>
5:13 pm - Friday April 19, 8171

ከለማ ምን አገኘን? [ያዬ አበበ - የግል ዕይታ]

 

አቶ ለማ መገርሳ በብዙዎቻችን ሰፊ ትኩረት ስበዋል። ትኩረት የሳቡባቸው ከአቶ ለማ ያየናቸው ሦስት ተመራጭ (quality) ነገሮች አስተውያለሁ፦

1. በጎነትና የዋህነት /kindness and innocence

በስጋት የዛልን ፥ በዛቻ የደከምን ፥ በደረቅ ፕሮፓጋንዳ የመነመንን ህብረተሰብ ነን። እውነት የራበን ፥ ቅንነት የናፈቀን ፥ ሚዛን የምንሻ ለመሆናችን በአቶ ለማ ሃሳቦች መማረካችን ጠቋሚ ይመስሉኛል።

የዋህነታችን በኃይል እርምጃና ደም መፋሰስ ሲገሰስ ኖሯል። ውሸት ተደጋግሞ ጆሯችንን ደፍኖታል። የስውር አዕምሮ (subconscious) ዋናው ምኞታችን ጀግና ማግኘት ሳይሆን እውነትን ማግኘት ነው። ለማ እውነትን አቅምሰውናል።

2. ተስፋ / hope፦

ሰው ተስፋ ካጣ ትርጉም ያጣል። በሀገራችን ‘የድርብ አሃዝ ኢኮኖሚ እድገት’ ያልፈጠረውን ተስፋ በአቶ ለማ አቀራረብና የሀሳብ ሚዛናዊነት ተስፋችን ፈንጥቋል። ምናባችን ለጊዜውም ቢሆን እፎይታና ፈውስን አግኝቷል።

ታዳጊ ወጣቶች በየመንገዱ በአልሞ ተኳሽ ተደፍተው ፣ ደማቸው ከአፈር ተለውሶ ፤ በእናቶች የእንባ ጅረት ፣ በአባቶች የቁጭት ምሬት ለተሰበረው ልባችን የለማ መገርሳ እርጋታና ፅኑነት ድጋፍ ሆኖታል።

3. ታማኝነት / honesty and integrity፦

ቴሌቪዥን ፥ ሬዲዮ ፥ ጋዜጦችና ፥ ማህበራዊ ሚዲያው ከየራሱ መስመር ሁኔታዎችን ሲያነጠጥን ፡ አቶ ለማ በቀላልና በግልፅ ቃላት ነባራዊ እውነታዎችን ፍንትው አድርገው ሲናገሩ ፡ የተሰለብነውን የእውነት አቅጣጫ አመልካች የህሊና ኮምፓስ መልሰን ጨብጠናል።

ከአቶ ለማ መገርሳ አቀራረብ የቀመስነውን እውነት ፥ የሰነቅነውን ተስፋና የጨበጥነውን አቅጣጫ የኦሕዴድም ሆነ የኢህአዴግ ኮሚቴዎችና ስብሰባዎች አይነጥቁንም ፡ አያስጥሉንም።

Filed in: Amharic