>

የኦሮሞ ህዝብ ትግል ደረጃው ከፍ ብሏል!! (ደረጀ ገረፋ ቱሉ)

የኦሮሞ ህዝብ በደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ የትግል ደረጃውን ከፍ አድርጎ ሰቅሎታል።
1. የኦሮሞ ህዝብ በደሙ በክልሉ ላይ በአሁኑ ጊዜ የሚታዘዙትን እና የሱን ፍላጎት ብቻ የሚያስፈፅሙ አመራሮችን ወደ ፊት ለፊት ማምጣት ችለዋል።
2.  እነዚህ በህዝብ ትግል ወደ ፊት የመጡ አመራሮች ለኦሮሞ ህዝብ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃካይ ተስፋ ሆነዋል።በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን ለገጠማት ፈተና አንድ ተስፋ ካለ ይህው በኦሮሞ ህዝብ ትግል ወደ ፊት የመጣው የኦህዲድ አመራር እና የኢትዮጵያ ህዝብ አርቆ አሳብነት ነው።ህዝቡ አሁንም ድረስ ከጩሀት በዘለለ በትዕግስት እና በቀናዕነት ነገሮችን እየተከታተለ ነው።
3 . የኦሮሞ ህዝብ ባደረገው እልህ አስጨረሽ ትግል ዛሬ ኦሮሚያ ውስጥ ህዝቡ በመቶ ሺዎች ወጥቶ የተቀዋሚ መሪን እንደ ንጉስ የሚቀበልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።ዛሬ በኦሮሚያ የኦሮሚያ ፖሊስ ለተቀዋሚ መሪዎች ወንበር የሚያስተካክልበት እና እንደ ንጉስ አጅቦ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ።
4 . ዛሬ በኦሮሚያ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሀገራችን አስቸጋር ሁኔታ ላይ ስላለች ለተቀዋሚዎች የአብረን እንስራ ጥር እያቀረበ ተቀዋሚዎች በተራቸው ኮራ የሚሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።ዛሬ በኦሮሚያ ትሁት መንግስት እና ኩሩ (አዛዥ ) ህዝብ መፍጠር ተችሏል።
5.  ዛሬ በኦሮሚያ የክልሉ ፕረዝዳንት ለክልሉ ፀጥታ ኃይል ከህዝብ ጎን ቆሞ ህዝቡን ከጥቃት እንድከላከል ጥር የሚተላለፍበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
6.  ዛሬ በኦሮሚያ ዜጎች ከሚተሰሩበት ዜና ወደ በሺዎች የሚፈቱበት ዜና መሰማት ደረጃ ላይ ደርሰናል።
7 . ዛሬ በኦሮሚያ የኦሮሞ ህዝብ እራሱን በራሱ ያስተዳድር የሚለው መፈክር ወደ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ሀገርን በዲሞክራስያዊ መልኩ በቀዳምነት ያስተዳድር የሚል ዜና በመላው ሀገርቱ እየናኘ ነው።
8.  ዛሬ በኢትዮጵያ የኦሮሞ ህዝብ የሀገር መፍረስ ምልክት እና ስጋት ተደርጎ ሳይሆን የሀገር ተስፋ ተደርጎ እየታየ ነው።
9.  ዛሬ ኦሮሚያ የዜጎች ስቃይ ካምፕ ሳይሆን የነፃነት ደሴት ተደርጋ እየተቆጠረች ነው።
10.  ዛሬ የኦሮሚያ ሚዲያ አፋኝ ሚዲያ ሳይሆን የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት ተቋም በመሆን በኢትዮጵያ ደረጃ የህዝብ ድምፅነቱ እየተረጋገጠ ይገኛል።
11.ዛሬ በኦሮሚያ ህዝብን የገደሉ ወገኖች የሚቀጡበት እንጂ የሚሸለሙበት አይደለም።
12 . ዛሬ በኦሮሚያ ያለ ምንም እርዳታ በራስ አቅም ብቻ በሚለየን የተፈናቀሉ ወገኖች የሚቋቋሙበት ነው።ዛሬ በኦሮሚያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በአንድ ጊዜ 30,000ቤቶች እየተገነቡ ያለበት ክልል ነው።
ይህ ሁሉ የሆነው በነፃ ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ደም ነው።ይህ ውጤት ደም ተገብሮበታል።
ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ክልል ፣ይህንን ሁሉ በራሱ ደም ያስመዘገበን ህዝብ በህቡዕ የቤት ውስጥ መቀመጥ እና የስራ ማቆም አድማ መጥራት ይህንን ህዝብ አይመጥነውም።
ይህ ህዝብ ዛሬ ከፈለገ ያለ ምንም መሸማቀቅ በአንድ ቀን ተጠራርቶ የክልሉን መንግስት ከጎኑ በማሰለፍ በሚልዮኖች በሰላም ወጥቶ ጎዳናዎችን ማጥለቅለቅ ይችላል።
ስለዚህ ጥቃቅን እና አነስተኛ የህቡዕ የአድማ ጥሪዎች ለኦሮሞ ህዝብ ከደረጃው በታች ናቸው።የኦሮሞ ህዝብ ዛሬ ከማነው ተደብቆ ቤቱ የሚቀመጠው? ስለዚህ እሄንን መረዳት እጅግ ወሳኝ ነው።

Filed in: Amharic