>

አንዷለም አራጌ፤ ስለ እስር ቤት ቆይታው ይናገራል (አለማየሁ አንበሴ)

• ሃሳብ በሃሳብ እንዲሸነፍ እንጂ ሃሳብ በኃይል እንዲመታ መደረግ የለበትም
    • አገዛዙ፣ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር መመካከር አለበት
    • ”እኔ ብቻ ልምራ” ማለት መታከምና መፈወስ ያለበት ደዌ ነው
    • *የፖለቲካ ትግል ራስን ማዳን ሳይሆን ዓላማህን ማዳን ነው

ሁለት ጊዜ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት የአንድነት ፓርቲ የቀድሞ አመራር አቶ አንዷለም አራጌ፤በእስር ቤት ቆይታው፣በሀገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

ለእስር የተዳረግህበት አጋጣሚ እንዴት ነበር? የእስር ቤት ቆይታህስ ምን ይመስላል?
የታሰርኩበት አጋጣሚ የ3 ዓመቱ ልጄ ሩህ፣ ሶስት ዓመቱ  አካባቢ ነበር፡፡ ኬጂ የገባበት የመጀመሪያ ቀን ነበር፡፡ ጠዋት ከባለቤቴ ጋር አድርሰነው፣ 9 ሰዓት ላይ ከትምህርት ቤት ልንቀበለው ቀጠሮ ይዘን ተለያየን። በዚህ መሃል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በ”አንድነት” ፓርቲ ላይ ያቀረበው አንድ የውይይት መነሻ ጥናት (ፕረዘንቴሽን) ነበር፡፡ ጥናቱን በሲዲ አሳትመን ለህዝብ ልናደርስ፣ ከእስክንድር ጋር ሌሎች ስራውን የሚሰሩ ሰዎችን ለማገናኘት ቀጠሮ ነበረኝ፡፡ እንደማስታውሰው፣ የእስክንድር ልጅም ትምህርት ቤት የጀመረበት ዕለት ነበር፡፡ እሱም ከተገናኘን በኋላ በመሃል ልጁን ከትምህርት ቤት ሊያመጣ ይሄድ ነበር፡፡ በመሃል የቀጠሮአችንን ጉዳይ ለመከወን ስንሯሯጥ፣ እኔና እስክንድር መኪናችንን አቁመን ባለበት ሰዓት፣ የመኪናችን መስኮት ተንኳኳ፣ ቦታው ወደ “አንድነት” ቢሮ መግቢያ አካባቢ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ሁለታችንም የታሰርነው፡፡
ከዚያ በኋላ ለፍተሻ ወደ ቤት ስወሰድ፣ ከትምህርት ቤት ልወስደው ቀጠሮ የያዝኩለት ልጄ፣ እቤት ደርሶ በመጋረጃ ተከልሎ ይመለከተኝ ነበር፡፡ የፖሊሶችን ግርግር ሲያይ ተደናግጦ ነበር፡፡ ትንሹ ልጄ ደግሞ ገና ከተወለደ 10 ወሩ ሲሆን እሱም ሶፋ ላይ ተኝቶ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ከልጆቼና ከቤቴ የተለየሁት፡፡
በእስር ቤት በነበረኝ ቆይታ ብዙ ነገር ነው የታዘብኩት። በምርመራ ወቅት ማሰቃየት ይፈፀማል። ለምሳሌ እነ ናትናኤል መኮንንና አበበ ቀስቶ (ክንፈሚካኤል ደበበ) በእኔ ላይ እንዲመሰክሩ ለማድረግ፣ ድብደባ ተፈሞባቸዋል፡፡ ጆሮአቸው ተጎድቷል፡፡ በውሸት መስክሩ ተብለው፣ “በማናውቀው ባላየነው ጉዳይ አንመሰክርም” በማለታቸው የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ነው የወጡት። ሌሎችም ተመሳሳይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ይፈጸሙ ነበር፡፡ ሰው ያውቀዋል ሚዲያ ይከታተለዋል ብለው የገመቱትን ሰው ደግሞ ከአካላዊ ጥቃት ይልቅ ስነ ልቦናዊ ጥቃት ነው የሚፈፅሙበት፡፡
ወደ ማረሚያ ቤቱ ስንመጣ፣ በመተቸት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ስሙ ነው ማረሚያ እንጂ ግብሩ ሌላ ነው፡፡ ይሄ የሀገሬ ተቋም እንደመሆኑ እኔ እንደታዘብኩት እንዲሆን አይደለም የምፈልገው። እውነታው ግን እስረኞች  የሚታረሙበት ሳይሆን በጅምላ የሚኖሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እስረኛን በፖለቲካ ዓይን ማየት፣ በገለልተኝነት ያለማገልገል ሁኔታ በስፋት ይታያል። በተለይ እኛን እንደ አሸባሪ ነበር የሚያዩን። ለሌሎችም “ተጠንቀቁ፤ ይሄ ሽብርተኛ ነው” ይላሉ፡፡  እነሱ ለእኔ ወንድሞቼ ናቸው፤ እንደዚያ ባያደርጉ ጥሩ ነበር፡፡ ነፃ ሆነው ስራቸውን ብቻ ቢሰሩ ጥሩ ነበር፤ ግን ልክ እንደ ጠላት እየቆጠሩን እኛን በስነ ልቦና ለመስበርና ቤተሰብን ለማሰቃየት የማያደርጉት ጥረት አልነበረም፡፡ ይሄን ስል ግን ቀና ሰዎች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ ቀና የሥራ ኃላፊዎችም አሉ፡፡
ሰውን አስሮ፣ እያሰቃዩ መንግስትን እንዲደግፍ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ አንዳንዴ እስር ቤት ከመግባትህ በፊት ሃገርህን የምትወድ ሰው ሆነህ፣ ስትወጣ ጠልተህ ልትወጣ ትችላለህ፡፡ በሀገርህ ላይ ያለህ አቋም ከሚፈተንባቸው ቦታዎች አንዱ እስር ቤት ነው። ከእስረኛ አያያዙ፣ ከአመጋገቡ ከጤና አኳያ ያለው ሁኔታ፣ በሀገርህ ተስፋ እንድትቆርጥ የሚያደርግ ነው፡፡ እኔ እንኳ ከልጅነቴ ጀምሮ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” እያልኩ ያደግሁት ሰውዬ፣ በሀገሬ ላይ ባለኝ አቋም የተፈተንኩበት ቦታ ነው፤ እስር ቤቱ፡፡ የሚደርስብህ በደል ሲደጋገም በአገዛዙና በኢትዮጵያ መሃል ያለውን ልዩነት ሁሉ እንድትረሳ ያደርግሃል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሄር ረድቶኝ ፈተናውን ተወጥቼዋለሁ፡፡
በማረሚያ ቤት ያሉ የሥራ ኃላፊዎች መሆን የሚገባቸው ጡንቸኛ  ወታደሮች ሳይሆን የሰውን ልጅ በስነ ልቦና ማከም፣ በስነ ምግባር መቅረፅ የሚችሉ መሆን ይገባቸው ነበር፡፡ ይሄ እንደ ሀገር ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ ማረሚያ ቤቱ፣ ስሙና  ግብሩ የተለያየ ነው፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ ወቅት ጊዜህን እንዴት ነበር የምታሳልፈው?
ጠዋት 11፡30 እነሳለሁ፡፡ ፀሎት አደርጋለሁ። በር እስኪከፈት ድረስ ሰውነቴን አፍታታለሁ፡፡ 12 ሰዓት በር ሲከፈት እወጣለሁ፣ እስከ 2 ሰዓት ድረስ ስፖርት እሰራለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ተጣጥቤ ያገኘሁትን ቁርስ በልቼ ወደ መጽሐፍ ንባብ እገባለሁ፡፡ ኢቢሲ እና አዲስ አበባ ቴሌቪዥን አለ፤ እነሱን እመለከታለሁ።  በኋላ ላይም ጄቲቪና ፋና ተጨምረው ነበር፡፡ የኳስ ቻናልም አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች መልካም ነበሩ። ግን ሚዛናዊ መረጃ አናገኝም፡፡ ጋዜጣ፣ መፅሄት አይደርሰንም፡፡ በአጋጣሚ ገብቶ ከተገኘም ልክ እንደ ሃሺሽ ነው የሚቆጠረው፡፡ ስለዚህ ብናገኝም ወዲያው አንብበን እናስወግደዋለን፡፡ ሬዲዮም መስማት አንችልም፡፡
“ያልተሄደበት መንገድ” እና “የሀገር ፍቅር እዳ” የተሰኙ መፅሐፎችህን በእስር ላይ ሆነህ ነው የፃፍከው፡፡ እንዴት ነው ልትጽፋቸው የቻልከው?
እርግጥ የፃፍኳቸው መፅሀፍት እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ሁሉም የህትመት ብርሃን ቢያገኙ ኖሮ በ6 ዓመት የእስር ቆይታዬ የፃፍኴቸው መፅሐፍት አምስት ይሆኑ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የማርቲን ሉተር ኪንግ አድናቂና ወዳጅ ነኝ፡፡ የሱ መርሆች ደስ ይሉኛል። I have a Dream የሚለው መፅሐፉን ተርጉሜ ለማውጣት ስሞክር ተያዘብኝና ተወሰደ። በድጋም ተስፋ ሳልቆርጥ ተርጉሜ ለማውጣት ችዬ ነበር፡፡ ለወዳጆቼ እንዲያሳትሙት ሰጥቼ ነበር፤ የት እንደደረሰ ገና አልጠየኳቸውም፡፡  የማረሚያ ቤት የመጀመሪያ ስራዬ እሱ ነው፡፡ ሁለተኛው “ያልተሄደበት መንገድ” የሚለው መፅሐፌ ነው። በጣም ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ነው የፃፍኩት። ዋናው ዓላማ ማንዴላ እንዳሉት፤ አሳሪው በስነ ልቦናና በአካል ታሳሪውን ሰብሮ ለማውጣት ነው። እስረኛው ደግሞ በአካልም በመንፈስም ሳይዝል ተጠናክሮ መውጣት ነው አላማው፡፡ ስለዚህ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ግብግብ አለ ለማለት ነው። እኔም በመንፈስም በአካልም ጠንክሬ ለመውጣት ጊዜዬን በአግባቡ፣ በማይመች ሁኔታ ውስጥም ቢሆን መጠቀም ነበረብኝ፡፡ የታሰርኩበት ክፍል ቤቷ ጠባብ ነበረች። መሬት ላይ ነበር የምተኛው፡፡ በሯ ሲዘጋ ቤቷ በፍርስራሽ ነው የምትሞላው፡፡ በዚያ ላይ በቤቷ ውስጥ በተለያየ ወንጀል የታሰሩ አብረውኝ ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳ ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ክፍሏ መቀመጫ ቦታ እንኳ የላትም፡፡  ስለዚህ እዚያው ፍራሽ ላይ ለመሆን ግድ ይላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያለው አማራጭ ወይ ማንበብ አሊያም መፃፍ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ነው መጻህፍቶቼን የፃፍኳቸው፡፡ በተጨማሪም ብዙ ግጥሞችን እፅፍ ነበር። “የማይሸነፈው መንፈስ” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ አንድ ረዥም ግጥም ፅፌ ነበር፡፡ ለፕሬዚዳንት ኦባማም የፃፍኩት ደብዳቤ አለ፡፡ ሌሎችም በርካታ ግጥሞችና ፅሁፎች አሉኝ፤ ሁሉም የህትመት ብርሃን እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ ሁለተኛው መፅሐፌም በዚህ መንገድ ነው የታተመው፡፡
በምትጽፍ ወቅት የሚያጋጥሙህ ችግሮች አልነበሩም? እንዴትስ ከማረሚያ ቤቱ  ወጥተው ሊታተሙ ቻሉ?
በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ተደብቀን ካልሆነ በፍተሻ ካገኙት ስንት የደከምንበትን ይወስዱብናል፡፡ እነዚህን ችግሮች በሙሉ ተቋቁመን ነው የምንፅፈው፡፡ ወደ ውጪ ወጥተው የታተሙበትን መንገድ ግን ባልገልፀው መልካም ነው፡፡ ሌሎችም ያንን መንገድ ስለሚጠቀሙበት መናገሩ አይጠቅምም፡፡
የዕድሜ ልክ እስራት ነው የተፈረደብህ … ከእስር ቤት እወጣለሁ ብለህ አስበህ ታውቃለህ?
የታሰርኩበት ምክንያትና አላማ ለውጤት እንደሚበቃ አምን ነበር፡፡ ስታሰር ተስፋዬ ያ ነበር። ግን ልሞትም እንደምችል አምን ነበር፡፡ ምክንያቱም በ1997 እድሜ ልክ ተፈርዶብኛል፡፡ ይሄኛው ሁለተኛ የእድሜ ልክ ፍርድ ነው፡፡ በነበረው የህግ አግባብ ቢሄዱ ኖሮ፣ ሊፈረድብኝ የሚችለው ሞት ነበር፡፡ ይሄንንም አምኜ ባለቤቴን በስነ ልቦና አዘጋጅቼያት ነበር። ቀጥሎ የሚፈጽሙት የሞት ፍርድ ነው ብዬ ደጋግሜ ነግሬያታለሁ፡፡ እኔም ፍርዱን ለመቀበል ዝግጁ ነበርኩ። ከፍርድ አልፎም ድንገት ልገደልም እችላለሁ የሚል ግምት ነበረኝ። ለዚያም በህሊናዬ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአረብ አብዮት የተቀሰቀሰበት ወቅት ነበር፤ ያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቀሰቀስ አይፈልጉም፤ ስለዚህ እኔን መቀጣጫ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ግን ብሞትም የቆምኩለት አላማ ለውጤት እንደሚበቃ አምን ነበር፡፡ ዝም ብዬ ያንን ብሩህ ጊዜ አስበው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ሲመጡ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ልፈታ እንደምችል እያመንኩ መጥቻለሁ፡፡
ትግሉ ከፍ ወዳለ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን ስመለከት፣ ተስፋ አድርግ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ለነፃነቱ የሚከፍለውን ዋጋ ሁሉ መክፈል አለበት ብዬ አምናለሁ። ከፈራህ ነፃነትን መጎናፀፍ አትችልም፡፡ አንድን አፈና ፊት ለፊት ሳትጋፈጥ፣ ዝም ብለህ ስልታዊ ትግል እያልክ መቀጠል፣ አምባገነንነትን አያሸንፍም፡፡ አንዳንዶች በብልጣብልጥነትና በመሙለጭለጭ መታገል የሚቻል ነው የሚመስላቸው፡፡ ይሄ አይደለም ውጤት የሚያመጣው፡፡ ውጤት የሚያመጣው የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል ሲቆረጥ ነው፡፡ ያኔ ፈጣሪም ይረዳሃል፡፡ የፖለቲካ ትግል ማለት ራስን ማዳን ሳይሆን ራስህ ሞተህ ዓላማህን ማዳን ነው። በዚህ ቆርጬ ስለገባሁበት፣ ይሄ ነገር እንደሚመጣ አውቅ ነበር፡፡
አንድ ወቅት ብቻህን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተህ ነበር … ስለሱ ጉዳይ ብትነግረን?
አስታውሳለሁ 1994 ዓ.ም ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን በታሰርኩበት ወቅት አንዱ ደስ ያለኝ ጉዳይ፣ ውጪ አየው የነበረውን የሰውን ሰቆቃና ስቃይ አለማየቴ ነው። ምክንያቱም ውጪ በነበርኩበት ወቅት እኔ የሞቀ ብርድ ልብስ ለብሼ፣ ሌላው ዝናብ ላይ እንደተኛ ነበር የማስበው፡፡ ይሄ ውስጤን እረፍት ይነሳኝ ነበር፡፡ ያ አጋጣሚ የተፈጠረውም በ1994 ድርቅ ነበር፡፡ ተማሪ በነበርንበት ወቅት ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው ጓደኞች ነበሩኝ። እኔና ጓደኞቼ፤ “ብሉ ሸርትስ አጌነስት ፖቨርቲ” የሚል ቡድን አቋቁመን፣ በየአካባቢው መፈክር እየጻፍን፣ ”ሰው ሰውን እንዲረዳ እናንቃ፤ 14 ሚሊዮን ህዝብ ተርቦ ሰው እንዴት የራሱን ኑሮ ይኖራል” በሚል ህብረተሰቡን እንቀስቅስ ብዬ ጓደኞቼን ጠየቅኋቸው፡፡ “አንተ እብድ ነህ እንዴ? የማይሆን ነገር ነው” አሉኝ፡፡ ወዲያው ራሴ በግሌ ማድረግ ያለብኝን አሰብኩና፤ “የረጅም ዘመን የገናና ታሪክ ባለቤት ሆነን፣ ሰፊ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት ሆነን እንዴት ልንራብ እንችላለን” የሚል እና ሌሎች መፈክሮች በራሴ ላይ ለጠፍኩኝ፤ ከዚያ ወደ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሄድኩና ከየኔ ቢጤዎች ላይ ድሪቶ አገኘሁ፡፡ ድሪቶውን የሰጠኝ የኔ ቢጤ የደርግ ወታደር ነበር፤ በ10 ብር ነበር ልከራየው የፈለግሁት፤ እሱ ግን አላማዬን ስነግረው፣ ”አንተ ለኛ ይሄን ያህል ከጮህክ ለምን አስከፍልሃለሁ” በማለት እምቢ ብሎኝ በግድ አግባብቼ፣ አስር ብር ሰጠሁት። በወቅቱ ያደረግሁት ከስር የኢትዮጵያ ባንዲራን ለብሼ፣ በላዬ ላይ ድሪቶውን ደረብኩበት፡፡ በላዬ ላይ ከለጠፍኳቸው መፈክሮች አንዱም፤ “ይሄ ድሪቶ በባንዲራው ላይ እንደሚያስጠላ ሁሉ ድህነትም በኛ ላይ ያስጠላል” የሚል ነበር፡፡
የሰላማዊ ሰልፉን መነሻ ያደረግሁትም ከመስቀል አደባባይ ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙ ሚዲያዎች ሁነቱን እንዲዘግቡልኝ ጠርቼ ነበር፤ ግን አንድም የተገኘ የለም። ሔለን መሃመድ ብቻ ከአሜሪካ ድምፅ ዘግባዋለች፡፡ ሰልፉን ከመስቀል አደባባይ ጀምሬ፣ በመገናኛ ዞሬ፣ በ4  ኪሎ ፒያሳ፣ ከፒያሳ መስቀል አደባባይ ሄድኩ፡፡ ይሄን ሳደርግ ባዶ እግሬን ነበርኩ። 4 ኪሎ አካባቢ ስደርስ እግሬ በመሬቱ ንዳድ ግሎ፣ በጣም ነበር ያሰቃየኝ። ሄለን መሃመድ ራሷ እግሬን አይታ ነበር ስለ ጉዞው ያመነችው፡፡ እየተጓዝኩ እያለ 4 ኪሎ ነበር ያገኘችኝ፡፡ ኢቲቪዎችንም ጠርቻቸው ነበር ግን አልተገኙም፡፡ አሁን ስሙን የማልጠቅሰው አንድ በህይወት የሌለ ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ፣ “አንድ ልጅም እንዲሁ በብስክሌት ጉዞ አደርጋለሁ እያለ ውጪ ሄዶ ቀርቷል፤ አንተም እንደዚያ ልታደርግ መሆን አለበት” ብሎኝ ነበር፡፡
ዓላማህን ደግፎ የተከተለህ ሰው አልነበረም?
እንዲያውም አንዳንድ ቦታ ላይ ይሰድቡኝ ነበር፤ ከፒያሳ ቁልቁል ስሄድ አስቁመው ሁሉ አስፈትሸውኝ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ነገር  እንጂ ማንም የተከተለኝ አልነበረም፡፡
ብዙ ዋጋ የከፈላችሁበት “አንድነት” በውዝግብ እንዳልነበረ ሲሆን ምን ተሰማህ?
እኔ በአንድ በኩል መንቻካ ነኝ መሰለኝ ነገሮችን ቶሎ አልቀበልም፡፡ ቅንጅትም ይፈርሳል የሚል ግምት አልነበረኝም ነበር፡፡ ሰዎች ሁሉ በቅንጅት ተስፋ ሲቆርጡ እኔ አልቆረጥኩም ነበር፡፡ አሁንም አንድነት እንደዚያ ሲሆን እስር ቤት ሆኜ ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ በመጨረሻ ወንደሰን ክፍሉ መጥቶ ስለ ጉዳዩ ሲነግረኝ፤ “ግዴላችሁም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ሞክሩ” አልኩት፡፡ እሱም አምርሮ እያለቀሰ፤ “አሁንም ተስፋ አትቆርጥም?” አለኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ማንንም ሰው አላገኘሁም። በኋላ ትንሽ ተሰምቶኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን ትግል በዚህ ብቻ አይደለም በሚለው ተፅናናሁ፡፡ ዛሬ በየቦታው ተበጣጥሰው የምናያቸው ፓርቲዎች እንዲህ የሆኑት የሊቀ መንበርነትን ቦታ ለመያዝ በሚደረግ ሽኩቻ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የህዝብ ትግል ሲሞት በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ስልጣን መፈለግ ጤናማነት ነው፤ ሆኖም የትግል ዓላማው ራሱ ስልጣን ብቻ ሲሆን ግን አደገኛ ነው፡፡ ይሄ በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ መታረም ያለበት ነው፡፡ “እኔ ብቻ ልምራ” ማለት መታከም ያለበት ደዌ ነው። በዚህ ውስጥ ገዥው ፓርቲም ድርሻ ነበረው። እኔ “ፓርቲዎች ከተዳከሙ ህዝቡ ትግሉን ይረከባል” የሚል ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ አንዳንዴ ሁኔታው በመከራ ውስጥ የተገኘ ፀጋም ይመስለኛል፡፡ አገዛዙ ፓርቲዎችን ሲያፈርስ፣ ትግሉ ወደ ህዝቡ ወረደ፡፡ ተስፋ ያደረገባቸው መሪዎቹ ተስፋ ሲያስቆርጡት፣ ህዝቡ ራሱ ታጋይ ሆነ፡፡ ለኔ አሁን ያለው የሰው ስሜት ተዓምር ሆኖብኛል፡፡ ነፃ አውጪዎችን ቁጭ ብሎ ከመጠበቅ ይልቅ እያንዳንዱ ለራሱ ነፃነት ነበር መታገል የሚገባው፡፡ ይሄም በመሆኑ ትግሉ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ልክ እንደ 1966 አብዮት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ያኔ አብዮቱ በወታደር ነበር የተነጠቀው፤ ይሄ እንዳይደገም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
አሁን በሀገሪቱ የሚታየውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዴት ታየዋለህ?
ከ1997 እና 1953 የእነ መንግስቱ ንዋይ እንቅስቃሴ ጋር ማመሳሰል ይቻላል፡፡ እነ መንግስቱ ንዋይ ዓላማቸውን ይዘው የሚሄዱ ወጣቶችን ነበር ያነቁት። በ1997 ላይም የታሰርነውና ፓርቲያችን የፈረሰው ሳንተኩስ ሳንገድል፣ በግፍ ነበር፡፡ የእነ መንግስቱ ንዋይ እንቅስቃሴ የፈጠረው ተፅዕኖ እየተስፋፋ መጥቶ በመጨረሻ ንጉሱን ጭንቀት ውስጥ ነበር የከተተው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተተካክተው ነበር፡፡ ህዝቡ ደግሞ ሂደቱን እየተሳተፈ ይከታተል ነበር፡፡ አሁንም ያለው ስሜት የዚያ አይነት ነው፡፡ የህዝብ ግፊት አለ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለመልቀቅ ማመልከቻ አስገብተዋል። በዚህ በእጅጉ ይመሳሰላል፡፡ ይሄን ሁኔታ በጥንቃቄና በብልሀት ካልያዝነው፣ የ1966 እጣ ፈንታ ሊያጋጥም ይችላል። ሀገሪቱንም ወዳልታሰበ ውድቀት ልንወስዳት እንችላለን።
አገዛዙም ለውይይት መንገድ መክፈት አለበት። መፍትሄው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አይደለም፡፡ ህዝብ፤ “ታፍነናል ነፃ አድርጉን” ነው እያለ ያለው። ይሄን ጥያቄ ለሚያቀርብ ህዝብ፣ ሌላ የባሰ አዋጅ ማወጅ፣ ጨለማን በጨለማ ለመግፈፍ መሞከር ነው፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው አገዛዙ፣ የአገራችን ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር መመካከር ነው፡፡ ያገባናል የሚሉትም ወገኖች፣ አገዛዙን ገፍትሮ ለመጣል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ሁላችንም ሀገሪቱን ወዴት እንውሰዳት ማለት ነው ያለባቸው፡፡ ሃሳብ በሃሳብ እንዲሸነፍ እንጂ ሃሳብ በኃይል እንዲመታ መደረግ የለበትም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ለዚህ አላማ መቆም አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር መታሰብ አለበት፡፡
ከዚህ በኋላ ዕቅድህ ምንድን ነው? በፖለቲካ ተሳትፎህ ትቀጥላለህ ወይስ–?
ገና አልወሰንኩም፡፡ ከቤተሰቤ፣ ከወዳጆቼ ጋር መምከር፣ ማንበብና መረዳት አለብኝ፡፡ ያኔ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ፡፡

አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic