>

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ኦህዴድ (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ናቸው። የቀድሞው አምባሳደር ያማማቶ ስለለውጥ ያወራሉ። የትግራይ ገዢ ቡድን የአሜሪካን ባለስልጣናት እግራቸው የአዲስ አበባን መሬት መርገጡን ተከትሎ በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት የቀለም አብዮት ላይ አካኪ ዘራፍ እያለ ነው። ለመጪው ዕሁድ የተጠራው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምክርቤት ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እስከመኖሩም የዘነጋው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራዩን አገዛዝ አረፋ እያስደፈቀ ማንደፋደፉን ቀጥሎበታል። ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም። ይሮጣል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድብን ካለ ድብታ፡ ድንዛዜና ሰመመን ወጥቶ በብርሃን ፍጥነት ወደ ለውጥ እየገሰገሰ ነው። ጥያቄው ምን ዓይነት ለውጥ ይሆናል የሚለው ነው። ወደተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ልግባ።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጥቅል የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የታወጀ የሞት አዋጅ ቢሆንም በተናጠል ያነጣጠረው ኦህዴድ ላይ ነው። መቀሌ ላይ ለሁለት ወራት ተጎልተው መርዝ ሲቀምሙ የከረሙት የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት መርዛቸውን ሸክፈው፡ ጓዛቸውን ጠቅለለው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የጠበቃቸው የሙክታር ዓይነቱ ተላላኪው ኦህዴድ አለነበረም። በአንድ ቀጭን ትዕዛዝ በስልክ መሪውን የሚቀይሩት የአባዱላ ገመዳ አደርባዩ ኦህዴድም አልነበረም። ሰለሞን ጢሞ የተሰኘው የትግራይ ገዢ ቡድን አመራር እንደፈለገው የሚያሽከረክረው የኩማ ደምቅሳ ኦህዴድም አይደለም። ይልቅስ በባለራዕዮቹ፡ በሀገራዊ መልዕክታቸው የሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ልብናቀልብ የገዙት፡ በሚሊዮን ወጣቶች ብረት ዘብ የቆሙት፡ አሽከርነትን የሚጠየፉ፡ ሎሌነት ያልፈጠረባቸው፡ ሰው መሆን ክቡር ነው የሚል መርህ ከነፍሳቸው ጋር የተጋመደባቸው መሪዎች እጅ የሚገኘው አዲሱ ኦህዴድ እንጂ።
የለማ- አብይ ኦህዴድ ለትግራይ መሪዎች ያልተጠበቀ ዱብእዳ ሆነባቸው። እንደፈረስ ሊጋልቡት የሚችሉት አይደለም። ከዕውቀት ነጻ በሆነ አእምሮ ጠፍጥፈው የሰሩት፡ ምርኮኞችን ሰብስበው እስትንፍስ ዘርተው ያቆሙት ኦህዴድ እነለማ እጅ ሲገባ እንደኤርታሌ ፍም እሳት የማይጨበጥ የማይነካ ሆነባቸው። ትላንት ዛሬ አይደለም። ጊዜ ተቀይሯል። ዘመን ተለውጧል። የትግራይ ገዢ ቡድን ትዕቢት ተንፍሷል። ኦህዴድ እግር አውጥቷል። ጥርስ አብቅሏል። እጁን ይዘው መንገድ የሚመሩት፡ እንደአሻንጉሊት የሚጫወቱበት ዘመን አልፏል።
ምንግዜም የበላይ ሆኖ መቀጠል አለበለዚያም ሞት የሆነባቸው እነስብሃት ነጋ የመጣባቸውን አደጋ የሚሻገሩበት አንዳች ተአምር ማግኘት አለባቸው። በስብሰባ ሞከሩት። አልሆነም። ግምገማ ተቀመጡበት። የሚቻል አይደለም። በደህንነት፡ በጸጥታ ሃይሎች ወከባና ማስፈራራት ሁኔታውን አዩት። አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ….ሲሆንባቸው ተዉት። የቀራቸው አንድ ዕድል ብቻ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ። በዚህ ኦህዴድ ማንበርከክ ካልቻሉ የአጼ ዮሀንስን ዘውድ ለመቶ ዓመታት የማንገስ ህልማቸው አፈር ከድሜ በልቶ እነሱም ከነቅሌት ታሪካቸው መወገዳቸው አይቀርም። እናም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሞት ሽረት ጉዳይ ነበር። ህልውናቸውን የሚያስቀጥል የመጨረሻ ዕድል ነው።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በግልጽ ኦህዴድ ላይ የተሰነዘረ ሰይፍ ነው። መከላከያ ሰራዊት ያለእኛ ፍቃድ በክልለችን ምግባት አይችልም የሚል ኮስተር ያለ አቋም የያዙትን እነለማን በአስቸኳይ አዋጅ ስም ለማንበርከክ የትግራይ ገዢ ቡድን አሰፍስፏል። ወገኖቻችን ላይ አንተኩስም የሚል አቋም የያዙትን የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶችን ትጥቅ ለማስፈታት ቋምጧል። የገበሬውን መሬት አትፈነጩበትም የሚል ጠንከር ያለ ውሳኔ ያስተላለፈውን ኦህዴድን መልሶ በቁጥጥር ስር ለማድረግ እነስብሃት ቸኩለዋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስት የተለጠጠ ስልጣን ተሰጥቶት እንዲዋቀር የተፈለገውም ለዚሁ ነው። ከጸጥታና ሰላም ባሽገር የመሬት ጉዳይንም እንዲመራ አድርገው ያዋቀሩት ያለምክንያት አይደለም። የኦህዴድን አመራርና የጸጥታ ሃይል በአስቸኳይ አዋጁ በመጠርነፍ፡ አፉ ተሎጉሞ፡ እጅና እግሩ ተቀፍድዶ፡ በሂደትም ተዳክሞ ኮስምኖ እንዲቀር፡ በመጨረሻም የተነቃነቀውን ዙፋን በማረጋጋት በአዲስ ጉልበት ረግጦ ለመግዛት እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
አስቸኳይ አዋጁ በፓርላማው ህግና አሰራር ውድቅ ሆኗል። ድምጽ ለማግኘት በየሀገራቱ የተላኩትን አምባሳደሮች ሳይቀር ያስመጡት፡ ተሰባስበው ገብተው አዋጁን ለማጸደቅ ይሉኝታ ባጣ መልኩ የተረባረቡት የትግራይ ገዢ ቡድን ባለስልጣናት ቁጥር አልሞላ ሲላቸው እንደፈረስ በሚጋልቡት ታማኝ አገልጋያቸው አባዱላ አማካኘነት ሰርዘውና ደልዘው በጉልበት ጸድቋል ያሉበትና ዓለም የታዘባቸው ሂደት የሚያሳየው አስቸኳይ አዋጁ ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ነው። አቶ አባዱላና ጥቂት የኦህዴድ ሰዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ የታወጀውን ሞት እጅና እግራቸውን አውጥተው መደገፋቸው በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ የሚቀመጥ አሳፋሪ ተግባር ነው።
ሆነም ቀረም፡ ተደልዞና ተሰርዞ የጸደቀው አዋጅ ኦሮሚያ ክልል ላይ አነጣጥሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል። እንድተባለውም ኦህዴድን የማዳከም ስራ በስፋት እየተካሄደ ነው። እነለማ መግለጫ እንዳይሰጡ በአዋጁ ተቀፍድደው ተይዘዋል። ኮማንድ ፖስቱ የኦሮሚያን ፖሊሶች ትጥቅ ካላስፈታሁ አስቸኳይ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ አልችልም የሚል ሪፖርት አቅርቧል። ከወዲሁ አምስት የኦህዴድ ባለስልጣናት በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ውለዋል። የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲራዘም ተደርጓል። የትግራዩ ገዢ ቡድን አባዱላ በሚባል አገልጋዩና በሌሎች የኦሮሞን ህዝብ አሳልፈው ለአራጅ በሰጡ የኦህዴድ አባላት እየታገዝ የእነለማን ኦህዴድ በማጥቃት ላይ ተጠምዷል። ምንም እንኳን የህዝብ ድጋፍ በአስተማማኝ ደረጃ ከጀርባ ያላቸው እነለማ ለጊዜው በጀመሩት ፍጥነት መጓዝ ባይችሉም በዚህን ቀውጢ ጊዜ የህዝባቸውን አደራ የሚዘነጉት አልሆነም። እንደሰማሁት ኦህዴድ ኢህአዴግ ከሚባለው የህወሀት ዣንጥላ ለመውጣት እየመከረ ነው። መውጣቱ ብዙ ፖለቲካዊ ዋጋ ቢያስከፍለውም እንደአንድ አማራጭ በመፈተሽ ላይ ነው።
የትግራዩ ገዢ ቡድን በጭፍን እየሮጠ ነው። የስልጣን ስግብግብነት ልቦናውን ደፍኖት በጥፋት ጎዳና ላይ እየሸመጠጠ ነው። ኦህዴድን ለማዳከም የጀመረውን እንቅስቃሴ በሚቀጥሉት ሳምንታት በስፋት እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል። እንግዲህ የህዝብ ጉልበት የሚፈተሸውም እዚህ ላይ ነው። የትግራዩን ገዢ ቡድን ከመሬት ቀብሮ፡ ከነጉድፉ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ መዝግቦ ለሁሉም የሆነችዋን ኢትዮጵያን በነጻነት ደሴት ላይ ለማስቀመጥ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንጊዜውም በላይ አንድ መሆን ያለበት ጊዜ ላይ ነን። እነለማን ሊሰለቅጥ ጥርሱን እያፏጨ ያለውን የትግራይ ገዢ ቡድን ጥርሱን አወላልቆ ከታሪክ ገጽ ላይ የማጥፋት ሃላፊነቱን ከዳር ማድረስ ምርጫ የሌለው እርምጃ ነው። ለጥገናዊ ለውጥ እየተሯሯጠ ያለውን አገዛዝ እስከወዲያኛው የማሰናበቱን የተጀመረ ስራ መጨረስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
Filed in: Amharic