>

ድምጽ የመስረቅ አባዜ (ክንፉ አሰፋ)

      አይን እና እግር ያወጣ ውሸት ሲሰማና ሲታይ ይህ የመጀመርያው አይደለም። “ጨፍኑ እናሞኛችሁ” አይነት ንቀት ግን አሁን ላይ ፈሩን እየለቀቀ ይመስላል። ወያኔ እንደለመደው በአደባባይ ህግ አፍርሷል። ይህ ስርዓት ራሱ ያላከበረውን ህገ-መንግስት ሌላው፣ ሕዝብ እንዴት አድርጎ ሊያከብርለት ይችላል?

      ሃገሪቷን  በወታደራዊ አገዛዝ ስር የሚያስገባ ሕግ ወጥ አዋጅ በተጭበረበረ ድምጽ ዛሬ አጽድቀዋል።ይህ በታሪክ መዝገብ ላይ ከሚሰፍሩ የጨለማ ቀናት አንዱ ነው።

      የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም፣ 122ኛው የአድዋ  በዓል ከወትሮ ለየት እና ደመቅ ብሎ ተከብሯል። ይህ ቀን ለወያኔ ምኑም አልነበረም። ህወሃት የአድዋ ድል ቢቻል ባይነሳ ይመርጣል። ሃገሪቷን  እየጠላ፣ ታሪኳን እያንቋሸሸ፣ ሕዝቧን እየገደለ የሚገዛ ስርዓት።    ጭንቅ ሲይዘው፣  የባንድራ ቀን ማክበር እንደጀመረ ሁሉ፣ አድዋም ዘንድሮ እንዲከበር ፈቅዷል። ይህ ያለምክንያት አልሆነም።  ሕዝብ በአደባባይ በነቂስ ወጥቶ በእልህ ስሜት አድዋን ሲያከብር፣ ፓርላማ ውስጥ አንድ ድራማ ይታይ ነበር።

      ፓርላማ ውስጥ እያሉ በ346 ድምጽ ጸደቀ አሉን። ከፓርላማ ሲወጡ ደግሞ ድምጹ አድጎ 395  ሆነ!  ልብ በሉ ልዩነትቱ የ49 ሰው ድምጽ ነው። 49 ድምጽ ከየት መጣ? ሞተዋል የተባሉ አባላትም ቢሆኑ 8 ናቸው።  ለመዋሸት እንኳ የማይመች ውሸት ነው ምክንያቱም ቁጥር ነዋ! ቀጥር ደግሞ ከመደመር፣  ከመቀነስ፣ ከማካፈል እና ከማባዛት ውጭ አይደለም። በነሱ አተያይ 90 ሚሊየን ሕዝብ ሂሳብ አይችልም። መላው የኢትዮጵያ  ሕዝብ አልተማረም።  በዚህ ደረጃ ዘቅጦ ሕዝብን መናቅ እና ሕዝብ ላይ መቀለድ ግን ከምን ሊመጣ ይችላል? ከፍርሃት ወይንስ ከድንቁርና?

      አባዱላ የተቀመጠበት ወንበር ራሱ በተሰረቀ ድምጽ የተገኘ ስለሆነ፣  ስርቆቱ ለሱ አዲስ አይሆንበትም። ስለተደጋገመ ለምዶታል። ሰውዬው የፓርላማውን መዶሻ ከመጨበጡ አስቀድሞ መሰረታዊ የሂሳብ ትምህርት እንኳን ቢወስድ፣  ለአሁኑ ውርደት ላይዳረግ ይችል ነበር። የ539 2/3ኛን ለማስላት መሰረተ ትምህርት መማር ብቻ ይበቃል እኮ!

      እርግጥ ነው ሂሳብን ለፖለቲካ ስሌት መጠቀም ሽምደዳን ሳይሆን ችሎታን ይጠይቃል። ብስለትን እና ጭንቅላትን ይጠይቃል። 27 አመት ወንበሩ ላይ ተቀምጠው ያልበሰሉ፣  መቼም ሊበስሉ አይችሉም። “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል” ይላል መጽሃፍ ቅዱስ። የሰው ልጅ ግን ያስመለሰውን መልሶ  አይበላም።  አባዱላ ወጥቶ ሲመለስ ከበፊቱ  የከፋ ስራ መስራት መጀመሩን አሁን አሳየ።  ወገኔ የሚለው ሕዝብ ላይ የተዶለተውን የእልቂት አዋጅ  ለማጽደቅ ተጨነቀ። “ድምጽ ከምንሰጥ በጭብጨባ እናሳልፈው!” እስከማለት እጅግ እሩቅ ተጓዘ።

      ደብረጽዮን፣ ሳሞራ የኑስ እና ገታቸው አሰፋ በሕዝብ ላይ የጫኑትን ሕግ ለማጽደቅ ቢያንስ 539 ድምጽ ያስፈልግ ነበር። አባዱላ ገመዳ በ 346 ድምጽ አጽድቆታል። የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዘጋቢ ከስፍራው በመቅረጽ-ድምጽ የስተላለፈም መልዕክት፣ ከአፈጉባኤው ድረ-ገጽ ላይ ሰፍሮ ከነበረው ጋር አንድ ነው። እጅግ የሚያሳዝነው፣ አዋጁን በተጭበረበረ መንገድ ማሳለፋቸው ሳይሆን፣  ስህተታቸውን ለመሸፈን የሚፈጥሩት ሌላ ስህተት ነው። እውነታውን ላይለውጠው፣ እንደ ሰነፍ ተማሪ ማህበራዊ ድረ-ገጻቸውን መሰረዝ እና መደለዝ ብዙ ጣሩ።

      ወደ ህሊናቸው የተመለሱት አባላት፣  በተገኘችው ትንሽ ቀዳዳ ድምጻቸውን ለማሰማት እጅ ቢያወጡም አልተሳካም።  ህሊናቸውን የሸጡ አባላት ይሰሩ የነበረውን ድራማ እየተመለከትን ብዙ ታዘብን።  የአንዳንዶቹ መንሰፍሰፍ ጉድ ያስብላል። ሁለት እጁን ያወጣ “የህዝብ ተወካይ” በምስል ይታይ ነበር። ታዛቢዎች እንደሚሉት ሰውየው ምናልባት  እጆቹን ከፍ አድርጎ “እግዚኦ” እያለ ይሆናል። አባ ዱላ ግን አንድ ሳይሆን ሁለት ብሎ ሳይቆጥረው አልቀረም። ጌታቸው ረዳ እና አህመድ ሽዴ፣  አንገታቸው እስኪጣመም እየተጠመዘዙ አባላቱን በአይን ሲያስፈራሩ ይታያል።  ሰዎቹ ምን ያህል ብርክ እንደያዛቸው በግልጽ ይታያል። ግን አዋጁ መሬት ላይ ያለውን ሁነታ አይለውጠውም። 27 ዓመታት በአዋጅ ለምትገዛ ሃገር አስቸኳይ የሚሉት አዋጅ አዲስ ነገር አይደለም።  ለሃገሪቱ ችግር መፍትሄው አዋጅ ያለመሆኑን ከቅርቡ ግዜው ትዝታ እንኳን አልተማሩም።

      ስርዓቱ በስብሻለሁ ብሏል። ደግመው ደጋግመው ይህንን ብለውታል። እንደ ጫማ ወልቆ ለሚቀየር ለዚህ   ስርዓት በዚህ ደረጃ የሚያጎበድዱ ግን ባጣን ያስገርማሉ። ከሰው የተፈጠረ፣ እንደሰብአዊ ፍጡር የሚያስብ ይህንን ህገ-ወጥ አዋጅ ለማጽደቅ ህሊናውን አይሸጥም።

      አይ አንቺ የጉድ ሃገር። “የሕዝብ ተወካዮች” በሕዝብ ላይ ጦርነት የሚያውጁባት ሃገር!

Filed in: Amharic