>
5:13 pm - Thursday April 19, 3145

ህዝቡ አሁን በአዋጁ ምክንያት የሚያጣው ዴሞክራሲያዊ መብት የለውም (አብርሀ ደስታ)

የኢህአዴግ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል። በህገመንግሥቱ መሰረት አዋጁ በሚኒስትሮች ምክርቤት ይወጣል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይፀድቃል። በሁለቱም ምክርቤቶች ልዩነት ስለሌለ መፅደቁ አይቀርም።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚታወጀው አደጋ ሲያጋጥም ነው፡ ህዝብንና ሀገርን የሚጎዳ አደጋ። አደጋው የተፈጥሮ ወይ ሰው ሰራሽ ወይ የፖለቲካ (ለምሳሌ የውጭ ጠላት ሀገርን ሲወር) ሊሆን ይችላል። መንግስት ህዝብን ከአደጋው ለማዳን ሲል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊያውጅ ይችላል።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ ማለት የመንግስት አካላት  ከተለመደው ተግባራቸው ለየት ባለ መልኩ ስራቸው ያከናውናሉ ማለት ነው። የዜጎችን የተለመዱ (ይከበሩ የነበሩ) ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ለግዜው ይገደባሉ፡ አደጋውን ለማስወገድ ሲባል። ሰብአዊ መብቶች ግን በየትኛውም ሁኔታ አይገደቡም።
አሁን አዋጁ የታወጀው በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት አይደለም። የወረረን የውጭ ጠላትም የለም። በፖለቲካ ተቃውሞ ምክንያት ነው። ህዝቡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተገደበና ታፈንኩ ብሎ ተቃወመ።
አደጋ ተደርጎ የተወሰደው ህዝባዊ ተቃውሞውን ነው። ህዝብ መንግስትን የመቃወም መብት አለው። ፀረ መንግስት የሚደረግ ህዝባዊ ተቃውሞ ዴሞክራሲያዊ መብት እንጂ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚጠይቅ አደጋ አይደለም። የህዝብ ተቃውሞው ፀረ ገዢው ፓርቲ የሚደረግ ነው። የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚያስፈልገው ህዝብንና ሀገርን ከአደጋ ለማዳን እንጂ ገዢውን ፓርቲ ከህዝብ ተቃውሞ ለመጠበቅ አይደለም። ለገዢው ፓርቲ ደህንነት ሲባል ህዝብ ሊቀጣ ነው? ፓርቲን ከህዝብ ተቃውሞ ለመከላከል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሊታወጅ አይችልም። ምክንያቱም ፀረ ገዢው ፓርቲ የሚደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ አደጋ የሚወገደው የችግሩ ምንጭ የሆነውን ገዢውን ፓርቲ ከስልጣን በማባረር እንጂ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን በማወጅ መብቱ የጠየቀ ህዝብን በማፈን አይደለም። ስለዚህ የአዋጁን አስፈላጊነት የተሳሳተ ነው።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ታወጀ። ምን ሊደረግ ነው? የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይገደባሉ። በኢህአዴግ ዘመን መቼስ የዴሞክራሲ መብቶች ተከብረው ያውቃሉ? ያልነበሩ መብቶች እንዴት ይታገዳሉ? በኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለ25 ዓመታት ፀንቶ ቆይቷል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅ አንድምታው፡ ተከብሮላቹ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ መብታችሁን ለግዜው ሊገደብ ይችላል ማለት ነው። መቼ ተከብሮልን ያውቃል? ዴሞክራሲያዊ መብታችን ኮ ሁሌ እንደተገደበ ነው። ሁሌ የአስቸኳይ ግዜ እንደታወጀብን ነው።
  አሁን በአዋጁ ሊገደብ የሚችል ዴሞክራሲያዊ መብት ቢኖረን ኖሮ እንዴት ይህን ያህል ኢህአዴግ እንቃወም ነበር? የዴሞክራሲ መብት ቢከበር ህዝባዊ ተቃውሞስ መቼ ይኖር ነበር? ህዝብ ተቃውሞውን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ቢከበርለት ኖሮ እንዴት ያምፅ ነበር? ዴሞክራሲ ሰፍኖ ህዝብ ያለ ምንም ተፅዕኖ የፈለገውን መርጦ ድምፁ ተከብሮለት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ቢከናወን ኖሮ መቼ ህዝባዊ ዐመፅ ይኖር ነበር?
ህዝቡኮ የሚቃወመው ዴሞክራሲያዊ መብቱ ስለተከለከለ ነው። ስለዚህ ህዝቡ አሁን በአዋጁ ምክንያት የሚያጣው ዴሞክራሲያዊ መብት የለም። ምክንያቱም ከአዋጁ በፊትም ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተነፍጎ ነበረ። የዐመፁ መንስኤም የዴሞክራሲ እጦት ነውና።
ስለዚህ አሁን አልነበረውም፡ አይቀነሰውም። ህዝቡ እየተቃወመ ያለው ዴሞክራሲያዊ መብቶች ባልተከበሩበት ነው። ህዝቡ ያመፀው ኢህአዴግ እስካሁን የሐይል እርምጃ ስላልወሰደ አይደለም። ህዝቡ እየተጨፈጨፈ ነው እየተቃወመ ያለው። ከአዋጁ በፊትም ጭፍጨፋ አለ፤ ከአዋጁ በኋላም ጭፍጨፋ ይኖራል።  አዋጅ የሚያመጣው አዲስ ክስተት የለም። ምክንያቱም ለ25 ዓመታት ሙሉ የኖርነው  በተደነገገው ህገመንግስት ሳይሆን ባልታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ነበር፤ አሁን ደሞ ታወጀ። ልዩነቱ የማወጅና ያለማወጅ ነበር።
በዚህ አዋጅ አዲስ ነገር ካለ ኢህአዴግ መጨናነቁና ለህዝባዊ ተቃውሞው እውቅና መስጠቱ ብቻ ነው። ህዝባዊ ተቃውሞው ከኢህአዴግ ቁጥጥር ስር መውጣቱና ጣዕረ ሞት ላይ መሆኑ ያሳያል።
የችግሩ መፍትሔ ግን የአስቸኳይ ግዜ ማወጅ ሳይሆን ስልጣንን ለባለቤቱ ህዝብ ማስረከብ ነው። ስልጣንን በክብር ለህዝብ ከመስጠት ይልቅ ስልጣንን በኃይል እስክትነጠቅና ተገፍትረህ እስክትባረር ድረስ መጠበቅን የመሰለ አላዋቂነት የለም።
ኢህአዴግ ያለው ዕድል ስልጣኑን በኃይል ሳይነጠቅ በፍቃደኝነት ለህዝብ ማስረከብ ብቻ ነው።
It is so!!!
Filed in: Amharic