>

''አንዳርጋቸውን አግኝተኸው ታውቃለህ ወይ?'' ለእስክንድር የቀረበ ጥያቄ (ሰርካለም ፋሲል)

እስክንድርም፦” እኛ የታሰርንበት ስፍራ ዋይታ ይባላል። ዋይታ በ 3 ይከፈላል። ማለትም፣ ግቢው አንድ ሆኖ ሶስት ቦታ ከልለውታል። በዚህ ግቢ ውስጥ ፣ አንደኛው፦ አንዳርጋቸውና 2 ሰዎች ይገኙበታል።
ሁለተኛው፦ አንዱአለምና መላኩ ፈንታ
ሶስተኛው፦ እኔ (እስክንድር) አበበ ቀስቶ እና ገብረዋሃድ ያለንበት ነው።

ከአንዳርጋቸው ጋር አብረውት የታሰሩት ሁለት ሰዎች በነፍስ ማጥፋት የተፈረደባቸው ናቸው። በአዲስ አበባ ውስጥ ምንም ጠያቂ የላቸውም ። ተመርጠው የገቡ ይመስለኛል። አንዳርጋቸውን በሳምንት አንድ ግዜ ቅዳሜ ለቤተሰብ ጥየቃ ሲወጣ በቀዳዳ እንመለከተዋለን። አንዱአለምንም እንደዚያ። መነጋገር ግን አንችልም።ሁላችንም በቀዳዳ ከመተያየት በስተቀር መካከላችን ያለው አጥር እንድናወራ አያደርገንም። አንዳርጋችውን አግኝቼ ማውራት ባልችልም ልናገር የምችለው የተለየ ነገር አይተንበት አናውቅም” ብሎኛል።

የዋይታ አጥር ይናድ!! አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሁለም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!! ድል ለዲሞክራሲ!!

በተያያዘ በቅርቡ ከእስር የተፈታው እስክንድር addis insight ከተባለ ድህረ ገፅ ጋር ቃለምልልስ ማድረጉ ይታወሳል ። በቃለምልልሱ እስክንድር ሳይታሰር በፊት ያነሳው የነበረውን የህሊና ነፃነት ”ኢሹ”፣ እንዲሁም ወረቀት እንዳይገባ በተከለከለበት ግዜ ምን ላይ ይጠቀም እንደነበር የተናገረበትን ክፍል ገልብጬ አቅርቤዋለኹ… ተመልከቱት…..
አሳሪዎቹ እና እስክንድር “አትፃፉ” ….”እንፅፋለን የህሊና ነፃነት አትግፈፉን” 
*  የእስር ቤት ቆይታህ ምን ይመስል ነበር? ውስጥ የነበረው የመማር ሁኔታስ?  እንዲሁም ደግሞ እስር ቤት ውስጥ ስትሆኑ የሚዲያ ነፃነቱ ምን ይመስል ነበር?
እስክንድር፦
* እንግዲህ እስር ሲያጋጥምህ የተለያየ ስቴጅ ውስጥ ነው የምታልፈው። የመጀመሪያውን ስቴጅ የምታልፈው በማዕከላዊ ነው ። ማዕከላዊ ምርመራ ከጨረስክ በኅላ ወደ ቃሊቲ ትሄዳለህ። ቃሊቲ ሄደህ የሚፈረድብህ ከሆነ፣ እዛ ትቆያለህ። አለበለዚያ ነፃ ትወጣለህ። በማዕከላዊ በነበረኝ ቆይታ የተለየ ነገር አላጋጠመኝም። አሁን መጨረሻው ላይ ምንም የደረሰብኝ ነገር የለም። ይህ ማለት ግን፣ በገባሁባቸው 8 (ስምንት)ግዜ፣  ይሄ ለ9ኛ (ዘጠነኛ) ግዜ ነው የታሰርኩት፣ በእነዛ 8 ግዜ ውስጥ ከጥፊ አንስቶ…ወደ ካልቾና ድብደባ ተሸጋግረው፣  መጨረሻ ላይ ገልብጠው ውስጥ እግሬን ገርፈውኛል። እንደዚህ ያደረጉኝ በጋዜጠኝነት ስራ ብቻ ነው። ሌላ ጉዳይ ሳይነሳ። እንደአሁኑ የሽብርተኝነት ኢሹ ሳይነሳ ። በተፃፈ ጉዳይ ብቻ ከጥፊ እስከ ቶርች ያለፍኩበት ጉዳይ ነው። እግዜር ይስጣቸው አሁን መጨረሻ ላይ ምንም ያደረሱብኝ እንግልት የለም። ቃሊቲ ከደረስኩኝ በኅላ፣ ብዙ ነገር ሆኗል። አብዛኛውን ነገር ባልፈው ይሻላል። የማልፍበት ምክንያት አለኝ። የደረሰብኝ ነገር ትርጉም የለውም ብዬ አይደለም። ሲንቦሊክ ቫሊዩ አለው። ህዝብንም ያስተምራል። ወደፊትም እንዳይደገም መከላከያ አድርገን ልንጠቀምበት እንችላለን። ግን በሌላ ፎረም ላይ በደንብ ኦርጋናይዝ በሆነ መልክ ቢነሳ ይሻላል። ለግዜው ይሄ ነው።
የሚዲያን ነገር ካነሳህ፣ እንኳን ሚዲያ ለመከታተል አይደለም እኔ እስር ቤት በነበርኩበት ግዜ፣ የእስር ቤት እስር ቤት አለ። በነገራችን ላይ ሰው ታስሮ እስር ቤት ይገባል። እስር ቤት ውስጥ ደግሞ ፣ ከማረሚያ ቤት ሰዎች ጋር ሳትስማማ ስትቀር የምትገባበት እስር ቤት አለ። በተለምዶ ጨለማ ቤቶች የሚባሉት ናቸው። ጨለማ ቤት ማለት ምንም መብራት የሌለበት ክፍል ማለት አይደለም። ጨለማ ቤት ማለት ፣ በእስር ቤት ውስጥ ጥፋተኞች ናቸው የሚሏቸው እስረኞች ተለይተው የሚቆዩበት ነው። አብዛኛውን የእስር ግዜ ያሳለፍኩት እዚያ ነው። በነገራችን ላይ እኔ ጨለማ ቤት ውስጥ ብቆይም ፣ ማረሚያ ቤት ውስጥ ጨለማ የለም  ስልህ ሙሉ ለሙሉ ጨለማ የለም አይደለም። እዚያ ውስጥም ገብቻለኹ።  ለሁለት ቀን። ሌላው ጨለማ ቤት የምንለው መብራት አለው፣ግቢ የለውም። ጠበብ ያለች ነች። እዚያ ቦታ ላይ እንኳን የሚነበብ መፃፊያ የሚባል ነገር አይገባም። ወረቀት ክልክል ነው። እስክሪቢቶ ክልክል ነው።  ጋዜጣ መፅትሄማ አይታሰብም። እሱ ትልቅ፣ ትልቅ ኢሹ ነው። ከተገኘብህ ትልቅ ወንጀል ነው። ምንም ዓይነት የህሊና ነፃነት የማይፈቀድበት ቦታ ነው ከአራት ዓመት ተኩል በላይ ያሳለፍኩት።  በአካል ብቻ ሳይሆን የታሰርኩት ፍፁም የህሊና ነፃነትም የማይከበርበት ቦታ ነው የነበርኩት። እኛ ስንፅፍ የነበረው፣ በብጥስጣሽ ወረቀቶች ላይ ነው። ለምሳሌ፣ አቸቶ እንገዛለን፣ አቸቶ ዙሪያ ላይ ያለች ወረቀት ቀድደን እየፃፍን እንልካለን። ወደ ውጭ እናስወጣለን። ሳሙና እንገዛለን፣የሳሙና ወረቀት ላይ እንፅፋለን። ኦሞ ሲገባ ካርቶኑ ላይ እንፅፋለን።  ኬክ ከቤት ሲያመጡ ካርቶኑ ላይ እንጠቀማለን። በኅላ ይሄ ሲያስቸግራቸው፣ ኬክ ሲመጣ በፌስታል ያስገቡ ጀመር። ኦሞውን ገልብጠው ያስገቡ ጀመር። በእነዚህ ባሳለፍናቸው አራት ዓመት ተኩል ፣ “አትፃፉ” ….”እንፅፋለን የህሊና ነፃነት አትግፈፉን”  …በዚያ ጭቅጭቅ ውስጥ ነው ያለፍነው። እዚያ ውስጥም አላረፍንም። ውጭ የነበረንን የህሊና ነፃነት ኢሹ እዚ ውስጥም ስናነሳ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ነው ያለፍነው።
Filed in: Amharic