>
5:14 pm - Thursday April 20, 4017

ኦሕዴድ የለጋት ኳስ የት ታርፍ ይሆን?(መስፍን ነጋሽ)

ድርጅቱ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስተናገደ የሚፈልግ ይመስላል። ጋባዥ ምልክቶችን እያሳየ ነው። ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፣ ኦሕዴድ እያደረገ ያለውን ለውጥ ችላ ማለት አይቻልም። ድርጅቱ ፖለቲካውን የሚገልጽበት መንገድ በግልጽ ተቀይሯል፤ ቢያንስ በአማርኛ በምንሰማው፣ በኦሮሚኛ የሚባለውን አላውቅም። ነገሩ ከቋንቋም አልፎ የፖለቲካ ትንተናና አረዳድ ለውጥን እያካተተ መምጣቱን በአድናቆትም፣ በትዝብትም፣ በጥርጣሬም እየተከታተልን ነው።

ተሳካላቸውም አልተሳካላቸውም ራሳቸውን ከህወሓት ዓይነ ጥላ ለማላቀቅ እየሞከሩ ነው። ሙከራው ራሱ እውቅና ሊቸረው የሚገባ ነው፤ በተለይ የመጣንበትን መንገድ ወደኋላ ዞር ብለን ስናየው፣ እንዲሁም ከፊታችን ያለውን አደጋ በዐይነ ሕልና ስንቃኘው። ለማ መገርሳና ቡድኑ፣ በቃል ከነገሩን አንኳር ጉዳዮች ለግማሾቹ ታማኝ ሆነው ከዘለቁ አገር ይጠቅማሉ። የሚጠብቃቸው ፈተና ግን ከህወሓት ብቻ አይሆንም። ብዙም ሳንቆይ እንደምናየው ሌላ ብሔረሰብን ካልኮነነና በጠላትንት ከሶ ደም ካላፈሰሰ ፖለቲካ የሠራ የማይመስለው ግሪሳ ይነሣባቸዋል። ይህ ለእነ መረራም የሚቀር አይደለም። ይህን በዋናነት በብሶት ትርክት የሚመራ ቡድን ለማስደሰት ብለው የተወሰኑ ስሕተቶችን መፈጸማቸው እንደማይቀር ብጠረጥርም፣ የኦሕዴድን ጅምር ንሸጣ ሳላበረታታ አላልፍም። ንሸጣ ሲከሽፍ ቱሽሽሽ ብሎ ይከስማል፣ ሰለሞን ዴሬሳ እንደሚለው።

የኢትዮጵያን ያለፈ ፖለቲካ በጨቋኝ-ተጨቋኝ ብሔረሰቦች ትንተና ከሚያሰላው የህወሓትና መሰል ድርጅቶች ባህል በማፈንገጥ፣ ጭቆናው መደብ ተኮር ነበር የሚለው መግለጫ ትኩረት የተቸረው ሆኗል። ለእኔ ትልቁ ነገር የመደብ ትንተና ትክክል ከመሆን አለመሆኑ ላይ አይደለም። ቁልፉ ለውጥ፣ የብሔር ጭቆና ትንተናና ትርክት ዴሞክራሲን ለመመስረት ቀርቶ አብሮ ተማምኖ ለመኖርም እንደማያስችል ግንዛቤ መወሰዱ ነው። የመደብ ትንተናውን ሳያስገቡት፣ የብሔር ጭቆና ትርክቱን አሁን ካለው የፖለቲካ ትንተና ቋንቋቸው ማስወጣታቸው በራሱም በበቃ ነበር። ትልቅ ለውጥ ነው። ጤናማ የፖለቲካ አየር ባለበት አገር ቢሆን፣ ኦሕዴድ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ቦታ የሚያስጠይቅ ሁሉ ነው።

የፖለቲካ ትንተናቸውንና ግባቸውን “ጨቋኝና ጠላት ብሔረሰብ አለብን/አለልን” ከሚል መነሻ የቀመሩት ህወሓትና ሌሎቹ ቡድኖች ይህን አጀንዳ ለጊዜው ካልሆነ ዝም ብለው እንደማያልፉት መገመት ይቻላል። ከመቀሌም ይሁን “ከሚኒሶታ” ቢያንስ የክህደት ክስ መሰማቱ አይቀርም። እናያለን።

በእግር ኳሷ ጋዜጠኞች ቋንቋ፣ ኦሕዴድ ኳሷን ጥሩ አድርጎ አሻምቷታል ልንለው እንችላለን። ኳሷ አሁንም ያለችው በኢሕአዴግ ሜዳ ነው። ኳሷ በመጨረሻ ረድፍ በሚቆመው፣ ጨዋታውን የሚመጥን ቴክኒካዊም ሆነ ስነልቦናዊ አቅም በሌለው ህወሓት እግር ስር ነች። መልሶ ወደ ኦሕዴድ እንደሚለጋት መጠበቅ ነው። ብአዴን ቀድሞ ላገባ ነው። የኅይለማርያም ድርጅት ኳስ አይወድም፤ አይጫወትም፣ አያይም። እንግዲህ ጨዋታውን እናያለን፤ ለኢትዮጵያ የሚያተርፈው ነገር እንዳለ።

Filed in: Amharic