስፈላጊነቱ ተመጋጋቢነታቸውን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን ነፃነት በአዲስ ስርዓት ማዋለድ ይቻላል፡፡
የዓለም ታሪክ እንደሚነግረን ሕዝብ ተሸንፎ አያውቅም፡፡ የተሸነፈ መንግስት እንጂ ሕዝብ በዓለም የትግል ታሪክ አልተመዘገበም፡፡የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መጠኑ በበዛ የደም ጎርፍም ቢሆን ለውጡ አይቀሬ ነው፡፡ይኽም ሆኖ ከሩዋንዳ ታሪክ መማር ብልህነት ነው፡፡ከዓለም ተሞክሮ አኳያ ስናው ለተሸለች አገር ግንባታና ለነገ ተስፋ ሲባል በአገዛዙ የብረት መዳፍ የተጨፈለቁ፤ግፍና በደል የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ከባህላችን አኳያ ስልጣን በሰላም እስካስረከቡ ድረስ አምባገነኖቹን ‹ይቅር› ሊሏቸው ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡እዚህ ላይ በአገሪቱ ከተፈፀመው ግፍና በደል አኳያ የእኔ እስርና በደል ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ግፉአኑ ‹ይቅር› ሊሏቸው የሚችሉ ግን በህዝብ ሀይል ‹እጅ ወደ ላይ› ከተባሉ በኋላ አይደለም፡፡‹እጅ ወደ ላይ› ሳይባሉ አሁን ያለውን ግድያና አፈና አቁመው የሽግግር መግስትም ሆነ የባለ አደራ መንግስት ማቋቋም ሲችሉ ነው፡፡ከዚህ ውጪ የሚመጣ መፍትሄ መድረሻው የፈረንሳይ አብዮት የሚያስታውሰን የአንገት መቅያ ማሽን ጊሎቲን ወደመጨበጥ ያዘመመ ነው፡፡በአብዮት ጊዜ የፍርድ ቤት ደጆች ዝግ ናቸው፡፡ሕግና ፍርድ በሕዝብ መዳፍ ስር ይወድቃል፡፡የመንግስት ፍትሃዊ ሕግ ሲዝል ብሎም የህግ የበላይነት ሚዛኑን ሲስት የሕዝብ ህግና ፍርድ አደባባዩን ይቆጣጠራል፡፡የሕዝብ ሕግና ፍርድ ደግሞ የጋዳፊን መጨረሻ ያስታውሰናል፡፡ከዚህ አይነት መከራ ራሳቸውንና ‹እንወክለዋለን› የሚሉት ሕዝብ ከአንዣበበበት አደጋ ለመጠበቅ እውነተኛ የኃላፊነት ስሜት ከተሰማቸው የጊዜያዊ መንግስት አልያም የቀለላቸውን የባለአደራ መንግስት እንዲቋቋም አገራዊ ጥሪ ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡
.
የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት?
.
እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የሚሻገር ጊዜ የአደባባይ ምሁራንን አላፈራችም፡፡ከያ ትውልድ የተሻገሩትም ቢሆን በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ጋናዊው ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቲ ምሁራንን ‹ቅምጥ ምሁራን› እና የአደባባይ ምሁራን በሚል በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ በፕሮፌሰሩ አተያይ የእኛ ሀገር ቅምጥ ምሁራን ከአገዛዙ ጋር በመሞዳሞድ ካድሬ-ለበስ “ምሁራዊ” ትንታኔ ሲሰጡ የኖሩ ናቸውና እነርሱ የለውጡ እንቅፋት ከመሆን ተሸግረው ረብ ያለው ሚና የሚጫወቱ አይመስልም፡፡ “ቅምጥ ምሁራኑ” ከለውጡ አደናቃፊነት ቢታቀቡ መልካም ነው፡፡ አብረው ሲጨቁኑና ሲበድሉን የኖሩት ቅምጥ ምሁራኑ በመጨረሻው ሰዓት ህዝብ ከማደናገር ሊታቀቡ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል በየከፍተኛው ትምህርት ተቋማት አንገታቸውን ደፍተው ያሉ ፍዝ-ምሁራን የሕዝቡን የለውጥ ስሜት ወደ አደባባይ ወጥተው ቢጋሩት አገራዊ ትንሳኤያችን ቅርብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ከበቁት ሁሉ የላቁ በእግራቸው ኮቴ ልክ መርገጥ የማይቻለን የአደባባይ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አሉንና እዚህም እዚያም የተበታተነውን የኃይል ድምፅ ወደአማካይ ስፍራ እንደሚያመጡት ይጠበቃል፡፡

Filed in: Amharic