>

እምየ አንዳርጋቸው ፅጌ የማን “ዕዳ” ነው?!!! (መስከረም አበራ)

የሃገራችን ፖለቲካ ዕድለ-ቢስ የሚባል አይነት ነው፡፡የፖለቲካችን ሰፌድ እንጉላዩን ወደ ፊት ምርቱን ወደ ታች የሚቀብር ክፉ ልክፍት አለበት፡፡ ፖለቲካችን ፈውስ የራቀውም በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም! እንደ እኛ ባለው ተቋማዊነት በራቀው ኋላቀር ፖለቲካ ቀርቶ ተቋማዊነት በበረታበት ስልጡን ፖለቲካዊ ከባቢም ቢሆን የፖለቲካውን ልጓም የያዙ የግለሰቦች ስብዕና ለፖለቲካዊ ፈውስ ሁነኛ ግብዓት ነው፡፡ የሃገራችን ፖለቲካ ብዙም ባይሆኑ የእውነት ለህዝብ አስበው ራሳቸውን ረስተው አደገኛውን ጉዞ የሚያያዙ የእውነት ታጋዮች አላጣም፡፡አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሃገራችን ፖለቲካ አለመፈወስ የእውነት ከሚያሳስባቸው፣ልታይ ባይነት የማይነካካቸው የተግባር ሰዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን ፊተኛው ነው፡፡ አንዳርጋቸው የእርሱ ትውልድ ለመጭ ትውልድ ስራን ሰርቶ፣ጥርጊያን አመቻችቶ ያለመጠበቁ ወንጀል መስሎ ከሚሰማቸው ሰዎች መሃል እንደሆነ የሰጣቸውን ቃለምልልሶች፣ የፃፋቸውን ፅሁፎች አንብቦ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ይህ የአንዲ ልዩነቱ ነው!

አብዛኞቹ የአንዳርጋቸው ፅጌ ትውልድ ፖለቲከኞች በዘመናቸው ያጠፉትን ጥፋት ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ተተኪው ትውልድ በዘመናዊ ፖለቲካ ጎዳና ይጓዝ ዘንድ ምን መደላድል ፈጠርን የሚለውም እምብዛም  የሚያሳስባቸው አይመስልም፡፡አንዳርጋቸው ፅጌ ግን የእርሱ ትውልድ የተፈወሰ ፖለቲካ ለመጭው ትውልድ ያለማቆየቱ አጥንቱ ውስጥ ገብቶ ይሰማዋል! ‘ይሄ ሁሉ የደም፣የአካል ፣የስነልቦና ድቀት መስዕዋትነት ያስከፈለው የሃገራችን ፖለቲካ እንዲህ እንስሳዊ የጉልበት አካሄድ የተጠናወተው እንዴት ነው?’ ብሎ አጥብቆ እንደሚብሰለሰል በማያመልጡኝ ቃለ መጠይቆቹ ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ሰውየው የተግባር ሰው ነውና ይህን ህመሙን ይዞ መቀመጥን አልፈለገም! የእርሱን ወደ አረጋዊነት እየተጠጋ ያለ ጉልበት ቀርቶ የጎረምሳን ትክሻ ወደሚፈትን አስቸጋሪ እና አደገኛ   ስራ ሰተት ብሎ ገባ፡፡ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ በሚለው መፅሃፉ የገለፀው እና በግሌ አብዝቶ የሚገርመኝን ለፍትህ የመታገል ጉዞውን የጀመረው በህወሃት/ኢህአዴግ ቤት የነበረችው አጭር ቆይታ ከመጫኛ ረዝማበት በቃኝ ብሎ ከወጣ ጊዜ አንስቶ ነው! አንዳርጋቸውን ከኢህአዴግ ቤት ያበረረው ፣በእነሱ ዘንድም ክፉ ጥላቻን የተጠላው የአባቴ ቤት ሲዘረፍ አብሬ አልዘርፍም ማለቱ ነው! አብሮ ሊዘርፍ ቀርቶ ሲዘርፉ ማየት አቅለሽልሾት፣ፍርድ ሲጣመም መመልከት አልሆንልህ ብሎት፣የህውሃታዊያን የዘረኝነት ክርፋት አንገሽግሾት ነው ጥሎ ውልቅ ያለው፡፡ይህ ውሳኔው ሁሌም ልቤን የሚነካኝ፣ግዙፍ ስብዕናውን የሚመሰክርልኝ፣ልዕልናውን የሚያገዝፍብኝ ማንነቱ ነው!

“ሩቅ ሆኖ ከመውቀስ እስኪ ጠጋ ብየ ልያቸው የሚረዳ ነገር ካለም ልርዳ” ብሎ ነበር በፍፁም ከማይመጥኑት ሰዎች ጋር ሊሰራ የሞከረው፡፡የሆነ ሆኖ ውሃ ከዘይት ጋር እንደማይገጥም አንዳርጋቸውን የመሰለ ንፁህ ነፍስ እና ምጡቅ ግንዛቤ ያለው ሰው መተኮስ ብቻ ከሚሆንላቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ ሰዎች ጋር መስራት እንደማይችል እርግጥ ነው! እሱ በቅርብ እንዳያቸው እነሱም በውል አጢነውት ኖሮ እንደ ተከሰተ ሰይጣን ይፈሩታል፣እንደ አባት ገዳይ ይጠሉታል፡፡በሃሰተኞች መድረክ እውነተኝነቱ፣ በሆዳሞች ገበያ የመርህ ሰው መሆኑ፣ በበልቼ ልሙት ዘይቤ መጭውን ትውልድ ማሰቡ፣በአላዋቂዎች ማህበር ጥልቅ ግንዛቤው ወንጀል ሆኖበት እንደ ወንበዴ ተቆጠረ! ግንዛቤውን ልቀው ሊያታልሉት እንደማይችሉ፤እሱም እስከመጨረሻው አይቷቸዋልና እንደማይለቃቸው ስለሚያውቁ በጥርሳቸውም በጥፍራቸውም ሊበሉት ቆረጡ፡፡

ስራቸው እርሱን ማሳደድ ሆነ! እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ግዙፍ ተቋም ይቆጥሩታል፡፡ምጡቅ ሃሳቡ፣ጨዋ አንደበቱ፣ማራኪ ስብዕናው፣እውነተኛ ነፍሱ፣ቆራጥ አቋሙ፣ኩሩ ማንነቱ፣የተፈተነ የህዝብ ወገንተኝነቱ እልፎችን የማረከበት ውበቱ እንደሆነ ስለሚያውቁ አጥብቀው ይፈሩታል፡፡ከሚፈሩት በላይ ይጠሉታል!ጠመንጃ አንግበው አዲስ አበባ የመግባታቸውን ገድል አወድሰው የማይጠግቡ የትናንት ሸማቂዎች አማራጭ ሲያጣ የገባበትን የትጥቅ ትግል “ለሰይጣንነቱ” ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ፡፡

እንደዚህ ከአእምሮ በላይ በሆነ ጥላቻ እና ፍራቻ የሚያዩት፣ሊበሉት አሰፍስፈው ሲጠብቁ የኖሩት ሰው በጎደሎ ቀን እጃቸው ሲገባ ምን ሊያደርጉት እንደሚችሉ ማሰብ አልፈልግም! በዛች በእነሱ እጅ በገባባት ዕርጉም ቅፅበት እሱ ምን እንደተሰማው ማሰብም እንዲሁ በሽታ ላይ የሚጥል ነገር ነው!!!! መያዙን ስሰማ የተሰማኝ ስሜት በቃላት ልወክል ይቸግረኛል፤ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ሬሳ ቤቱ እንዳስቀመጠ ሰው ክፉ ስሜት ሰንብቶብኛል፤ ጥቅም አልቦነት፣ ደካማነት፣ክፉ የመጠቃት ስሜት፤እድለ-ቢስነት ሳይቀር ተሰምቶኛል!

አንዳርጋቸው ፅጌ በግሌ ልዩ ቦታ የምሰጠው ፖለቲከኛ ነው፤ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ረስቼው አላውቅም፡፡ በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ብዙ የማከብራቸው ሰዎች ቢኖሩም አንዳርጋቸው በብዙ እጥፍ ልቆ ይታየኛል፡፡ የተግባርም የንድፈ-ሃሳብም ሰው መሆኑ፣ብዙ የሃገራችንን ፖለቲከኞች የሚፈትነው ልታይ ባይነት፣ የወንበር ፍቅር የማይነካካው፣ለፊት ወንበር ከመሮጥ ይልቅ ከኋላ ያለውን ከጉተና የከበደ ሸክም ለመሸከም ትከሻውን የሚያበረታ ትሁት መሆኑ፣ከሚያወራው የሚሰራው መላቁ፣ጥልቅ ግንዛቤው፣ ቆፍጣና ማንነቱ፣እምቦቀቅላ ልጆቹን ጥሎ በስተርጅና ቀንበር ለመሸከም መቅደሙ፣ከለስላሳ አልጋ ወርዶ ሰሌን ላይ ለመተኛት ያስጨከነው የህዝብ ወገንተኝነቱ እጅግ አከብረው ዘንድ ግድ ያሉኝ ልዩነቱ ናቸው! አንዳርጋቸው ፅጌ የእርሱ ትውልድ ያጠራቀመውን የፖለቲካ እዳ በግለሰብ ትከሻው ተሸክሞ የትውልድን እዳ በግለሰብ አቅሙ ሊከፍል ሲማስን ጨቅላ ልጆቹን የማይችሉት ሰቀቀን ውስጥ፣ራሱን ሲኦል  የከተተ ጓደኛ አልቦ ሰው ነው!

አንዳርጋቸው የወለደ ሁሉ በሚያውቀው በልጆቹ ፍቅር፣ በራሱ ህይወት ላይ የጨከነው ለግል ጥቅሙ ብሎ ወይ ደግሞ ከዚህ ዘውግ ለተወለዳችሁ የወንዜ ልጆች ብሎ ወሰን ከልሎ አይደለም፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ያነገበው ከፍ ሲል ሰብአዊነትን ዝቅ ሲል የኢትዮጵያዊነትን እዳ ነው፡፡ስለዚህ ለአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት መታገል ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መወገን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ሁሉ ለአንዳርጋቸው ፅጌ መቆም አለበት፡፡ እስከ አሁን ባለው መረጃ አንዳርጋቸው ፅጌ ስለመፈታቱ የተባለ ነገር የለም፡፡ከሰው ተለይቶ እንደ መክፋፋቱ እንደ ሌላ ፍጡር የሚታይ ሰው ከመሆኑ አንፃር እንዲህ በቀላሉ እንደማይፈታም መገመት ከባድ አይደለም፡፡እስረኛ ሁሉ ተፈቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ባለቤት እንደሌለው እቃ እስርቤት ከቀረ ሽንፈቱ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እንጅ የሌላ አይደለም፡፡ ጥፋቱ የእኛ እንጅ የህወሃት አይደለም!

በሃገራችን የማይሰማ የለምና በጎሳ ፖለቲከኞች ዘንድ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ባለቤት፣ ህዝባዊ መሰረት (“Constituency”) የሌለው፣“ሲኒ ይሁን ጀበና” የማይታወቅ ነው ነገር ነው ተብሏል፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነትም የለም ይባል ተይዟል፡፡ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ክብር ነፍሱን የሰጠውን፣ክብሩን የጣለውን አንዳርጋቸው ፅጌን ባለቤት እንደሌለው ዕቃ ብቻውን እስር ቤት እንዲከረቼምበት ዝም ያልን ቀን ያኔ እውነትም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ባለቤት አልቦ ቅዤት እንደሆነ አስመስክረናል! ስለዚህ አንዳርጋቸው ፅጌን ከእስር ለማስፈታት መታገል ለአሸናፊው ሃሳብ፣ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን መቆም ነው፡፡

የሰሞኑ የሃገራችን ሁኔታ እንደሚያስረዳው እስረኛ የሚፈታው/የማይፈታው በጀርባው በቆሙት የትግል አጋሮቹ ብርታት/ድክመት ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲከኞች ቤታቸው ድረስ የሚሸኝ መኪና ታክሎላቸው የተፈቱት የወንዛቸው ልጆች ኮስተር ያለ ትግል ስላደረጉ ነው፡፡ማንም እስር ቤት መማቀቅ ስለሌለበት ይህ እሰየው የሚያስብል ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ ወቅት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ማንነት፣የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ርዕዮት ብርታት የሚታይበት የፈተና ወቅት ነው፡፡

ለሁላችን እንደሰው መቆጠር ነፍሱን ለሰጠ ሰው፣ የምንወዳትን ሃገራችንን ለማራመድ ከእባብ ጋር እየተያየ አፈር ላይ እስከመንከባለል ለጨከነ የተግባር ሰው፣ልጆቹን ነገሬ ሳይል፣ ለስላሳ ኑሮ ሳያማልለው ሁሉን ትቶ ሃገሬን ላለ ሰው ምን ብናደርግ ውለታውን ይመጥናል? እንዴት ብንጮህ ከሆነልን ጋር ይመጣጠናል? በአረመኔዎች ቤት እየተጋተ ያለውን መራራፅዋ የሚመጥን እንዴት ያለ ካሳ ነው? አንዳርጋቸው ፅጌ አይሆኑ የሆነለት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ነፍስ ዘርቶ ተንቀሳቅሶ ምልክቱ ሆነውን ትልቅ ሰው ማዳን ካልቻለ ሁሉም በየጎሳው ለመወሸቅ ጥሩ ምክንያት ይኖረዋል! በበኩሌ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ከምንም ምድራዊ ሃይል ገዝፎ፣ ልዕልናው ከምንም ጋር የማይወዳደር እሳቤ ሆኖ ይታየኛል፡፡

በዚሁ መስመር የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ የሚከተለው ርዕዮት በምክንያታዊነት ላይ የቆመ ስለሆነ በስሜት ገንፍሎ ሲናድ ስላልታየ እንጅ ትልቅ ጉልበት ያለው ሃይል መሆኑ አያነጋግርም፡፡የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እምነት ከዘውግ ተኮሩ ይልቅ ሩቅ የሚያስኬድ፣ዘመኑን የሚተካከል፣ሰውነትን የሚመጥን እንደሆነ አሌ የማይባል ነገር ነው፡፡ ሆኖም የእሳቤው ልዕልና በራሱ ተነስቶ የሚሰራው ስራ እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡አንድ የፖለቲካ ቡድን የሰለጠነ ሃሳብ ስለያዘ ብቻ አሸንፎ ይወጣል ማለት አይደለም፡፡ የያዘው ሃሳብ ተራማጅነት ከተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር ታጅቦ ስጋ እና ደም ካልለበሰ ሃሳቡ ብቻ የተፈለገውን መከናወን ሊያመጣ አይችልም፡፡ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን የምናቀነቅን ቡድኖች የሚጎድለን ይህ ነው – ተግባራዊ እርምጃ! ይህን ነገር አስመልክቶ ዶ/ር አብርሃም የተባሉ ምሁር በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርበው “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው የፖለቲካ ሃይል የአሸዋ ጭብጦ መሆኑን ማቆም አለበት፤ ሰብሰብ ብሎ አንድ ስራ መስራት አለበት እንጅ እንደአሸዋ ጭብጦ የተበታተነ መሆን የለበትም” ያሉት ትልቅ ንግግር ሃሳቤን ሁሉ የሚያስር አንኳር ነገር ይመስለኛል! ዛሬ ስራ የምንሰራበት፣ ማንነታችን የሚፈተሸበት ትልቅ ፈተና ፊታችን ተደቅኗል- የምልክታችን እምየ አንዳርጋቸው እጣፋንታ በእኛ በምናከብረው ወገኖቹ ተነስቶ መስራት እና አለመስራት ቀጭን ክር ላይ ተንጠልጥላለች!

ውድ ነፍሱን የሸጠልን፣ እምቦቀቅላ ልጆቹን በትኖ ሲኦል የወረደው አንዳርጋቸው ፅጌ ንፁህ ነፍስ የምትጠይቀን ቀላል ጥያቄ ጊዜ እና ትኩረት ብቻ ነው! የኮምፒተራችንን ኪቦርድ መነካካትን፣ቀናትን ወስደን ሰላማዊ ሰልፍን የማድረግን ያህል ከሙዝ መላጥ የቀለለ ስራ ነው! በበኩሌ የዚህን ንፁህ ሰው ነፍስ ለመታደግ ውጭ ውየ ባድር፣ እሱ በተንከባለለበት ትቢያ ብንከባለል፣ አመድ ነስንሶ የአለምን ጩኽት ሁሉ ቢጮህ ለውለታው አንሶ እንጅ ከብዶ አይታየኝም፡፡ እሱ ከእስር ወጥቶ በምስሉ ጣኦት ሰርተው እስከማቀፍ ለደረሱ ለጋ ልጆቹ እስኪደርስ ድረስ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመክፈል ማመንታት ውለታ ቢስነት ብቻ ሳይሆን ነገ በአንዳርጋቸው ጫማ ገብቶ ቀንበራችንን የሚሸከም የማጣት አደጋም አለው!

Filed in: Amharic