>

ታላቁ እስክንድር! እንደነእስክንድር አይነት ሰዎች ፍርሃትን ገድለውታል! (ዘውድአለም ታደሰ)

ይሄ እስክንድር የሚሉት ሰው ግን የምርም ታላቁ እስክንድር ነው! እውነተኛ የሐገር ፍቅር ስሜት ፣ እውነተኛ የመንፈስ ብርታት ፣ እውነተኛ የዴሞክራሲ ጥማት ፣ ሁሉም ነገር አለው! ኢትዮጵያ ውስጥ ከተነሱ የነፃነት ታጋዮች ልክ እንደነማርቲን ሉተር ኪንግ ከፍተኛ የሞራልና የጥንካሬ እርከን ላይ የወጡ ሁለት ሰዎች ጥራ ብባል ከሴት ርእዮት አለሙን ከወንድ ደግሞ እስክንድር ነጋን ነው ምጠቅሰው!!

ከአመታት በፊት ርእዮት ከእስር ስትፈታ በር ላይ ነበርኩ። ፊቷ ላይ የሚታየው በራስ የመተማመን ስሜትና የወህኒ ጠባቂዎቹ ፊት ላይ የሚታየው ቁጭት ገራሚ ነበር። በተደጋጋሚ የተለያዩ ማማለያዎች በማቅረብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ሲነገራት አሻፈረኝ ስትል ቆይታ ድንገት ከእስር እንደምትፈታ ሲነግሯት «ይቅርታ ጠየቀች ብላችሁ ከሆነ የፈታችሁኝ ተመልሼ እመጣለሁ!» ነበር ያለቻቸው። ገና እግሯ ከወህኒ እንደወጣ ነበር ትግሉን አጠናክራ እንደምትቀጥል በድፍረት ትናገር የነበረችው!!

ዛሬም እስክንድር ላይ ያየሁት ይሄን ነው! ገፁ ላይ ፍርሃት የሚባል ነገር አይነበብም! ይበልጥ ጉልበታምና ጠንካራ ሆኖ የወጣ ይመስላል! ተከብሮ ከሚኖርበት የሰለጠነ ሐገር ህዝቡን ብሎ ወደሐገሩ መጥቶ ይህን ሁሉ መከራ ቢያሳልፍም አሁንም የሚፈልገው የዴሞክራሲ ደመና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እስካልሰፈፈ ድረስ የሚቆም አይመስልም!

እንደነእስክንድር አይነት ሰዎች ፍርሃትን ገድለውታል! ነፍሳቸውን እስከሞት ድረስ አሳልፈው ሊሰጡ ስለቆረጡ የሰው ልጅ የሚፈበርከው ማንኛውም አይነት መከራ አያሸንፋቸውም! በየትኛውም ስቃይ መንፈሳቸው አይሰበርም! የነፃነት ታጋይና ፖለቲከኞችን ሚለያቸው ይሄ ነው። የነፃነት ታጋዮች የኔ የሚሉትን ህይወት እንደነብዩ ኤልሳ ሰውተው ነው ወደትግል ሚገቡት! ሞት ከመጣ እንደሶቅራጥስ እየሳቁ ለመጨለጥ ፣ ላመኑበት ነገር እንደክርስቶስ ለመሰቀል ዝግጁ ስለሆኑ እነሱን የሚሰብር ምድራዊ ሃይል የለም! ዛሬም ታላቁ እስክንድር ነጋ ላይ ያየሁት ይሄን ሃያል የነፃነት ታጋዮች መንፈስ ነው!!

Filed in: Amharic