>
5:13 pm - Saturday April 19, 5045

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና ክርስትያኖች ትልቅነት እና ኅብራዊ አኗኗር (ፐሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በችሎታችውና በምግባራቸው ልዩ ሰዎች ናቸው። ከነሱ ውስጥ የወጡት ሼኮችና የእስልምና አስተምህሮ ሊቃውንት በቁራን እውቀታችውና በአረብኛ ችሎታቸው የጠለቁና የተራቀቁ ናቸው።   በቁራን እውቀታቸውና በአረብኛ ቋንቋ ጌትነታቸው ከመራቀቃቸው ብዛት ዛሬ በ ሳኡዲ አረብያ እና በሌሎችም የአረብ አገሮች ቁራንን እና የአረብኛ ሰዋሰውን አረቦቹን ራሳቸውን በማስተማር ስመ-ጥር የሆኑ አሉ። ገና በጥዋቱ በጥንቱ አስልምና መስፋፋት በጀመረበት ሰዐት ከነቢዩ መሃመድ ጎን ቆመው እስልምና በአረብያ እና በሌሎችም ክፍለዐለማት እንዲሰራጭ  ኢትዮጵያውያን ስላገዙ፣ እና የነብዩንም ዘመዶች እና ተከታይዎች በህገራችው በኢትዮጵያ በጭንቀታችው ወቅት በክብር ስለ አስተናገዱ፣ አነዚህ ኢትዮጵያውያን ዛሬ የቁራን እና የአረብኛ ቋንቋ ብቁ መምህራን ቢሆኑ አይደንቅም።
ነቢዩ መሀመድም ለኢትዮጵያውያን በጣም ቅርብ ነበሩ። የታሪክ መፃህፍት አንደሚነግሩን ክኢትዮጵያውያን ጋራ ዝምድናችው የጀመረው ገና በልጂነታቸው ነው። ወላጆቻቸው ሞተውባቸው ነቢዩ ህፃን ሳሉ አሳዳጊ ሞግዚታቸው ኢትዮጵያዊቷ ኡም አይማን አንደነበሩ ተዘግቧል። ባዳዊ የተባሉት የአረብ ታሪክ ፀሃፊ አንደሚተርኩልን  ነቢዩ በሜካ የሚያድጉ ውጣት ሳሉ በከተማው ውስጥ አይሁዳውያን እና ከርስትያኖች ነበሩ። ክከርስትያኖቹ ውስጥ ገብሬ እና የስራ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ካህናት ነበሩበት። እነዚህ ሁለት ካህናት በመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርት እጅግ የበሰሉ ስለነበሩ በወጣትነታቸው ወራት ነብዩ ከእነሱ ተወዳጅተው ማውራት ያዘወትሩ ነበር።  ሙዘየኑን ቢላልን ጨምሮ ከወታደሮቻቸው መሃል እስልምናን የተቀበሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩበት።  በእዚህ ምክንያትም ጭምር ነው እሳቸውን ያሳድዷቸው ከነበሩት ቆርሾች ዘመዶቻቸውን አሽሽተው እስልምና እስኪጠነክር ድረስ በኢትዮጵያ አንዲቆዩ ያደረጉት። በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ጥገኝነት ካገኙት ሙስሊሞች መሃል የነብዩ ሴት ልጅ ሩቅያ እና የእሷ ባል ኦትማን ይገኙበታል። ከነሱ በኋላም የነብዩ የአጎት ልጅ የሆነው ጃፋርና አጃቢዎቹ  ሙስሊሞች በአረቢያ የተከሰተውን የቀውጢውን ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላምና በተድላ እሳልፈዋል። ይህን ውለታ በማስታወስ ነብዩ “ኢትዮጵያውያን ካልነኳችሁ አንዳትነኳቸው” ብለዋል። በኋለኛውም ዘመን ደግሞ መሃመዶች የተባሉ የነብዩ ተወላጆች በወሎ ሰፍረው በጊዜ ሂደት ውስጥ ከኢትዮጵያውያን ጋራ በሀይማኖት እና በደም ተቀላቅለው ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ለመሆን በቅተዋል። ክአነሱም መሀል የንጉሥ ሚካኤል እና የ ልጅ እያሱ ቤተሰብ አሉበት።
አስልምና በአረብያ ከተጠናከረ በኋላ  አረቦቹ  ወደ ሃገራችው ሲመለሱ የወቅቱ ኢትዮጵያዊው ንጉሠነገሥት ከአክሱም ለነቢዩ መሃመድ የተለያዩ ስጦታዎች ልከውላቸው ነበር። ከስጦታዎቹ  ውስጥ የሃር አልባሳት፣ የጦር መሳሪያዎች፣ አገልጋዮች፣ ሁለት ሰጋር በቅሎዎች ከነኮርቻቸው፣የከበረ ደንጊያ እና  ወርቅ፣ እንዲሁም ማርያም እና አክባር(በለጡ?) የተባሉ ክርስትያን ልጃገረዶች ይገኙባቸው ነበር። ማርያምን ነቢዩ ራሳቸው አገቧት። አክባርን ለሚወዱት ገጣሚያችው ለ ጣቢት ልጅ ለሃሰን ዳሩለት። ነቢዩ ታመው የአልጋ ቁራኛ ሆነው በሚሞቱበት ጊዜ በመጨረሻ የተጠቀሙበት በኢትዮጵያ መድኅኒት እንደሆነ ተዘግቧል። ይህ ሁሉ ሁኔታ እና ነገር ኢትዮጵያውያን ለእስልምና እድገት እና ጥንካሬ የአደረጉት አስተዋፅኦ ነው። በእዚህ ሁሉ  የሚኮሩት  ሙስሊሞቹ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቻችንም ጭምር ነን።  በአጠቃላይ ሲታይ ግን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በነገረ ሁኔታችው ልዩ ናቸው። ምን ማለቴ አንደሆን እታች እገልጣለሁ።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች፣ ከሃይማኖታቸው አስተምህሮ ጋራ ታላቅ ኢትዮጵያዊነታቸው ተደምሮበት ከፍተኛ ምግባር እና ተግባራት ያንፀባርቃሉ። ከክርስትያን ወገኖቻቸው ጋራ በአንድ ሀገር ሲኖሩ፣  በሌላ ሀገር የማይታዩ ታጋሽነት፣ ቀረቤታ፣ ሃይማኖታዊ መቻቻል፣  ጋብቻ፣ በሰላም የተጌጠ ማህኅበራዊ ኑሮ ያከናውናሉ። አነዚህ እሴቶች ከብዙ በጥቂቱ የነሱ ገንዘብ ናቸው። ሆኖም ክርስቲያን ወገኖቻቸውም እንደ እነሱው ምግባራቸው ከፍ ያለ ባይሆን ኖሮ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ በሆነባቸው ነበር።  የሁለቱም ሃይማኖቶች አማኞች የታላላቅ ኢትዮጵያውያን ዘር ስለሆኑ አነሱም ትልቅነትን ትጎናፅፈዋል። ሰለ እዚህም በህብር፣ በፍቅር እና በሰላም ተግባብተው እና ተቻችለው ”ሃይማኖት የግል ነው፣ ሀገር የጋራ ነው” ብለው ጠላትን እያስቀኑ አብረው ይኖራሉ። ክእዚህም በላይ ከተዋደዱ ያለ ምንም ጣጣ ትጋብተው ይዋለዳሉ።
በየትኛው ዐለም ላይ ሙስሊሞች እና ክርስትያኖች ተባብረው እየተጋገዙ መስጊድና ቤትክርስትያን ሲገነቡ ይታያሉ? በኢትዮጵያ ብቻ።
በየትኛው ሀገር እስላሞችና ክርስትያኖች በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ጎን ለጎን ሆነው አብረው እየፀለዩ ቁራናቸውን እና ቅዱስ መፅሃፋቸውን ያነባሉ? በኢትዮጵያ ብቻ። ለእዚህ ማስረጃ ከእዚህ ፅሁፍ ጋራ የቀረቡትን ሁለት ፎቶግራፎች መመልከት ነው። በእዚህ አጋጣሚ መዘንጋት የሌለበት፣ መርካቶ በሚገኙት በአንዋር መስጊድ እና በራጉኤል ቤተክርስትያን አስተዳዳሪዎች እና በምእመናኑ መካከል የአለው እጡብ ድንቅ ግኑኝነት ነው። ህልውናቸውን የሚያሰጋ ድንገተኛ ነገር ሲመጣ ሞረሽ ብለው ተጠራርተው ይደራረሳሉ። ምእመን በዝቶ ለመስገጃ ቦታ ከጠፋም ቦታ ይሰጣጣሉ። ከጥቂት ዐመታት በፊት አንዋር መስጊድ ሞልቶ ተርፎ  የሙስሊሙ ምእመን ተችግሮ ሳለ የራጉኤል ሊቀካህን “ኑ ልጆቼ እኛ ግቢ ውስጥ ስገዱ፣” ብለው አበባ ምንጣፍ እንደዘረጉላቸው ተወርቶ ነበር። ይህ ክስተት ብቻ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ክርስትያኖች ብርቅዬ ሰዎች እንደሆኑ ጮሆ ያውጃል።
በየትኛው ግዛት ሙስሊሞችና ክርስትያኖች ያለ ጣጣ በነፃ ተጋብተው “መሃመድ አማኑኤል እና ኡስማን ገብረክርስቶስ፣ ወይም በቀለ  ኢብራሂም እና  አሚና ጌታችው” ብለው ልጆቻቸውን ይጠራሉ? በኢትዮጵያ ብቻ።
በየትኛው ምድር  ሙስሊሞች ግምባራቸው ወይም ደረታቸው ላይ መስቀል አድርገው ያውቃሉ? በኢትዮጵያ ብቻ።
በየትኛው ሰማይ ስር ሙስሊሞች ወከባ፣ ድብድባና እስር እየደረሰባቸው የእመፅ አፃፋ ሳይመልሱ የሚያስደንቅ የስነምግባር ልዕልናን  በሚያስመሰክር እና አርአያዊ በሆነ ትዕግስት ለዐመታት ”ድምፃችን ይሰማ፣ መብታችን ይከበር፣” ብቻ እያሉ መብታቸውን በስላማዊ መንገድ ያስከብራሉ? በኢትዮጵያ ብቻ። አዎን በጨዋዎቹ፣ በቁጥቦቹና በስነምግባር በታነፁት የኢትዮያ ሙስሊሞች ዘንድ ብቻ። ከዚህ በተያያዘ መረሳት የሌለበት በአሜሪካ እና አውሮፓ ከርስትያን ጳጳሳት እና ምአመናን ከሙስሊም አቻዎቻቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በኅብረት ቆመው “የወገኖቻችን ድምፅ ይሰማ” እያሉ፣ በእርግጥም መብታቸው ይከበር ዘንድ በየከተማው ያለመታከት ሰላማዊ ስልፎች አድርገዋል። እንዲሁም በተለያዩ የሬዲዋ ጣቢያዎች የድጋፍ መግለጫ ለግሰዋል።
በሀረር ፍለሀገር ቁጥራቸው ከክርስትያን የሚበልጥ ሙስሊሞች ቤተክርስትያን ገንብተው የአካባቢውን በጳጳስ ጠርተው አስመረቁ። ለጳጳሱም መሸኛ ትልቅ በሬ ገዝተው ሰጡ።  በዚያው በሀረር አንዱ ወረዳ አንድ ቤተክርስትያን ደህይቶ ተዘጋ። የአካባቢው ኦሮሞ ሙስሊሞች ክርስትያኖቹን ካህናት ቀርበው ይህ ቤተክርስትያን ከተዘጋ ጀምሮ ዝናብ ጠፍቷል፤ ድርቀት አጥቅቶን ከብቶቻችን ሞተውብናል። የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ እኛ እናደርጋለን። እባካችሁ ቤተክርስትያኑ ይታደስ እና እንደድሮው ጸልዩልን፤ ብለው ገንዘብ አዋጥተው ቸሩአቸው። በእዚህ ምክንያቱ ቤተክርስትያኑ ተከፍቶ መሥራት ጀመረ።
በስልጤ ደግሞ የማርያም ቤተክርስትያን በተንኮለኞች ተቃጠለች። ወድያውኑ ሙስሊም አባቶች እና ሼካዎች ገንዘብ አሰባስበው 15 ሚሊዎን ብር አዋጥተው ከበፊቱ ከተቃጠለው ቤተክርስትያን መቶ ጊዜ ያሸበረቀ ቤተክትስትያን አንጸው ለክርስትያኖቹ ወገኖቻቸው አስረከቧቸው። እንዲህ ዐይነት አስገራሚ እና ቅዱስ ተግባር የሚፈጸም በድንቅዬዎቹ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዘንድ ብቻ ነው። ይሄ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ሙስሊሞቹን ወገኖቻችንን ልንወዳቸው፥ ልናፈቅራቸው እና ልናደንቃቸው እንገደዳለን።
በወሎ በአንድ ቤተክርስትያን ምእመናኑ ተመናምኖ የገንዘብ እጥረት በመከሰቱ ካህናቱ ታቦቱን ወደሌላ ቦታ ሊወሰዱ ተነሱ። ይህን የዐዩ ሙስሊሞች ተጠራርተው አገዷቸው። ምነው ቢሉአቸው ይህ ታቦት የኛም ነው። ይህ ታቦት ከአያት ቅድመአያቶቻችን ዘመን አንስቶ፥ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ አብሮን የኖረ ነው። ቡራኬአችን ነው። ስለእዚህ ለቤተክርስትያኑ የሚያስፈልገውን ሁሉ እርዳታ እኛ እናደርጋለን እንጂ ቡራኬአችንን ወደሌላ ሰፍራ አትወስዱም። ታቦቱ እዚሁ እንደጥንቱ አብሮን ይኑር፤ ብለው አስቀሩት።
እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ  እላይ በተቀመጡት ምክንያቶች የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልዩና ክቡር ናቸው። በመሆናቸውም የሚኮራባቸው እና የሚደነቁ ናቸው። እኔ በበኩሌ ከማድነቅም አልፌ እደመምባቸዋለሁ።
ለመደምደም ያህል፣ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ክርስትያኖች መሃል ያለው የተቀደሰ ግኑኝነት ለታላቅነታችን አማኝ ከመሆኑም ባሻገር አብሮ በሰላም፣ በፍቅር እና ኅብር ለመኖር የሚያስቸለን ስለሆነ ተንከባክበን ልንይዘው ይገባል። በዐለም ዙሪያ ላሉት ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖችም አርአያ ሆነን በአንድ ሃገር ውስጥ እንዴት ያለ ግጭት በመቻቻል፣ በፍቅር እና በሰላም ለመኖር እንደሚቻል እናስተምራቸዋለን። አስከዛሬ የአለው የሙስሊም እና ክርስትያኖች ግኑኝነታችን የአማረ ስለሆነ እንዲሁ አንደአማረብን አንድንዘልቅ በመሃላችን ንፋስ አንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን። እኔ ለጊዜው ስለ ሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች አወሳሁ እንጂ ሌሎቹም ባህላዊ ወይም ሀገራዊ ሃይማኖቶችም ከእነዚ ከሁለቱ  ሃይማኖቶች እና ምእመናን የ አላቸው ግንኙነትም ሸጋ ነው። አነሱም “ሃይማኖት የግል ነው፣ ሀገር የጋራ ነው፣” በሚለው መርሆ ቢመሩ ለፍቅራችን፣ ሰላማችን እና አንድነታችን ይበጃል።
እነዚህ እታች ያሉት ፎቶግራፎች  ከድሮ ዘመን ጀምሮ ሙስሊሞች እና ክርስትያን ኢትዮጵያውን  መስጊዶችን እና ቤተክርድትያናትን በፍቅርና መከባበር ተጋርተው እንደሚጸልዩ ይመሰክራሉ። እንደዚህ የሚሆን በቅድስቲቱ ኢትዮጵያ ብቻ ነው።
Filed in: Amharic