በዚህ ዓመት መስከረም ወር ላይ በአሜሪካን ሀገር የዋሽንግተን ዲሲ በነበረኝ የአንድ ሳምንት ቆይታ የታዘብኳቸውን ነገሮች በፎቶ አስደግፌ “እንሆ በረከት” ልላችሁ ወደድኩ። በዚህ ፅሁፍ የማቀርበው በግሌ የተሰማኝንና የታዘብኩትን እውነት ብቻ ነው፡፡ እንደምትወዱት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
“IN THIS TEMPLE AS IN THE HEARTS OF THE PEOPLE FOR WHOM HE SAVED THE UNION THE MEMORY OF ABRAHAM LINCON IS ENSHRINED FOREVER”
በግሌ አብርሃም ሊንከንን በጣም አደንቀዋለሁ። ስለ እሱ ለማወቅ ካለኝ ጉጉት የተነሳ ለፕረዜዳንትነት ሲመረጥ ያደረገው ንግግርን ሳይቀር አንብቤያለሁ። የፅሁፉ ጥልቀት የፖለቲካ ፍልስፍና እንጂ በፍፁም በፕረዜዳንትነት ሹመተ-በዓል ላይ የቀረበ ንግግር አይመስልም። ለአብርሃም ሊንከን ካለኝ አድናቆት በተጨማሪ አሜሪካ መሄዴን አመኖ መቀበል ለከበዳቸው አንዳንድ ወዳጆቼ ማስረጃ ይሆን ዘንድ እኔም ከሃውልቱ ፊት ቆሜ የተነሳሁትን ፎቶና በአደራሹ አንድ ጥግ የተመለከትኩት የፕረዜዳንቱን ምስል እንሆ…
ኢትየጲያዊያን ግን የአፄ ሚኒሊክን ስም እያነሱ፤ ግማሾቹ እንደ ሰይጣን ሲረግሙት፣ ሌሎቹ እንደ ጣዖት ሲያመልኩት፣ የተቀሩት በማን-አለብኝነት ሰምተው እንዳልሰማ ሲያልፉት ይውላሉ። የሀገሪቱን መስራች ከመስማት ይልቅ አፅሙን መቀስቀስ፥ ሃውልቱን ማፍረስ ያሰኘናል። ለታሪክ ከመማር ይልቅ የቀድሞውን ታሪክ በራሳችን ግንዛቤ ልክ መፃፍ ያምረናል። ታሪክን ማወቅ፣ እውነትን መገንዘብ ተስኖናል። በዚህ ምክንያት የሀገር ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ ጠፍቶብናል።
ከሊንከን ሜሞሪያል እንደወጣን ፓክስታናዊቷን ወዳጃችንን መፈለግ ጀመርን። ምክንያቱም የሊንከን ሜሞሪያል በከፍተኛ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን ከላይ በፎቶው ላይ እንደምታዩት ደረጃዎቹ ትላልቅ ናቸው። የዕለቱ አየር በጣም ሞቃታማ ስለነበር ፓክስታናዊቷ ወዳጃችን በጣም ደክሟት ነበር። በዚያ ላይ ቅድም እንዳልኳችሁ ከእኔ የባሰች ወፍራም ናት። በዚህ ምክንያት፣ ትላልቆቹን ደረጃዎች በመውጣት ወደ አዳራሹ ውስጥ መግባት አልቻለችም ነበር። በመጨረሻ ከአንዱ ጥግ ቁጭ ብላ ሲጋራ ስታጨስ አገኘናትና ወደ ኮሪያ የጦር ሜሞሪያልን ለመጎብኘት ሄድን።
ኮሪያ የጦር ሜሞሪያል እየሄድን ሳለ አስጎብኚያችን ስለ ኮሪያ ጦርነት ብዙ ነገር ማውራት ጀመረ። ብዙ ሀገራት ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያዎች ወረራ ለመታደግ ለከፈሉት መስዕዋት ክብር ሲባል የተገነባ ማስታወሻ እንደሆነ ተናገረ። በመቀጠል የሀገራቱን ስም ዘረዘረና ኢትዮጲያን ዘለላት። ታሪኩን በደንብ ያውቅ እንደሆነ ስጠይቀው በልበ ሙሉነት “በደንብ አውቀዋለሁ!” አለኝ። ከዛ “ታሪኩን በደንብ የምታውቅ ከሆነ ኢትዮጲያን ለምን ዘለልካት?” ብዬ በለበጣ ጠየቅኩት። “ኧረ በጭራሽ…ኢትዮጲያ የለችበትም” አለኝ። አለማወቁ ሳያንሰስ እርግጠኝነቱ አበሳጨኝና “ባክህ ስለማታውቀው ነገር ዝም ብለህ አትቀባጥር” አልኩት። ይባስ ብሎ “ይኸው ደርሰን የለ… አይተህ ማረጋገጥ ትችላለህ!” አለኝ።
እኔና እሱ ደግሞ በእልህ ወደ ኮሪያ የጦር ሜሞሪያል በጥድፊያ መራመድ ጀመርን። ሁለቱን ሴቶች ጥለናቸው ሄድን። የኮስታሪካዋ ቆንጆ ግን ከኋላችን ቱስ..ቱስ እያለች ነው። ልክ ከቦታው እንደ ደረስን የሀገራት ስም የተፃፈበት ጡብ ላይ አፈጠጥን። በእንግሊዘኛ ፊደል ተራ ቅደም ተከተል “Denmark” ይልና “Ethiopia” ይላል።
“OUR NATION HONORS HER SONS AND DAUGTHERS WHO ANSWERED THE CALL TO DEFENED A COUNTRY THEY NEVER KNEW AND A PEOPLE THEY NEVER MET. 1950. KOREA. 1953” KOREA WAR MEMORIAL, WASHINGTON DC, USA
ፅሁፉን ደግሜ-ደጋግሜ ሳነበው የሀገራችን የኮሪያ ዘማቾች በዓይነ-ህልናዬ መጡ። እነዚህ የሀገሬ ዘማቾች በአንድ ወቅት ከማያውቁት ሀገር እና በአካል ከማያውቁት ሕዝብ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለሰዎች ነፃነትና እኩልነት መስዕዋት ከፍለዋል። አሁን ያሉት የሀገራችን ወታደሮች በሁለት አመት ውስጥ ብቻ ከ1200 በላይ ንፁሃን የሀገራቸውን ዜጎች እንደ ጠላት ጦር በጥይት ተኩሰው ገድለዋል። ለማያውቁት ሀገርና ሕዝብ መስዕዋት ከመሆን የራስን ሕዝብ መስዕዋት ወደ ማድረግ ከመሸጋገር ይልቅ ወታደሮቹን እንደ ወራሪ ጦር ሰራዊት ማየት የሚቀል ይመስለኛል። በእርግጥ በዚህ አመት ብቻ በአምቦ፥ ጨለንቆ፥ ወልዲያ፥ ቆቦ፥ ሲሪንቃ፥… በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና ጭፍጨፋ ለተመለከተ “የውጪ ሀገር ወራሪ ጦር ቢሆንስ ከዚህ በላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?” ያሰኛል።