>

የኢህአዴግ ምናልባት ብቸኛ የተስፋ ገመድ በለማ መገርሳ የሚመራው አዲሱ ኦህዴድ ነው! (አበጋዝ ወንድሙ)

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ጠንከር እያለ ሲሄድ ሀገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ ገብታለች የሚለው አባባል ተደጋግሞ ቢነገርም፣ሃገራዊ ቀውሱ ገኖ እውነተኛ መስቀለኛ መንገድ የገባንበት ወቅት አሁን
ይመስለኛል።
ኢህአዴግን አስመልክቶ የሚካሄደው የህዝብ ተቃውሞ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም ፣አሁን ባለው ጥንካሬና ስፋት ላልተቋረጠ አምስት ዓመት የተካሄደበት አጋጣሚ ከዚህ ቀደም አልነበረም።
በነዚህ አምስት አመታት የተካሄደው ሕዝባዊ ትግልም የአገዛዝ ስርዓቱ ላይ ትልቅ ጫና በማሳረፍ፣ በገዥው ፓርቲ ውስጥ መከፋፈልን በመፍጠር ድርጅቱን ከስሩ ያናጋበት ወቅት ላይ እንገኛለን። በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ እንደሚያመላክተው ገዢው ቡድን መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር
ታሪኩና ፍጥረቱ እንኳን አይፈቅድለትም ቢባል፣ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ሲል ለመተባበር ፈቃደኛ
ካልሆነ ፣ የፖለቲካ ቀውሱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ለመገመት የሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ልንገባም
እንችላለን።
ይሄንን አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ደግሞ ባሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ ያለው ትንሹ የተስፋ ገመድ ፣የጠቅላይ ምኒስትር
ምርጫን አስመልክቶ፣ የህዝብን ብሶት ለመስማትና ውሱንም ቢሆኑ መልስ ለመስጠት የሚሞክረው በለማ
መገርሳ የሚመራው የኦህዴድ ቡድን ነው የሚል እምነት አለኝ ።

በቅርቡ ሃይለማርያም ደሳለኝ 'በድንገትና በገዛ ፍቃዱ ከጠቅላይ ሚንስትርነቱና የኢህአዴግ ሊቀ መንበርነቱ መልቀቁን ይፋ ካደረገ በዃላ ቀጣይ ጠቅላይ ሚንስቴር ማን ሊሆን ይችላል የሚለው እስካሁን ድረስ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው። የመለስ ሞት በታወጀ በማግስቱ ሃይለማርያምን ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚንስቴር (በፓርላማው እስኪጸድቅ ) ብሎ የሾመ ኢህአዴግ፣ ሃይለማርያምን ለመተካት ግን ሳምንት፣ አስራምስት ቀን እያለ ስብሰባዎችን በማስተላለፍ እስካሁን በዝግመት እየተጓዘ ይገኛል ።
ኢህአዴግ መቼ የሚለውን በግልጽ ባያሳውቅም ፣መጭው የድርጅቱ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠቅላይ ምኒስትር
ምርጫ በደመቀ መኮንን፣ሽፈራው ሽጉጤና አብይ መሀመድ ሊሆን አንደሚችል ያሳወቀ ቢመስልም ፣ ከሶስቱ
ሰዎች ማን ይሁን በሚለው ላይ አስካሁን ስምምነት ላይ ሊደርስ የቻለ አይመስልም።
አንዳንዶች ምናልባት ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት፣ አባዱላ እንዳደረገው (ወይንም አንዳስደረጉት!) የስራ
መልቀቂያውን ስቦ ቀጣዩን ሁለት ዓመት እንደምንም እንዲጨርስ ኃይለማርያምን ልያግባቡት ይችላሉ የሚል
ግምት ቢኖርም፣ ምርጫውን ያለቅጥ ማዘግየትም ሆነ ይሄን እርምጃ መውሰድ የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ
ያባብስ እንደሆነ እንጂ የሚያረግበው አይሆንም።
ቀጣይ ጠቅላይ ሚንስቴር ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ኢህአዴግ ካጫቸው ውስጥ በኔ ግምት ደመቀ መኮንንና  ሽፈራው ሽጉጤ በስከዛሬው የፖለቲካ ተሳትፏቸውና አጠቃላይ ዝግጅታቸው ተስፋ የሚያጭሩ ሆኖ አይሰማኝም።
ደመቀ ላለፉት ስምንት አመታት የብአዴን ሊቀመንበር፣ ላለፉት ስድስት አመታት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ
ሚንስትር ሆኖ የሚያገለግል ፣ ይሄ ነው የሚባል ሃገራዊ ራአይ የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ እወክለዋለሁ
የሚለው የአማራ ህዝብ ላይ በበርካታ አካባቢዎች የደረሰውን መጠነ ሰፊ ግድያና መፈናቀል ለማስቆም
ያልቻለ ፣ጥረትም ያላደረገ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን እንኳን በሚገባው ደረጃ ለማውገዝ ወኔ ያልነበረው ደካማ
በመሆኑ ለስራው የሚመጥን አይሆንም።

ሽፈራው ሽጉጤ ለሰባት አመታት የደቡብ ክልል ፕሬዘዳንት ሆኖ ያገለገለና፣ በሱ ያስተዳደር ዘመን በብዙ ሺህ
የሚቆጠሩ የአማራ ብሄረሰብ አባላት በግፍ ሲፈናቀሉ፣ ከማውገዝና ከማስቆም ይልቅ፣ 'አንዳንድ ሚድያዎች ያጋነኑት በሚል ድርጊቱን ለማኮሰስ የጣረ ግለሰብ ነው።
እስካሁን ተግባራዊ ባይሆንም ሃይለማርያም ደሳለኝ ፓርላማ ቀርቦ በማፈናቀሉ ድርጊት የተሳተፉ የአስተዳደር
አካላትም ሕግ ፊት ቀርበው እንደሚጠየቁ የተናገረው የሚመለከተው ግለሰብም ሊሆን የሚችል እንጂ፣ የሀገር
ጠቅላይ ምኒስትር ለመሆን የሚያስችል ብቃት የለውም። በአጠቃላይ ሲታይ ድርጅቱ ለጠቅላይ ሚንስተርኔት
የሚመጥን፣ በመጠኑም ቢሆን የህዝብ ይሁንታ ሊያገኝ የሚችል ሰው ድርቅ የገጠመው በመሆኑ ካቀረባቸው
አጩዎች የተሻለ የሚመስለው አብይ አህመድ ነው።

በኔ አምነት ኢህአዴግ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስቴር ማን ይሁን የሚለው ላይ የሚያሳየው ዝግመት ትልቁ
ምክንያት፣ የኦህዴድ አብይን አጩ አድርጎ ማቅረብና ፣ እስካሁን ኢህአዴግን በበላይነት ሲያሽከረክር የነበረው
ህወሃት ደግሞ ፣ የአብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚንስቴር መሆን ይሄንን የበላይነት ያሳጣናል የሚል
ፍርሃት ነው። የዚህ ፍርሃት ምንጩ ደግሞ በኦሮሚያ የሚካሄደውን ያልተቋረጠ የህዝብ ትግል  ከትሎ፣በኦህዴድ ውስጥ ባጠቃላይና በአዲሱ አመራር በተለይ የተፈጠረው መነቃቃትና በራስ መተማመን፣ የህወሃትን የበላይነት የሚሸከምበት ትከሻ እንደሌለው የሚያሳይ ፍንጭ ማሳየቱ ይመስለኛል።
ህወሃትም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ያለው ጤነኛ አማራጭ ከእንግዲህ ወዲህ ኢህአዴግን በበላይነት የማሽከርከሩ
ዘመን ዳግም ላይመለስ እንዳከተመ በመገንዘብ በቁመቱ ልክ ለመንቀሳቀስ መሞከር እንጅ ወደዃላ መመልከት ሊሆን አይችልም።
ይሄ የህወሃት ፍራቻ ፣የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚንስቴር እጩ የሆነ ተፎካካሪን አስመልክቶ፣እስከ ዛሬ
ድረስ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ (አብዛኛውን ጊዜ የሌለ ተክለ ሰውነት ለመፍጠር ሲጥሩ ስለሚታወቅ!)
ከከፍተኛ አመራር አስከ ቅጥረኛ ካድሬዎች አብይ አህመድን የማጥላላት ዘመቻ እንዲከፈትበት አድርጓል። ይሄ
አስፈላጊም ጠቃሚም አይደለም።
አሁን ሀገራችንን ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣትና የተረጋጋ አካሄድ እንዲኖር ፣ የህዝብንም እሮሮ በማዳመጥ
በሀገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ከተደራጁም ሆነ ካልተደራጁ፣ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር
በመወያየት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ መደላድል እንዲፈጠር በትጋት ለመስራት ፍቃደኛ ነን የሚል ውሳኔ ላይ
ደርሰናል በሚል ለሕዝብ ቃሉን የሰጠው ኦህዴድ አጩ አድርጎ ያቀረበውን ፣ አብይ አህመድ ለስፍራው
ስለሚመጥን ፣ ህወሃት ተቃውሞውን ወደጎን በመተው ሊተባበር ይገባል።
ይሄ ሳይሆን ቢቀር ግን በኢህአዴግ ላይ በአጠቃላይ በህወሃት ላይ በተለይ እምነቱን ሙሉ በሙሉ ያጣውን ህዝብ ተስፋ አስቆርጦ የሚወሰደው እርምጃና፣ እሱን ተከትሎ የሚመጣው ጠንቅ ሀገራችንን ወደ አስከፊ ጎዳና ሊከት ስለሚችል፣ከእስከዛሬው የጥፋት መንገድ ወጣ ብለው የተሻለውን መንገድ እንደሚመርጡ ተስፋ አደርጋለሁ።

Filed in: Amharic