>

የበረከት የአትርሱኝ ተማጽኖ (ፋሲል የኔዓለም)

ሰሞኑን በረከት ስምዖን በኢቢሲ ብቅ ብሎ የአትርሱኝ ተማጽኖውን አቅርቧል። አምና በረከት ስምዖን ከአባይ ጸሃዬና አባዱላ ጋር የኢቢሲን ሰዓት ለአንድ ሳምንት ያክል ተቆጣጥሮት ነበር። ብዙም ሳይቆይ እሱና አባ ዱላ “ስራ ለቀናል” በማለት ትንሽ አቧራ አስነሱ። ኩርፊያቸው ሲያበቃ ደግሞ “ተመልሰናል” አሉ። የበረከትን የተለመደ የመልቀቅና የመመለስ ባህሪ የሚያውቁ የድርጅቱ አባላት “ በረከት ቢሸፍት ከጓሮ አያልፍም” እያሉ ተሳለቁበት። በረከትም ሃፍረቱን ውጦ ዝም አለ። አባዱላ፣ በረከትና አባይ ጸሃዬ ድርጅታቸውን ለቀው እንደገና የተመለሱ በመሆናቸው የሚመሳሰል ባህሪ አላቸው። ድርጅትን ለቆ መመለስ ደግሞ በወላዋይነት፣ ጽናት ማነስና ተስፋ ቆራጭነት ያስፈርጃል። የኢህአዴግ አባላት ሶስቱንም ሰዎች በዚህ መልኩ እንደሚያዩዋቸው ግልጽ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሶስቱም ራሳቸውን የፖለቲካ አዋቂ አድርገው ይመለከታሉ።

ትናንት በድርጅቱ ተስፋ ቆርጦ መልቀቁን ያስታወቀው በረከት፣ ዛሬ በቴሌቪዥን ቀርቦ ትንተና ልስጥ ቢል የሚሰማው የድርጅት አባል እንደማይኖር ያውቃል። በረከት በዚህ ወቅት ከቴሌቪዥን መራቁን አይፈልገውም ። በቀጥታ በቲቪ ቀርቦ ትንተና ልስጥ ቢል ደግሞ “አንተ ማን ስለሆንክ ነው ከሌሎች ተለይተህ ትንተና የምትሰጠው” የሚል ከራሱ አመራር ጥያቄ ይቀርብበታል። በተለይ ከህወሃት በኩል የሚመጣውን ትችት የሚችለው አይሆንም። ስለዚህ በረከት የዶ/ር አብይ ጉዳይ ወደ ኢቢሲ ለመቅረብ ብቸኛ መንገድ እንደሆነ አይቷል ። በረከት ዶ/ር አብይን ተችቶ በስሙ ጽሁፍ ቢጽፍ ህወሃቶች እንደሚደሰቱ ያውቃል፤ በጽሁፉ ላይ ስሙ መውጣቱም ጽሁፉ ትኩረት እንዲያገኝ ያደርገዋል። ነገር ግን የጽሁፉ ባለቤት “እኔ ነኝ” ብሎ በድፍረት ቢናገር ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያላትመዋል። ስለዚህ በረከት ጽፎ በማስተባበል በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎችን ይመታል፤ ኦህዴድን ሳያስከፋ፣ ህወሃትን አስደስቶ፣ ጸሁፉም ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎ፣ እሱም በቴሌቪዥን የሚፈልገውን ተናግሮ እና የውሸት ገጽታ ገንብቶ ተልዕኮውን ይፈጽማል። በረከት በዶ/ር አብይ ላይ ጽሁፍ ጽፎ በህወሃት ደህንነቶች በኩል እንዲሰራጭ ማድረጉን አልጠራጠርም። ወዲያውኑ በብአዴንና ኢህአዴግ ፌስቡክ ገጾች ላይ “ በረከት አልጻፈም” የሚል ማስተባበያ እንዲሰጥ ያስደረገውም እሱ ነው። በረከት ለፌስቡክ ጽሁፍ በፌስቡክ የሚሰጥ ማስተባበያ በቂ እንደሆነ ቢያውቅም፣ አላማው እሱ አልነበረምና፣ በማግስቱ በቴሌቪዥን ቀርቦ የሚፈልገውን ነገር ተናግሮ ፣ አሁንም ራሱን የህግና ፖለቲካ አዋቂ የድርጅቱ ጠቃሚ ሰው አድርጎ አሳይቶ፣ ለድርጅቱ አባላትም የአትርሱኝ ተማጽኖውን አቅርቦ ግቡን አሳክቷል።

በረከት የጠ/ሚኒስትር ምርጫ በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ እንደሚካሄድ የተናገረው ከራሱ ያመነጨውን ሳይሆን ከህወሃት የተሰጠውን ተልዕኮ ነው። እንደሚታወቀው ኢህአዴግን ለረጅም ጊዜ የመራው መለስ ዜናዊ አንድም ቀን በሚስጢር ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት መመረጡን ለህዝብ ሲነገር አልሰማንም።ሃይለማርያምም መለስን ይተካል ተብሎ በበረከት የተነገረው የኢህአዴግ ምክር ቤት ውሳኔ ሳያሳልፍበት ነው። በየትኛው ጠ/ሚኒስትር ምርጫ ላይ ተግባራዊ የሆነውን ህግ ነው ዛሬ በረከት ህግ ብሎ የሚጠቅሰው? ጨዋታው ሌላ ነው። ስውሩ መንግስት የዶ/ር አብይን ወይም የእነ ለማን ቡድን ወደ ፊት መምጣት አይፈልገውም። ይህን በገሃድ መቃወም ደግሞ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በቀጥታ ያላትማል። ከህወሃት በስተቀር ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ለጠ/ሚኒስትርነት እጩዎችን ያቀርባሉ። ሁሉም የምክር ቤት አባላት ለራሳቸው የድርጅት እጩ ድምጽ እንደሚሰጡ ይታወቃል። የመጨረሻው ወሳኝ ድምጽ እጩ ያላቀረበው የህወሃት ድምጽ ይሆናል። ህወሃት ደግሞ ለአንዱ በግላጭ ድምጽ ቢሰጥ ከሌላው ጋር ይላተማል። አብይን “ የትግሬ ጥላቻ አለበት” በሚል እንደማይደግፉት ወስነዋል ፤ በግላጭ “አንደግፍህም” ማለት ደግሞ ከኦሮሞ ጋር ያጋጨናል ብለው ይፈራሉ። ስለዚህ ይህን ወሳኝ ድምጻቸውን በሚስጢር መስጠት ይፈልጋሉ። የሚስጥር ድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓቱን ደግሞ እነሱ ከሚናገሩት ገጽታውን ለመገንባት የጓጓውን በረከት ስምዖንን አቅርበው እንዲናገር ቢያደርጉት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር በቀጥታ ሳይላተሙ ግባቸውን ያሳካሉ። ይህ ሁሉ ጨዋታ የእነ ለማን ቡድን ወደ ማእከል እንደይመጣ ለመከላከል የሚደረግ ነው። በረከትም የሚፈልገውን “ ኢጎውን” አበጥሮ ያው የአጫዋችነትና የተጫዋችነት ሚናውን አስጠብቆ ይቆያል። አባ ዱላም ነገ የበረከትን መንገድ ተከትሎ በቴሌቪዝን ባይቀርብ ከምላሴ ጸጉር ይነቀል።

ኦህዴድ ብልጥ ከሆነ የጠ/ሚኒስትር ቦታ ካልተሰጠኝ በሚል ከስውሩ መንግስት ጋር መላተም ያለበት አይመስለኝም። በሶማሊ ክልል የደረሰበትን ጥቃት በብልጠት እንዳለፈው ሁሉ ይህንንም ወቅት በብልጠት ካላለፈው በስውሩ መንግስት የመመታቱ እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን ስውሩ መንግስት ተነቅሎ ይፋዊ መንግስት በህዝብ ምርጫ እስኪቆም ድረስ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ብቸኛ አማራጩ ነው።

Filed in: Amharic