>

የኦህዴድ አመራር ሁሉንም እንቁላሎቹን በአንድ ቅርጫት እንዳያስቀምጥ መምከር እንወዳለን (ያሬድ ጥበቡ)

 

ተኝቼም ተነሳሁ ። በ30 ዓመታት የስደት ዘመኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ትናንት ማታ አሜሪካ ውስጥ ተኝቼ ያደርኩት ። ሁሌም ራሴ ገና ትራሱን ሲነካ ጭው ብዬ ወደሃገሬ እገባለሁ ፣ ለመከራከር፣ ለማውጠንጠን፣ አንዳንዴም ወፌኢላላ ለመገረፍ ። የትናንት ሌሊት ግን ለየት ያለ ነበር። በኦህዴድ ውሳኔ እጅግ ከፍተኛ እርካታ ተሰምቶኝ ነበር ወደመኝታዬ ያመራሁት። እናም ስነሳ የት ቤት፣ የትኛው ክፍል እንዳደርኩ እንኳ ለጥቂት ጊዜ ግር እንደመሰኘት አደረገኝ። ለዚህ ነው አሜሪካ ተኝቼ አሜሪካ ነቃሁ ማለቴ ።

ከፈንጠዝያው ባሻገር ግን፣ እውን የኦህዴድ ዴሞክራሲያዊ ትልሞችና የወያኔ የአፈና እቅዶች ጎን ለጎን በሠላም ለረጅም ወራት መጓዝ ይችላሉን? የወያኔን የደም አበላ ታሪክ ለምናውቅ ይህን ጥያቄ ማንሳት የግድ ነው ። የትግራይ ነፃነት ግንባርን እንዋሃድ ብሎ አፍኖ የገደለ ድርጅት አሁን ማ ይሙት ኦህዴድ “በሃገር ውስጥም በውጪም ካሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እንሰራለን” ሲል ወያኔ ዝም ብሎ ይመለከታል? ወይስ የኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ዘጠኙም የኦህዴድ ሥራአስፈፃሚ አባላት ሲመጡ፣ ወያኔ በደቡብ ድርጅት ውስጥ ያለውን ሙሉ ተሰሚነትና፣ በብአዴን ውስጥ ያለውን መጠነኛ ድጋፍ ይዞ “የኦህዴድ አመራር ከድርጅታችን መርሆዎች አፈንግጦ በኤርትራ ከሚገኙ ጠላቶቻችን ጋር ‘በጉድኝት‘ እሰራለሁ በማለቱ ከፍተኛ አመራሩ በእስር ላይ እንዲቆይ ወስነናል” ቢል ማን ነው የኦህዴድን አመራር ከእስር ሊያስፈታው የሚችለው? የኦሮሞ ቄሮ እንል ይሆናል? ቄሮስ ቢሆን ይችላል ወይ ነው ጥያቄው ።

ለኢህአፓ ድጋፍ የነበራቸው የደርጉ አባላት ፣ እነ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ሻምበል ሞገስና መቶ አለቃ አለማየሁ ከህዳር 1969 ዓም ጀምረው የመንግስቱ ኃይለማርያምን ሥልጣን የሚገድቡ ተከታታይ ህጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጀምራሉ ። ሻለቃ መንግስቱን ከስልጣን ለማወረድ ወይም ደርጉን በመንግስት ግልበጣ ለመለወጥ አላቀዱም ። ሆኖም ሥልጣኑ እየተሸረሸረ የመጣው መንግስቱ አሜን ብሎ ሊቀበል አልቻለም ። ስለሆነም የካቲት ሶስት ቀን ለስብሰባ የደርጉ አባላት እንደተለመደው እየተፈተሹ ወደስብሰባው አዳራሽ ከገቡ በኋላ፣ መንግስቱና ደጋፊዎቹ እነጄኔራል ተፈሪ በንቲን በመትረየስ ቆልተዋቸዋል ። መንግስቱ ኃይለማርያም ያን ማድረግ የቻለው የፀጥታ ሐይሉ ላየ የነበረውን ቁጥጥር ተጠቅሞ ነው ። ልክ በ41 አመቱ ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ምን መከላከያ አለ?

ዛሬም እንደዛሬ 41 አመት በፊቱ መከላከያውና ፀጥታው ወይም ደህንነቱ በወያኔ እጅ ነው ። ዛሬም እንደዛሬ 41 ዓመቱ የኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ለስብሰባ ሲገቡ ፈትሾ የሚያስገባቸው ወያኔ ነው። ወደ አዳራሹ ካስገባቸው በኋላ ልክ እንደዛሬ 41 ዓመት በፊቱ እጅ ወደላይ እያለ እንዳያስራቸው ወይም “በሰላም እጃቸውን አልሰጥ ሲሉ በተኩስ ልውውጥ መሃል ሞቱ” የሚለ መግለጫ ጌታቸው አሰፋ ወይም ደብረፅዮን ቢሰጡ የሚከለክላቸው ማነው? ለምሳ ሲያስቡን ቁርስ አደረግናቸው ብለው ቢፈክሩ ማን ይከለክላቸዋል?

አንድ ሊቀርብ የሚችለው ክርክር ወያኔ እንዲህ ዓይነት ግፈኛ እርምጃ ወስዶ ቄሮውና የኦሮሚያ የፀጥታ ሃይላት በሚወሰዱት የአፀፋ ምት ይበልጥ የሚጎዳው ወያኔና የድጋፍ መሠረቱ በመሆናቸው፣ ወያኔ ከእንዲህ ዓይነት እብደት ለመታቀብና በመለወጥ ላይ ካለው ኦህዴድ ጎን በሰላም ለመኖር ይገደዳል የሚል ይመስለኛል ። ይህ ክርክር የራሱ ጥንካሬ ቢኖረውም፣ ወያኔ የሚመጣውን ሪስክ ለመቀበል እስከፈቀደ ድረስ አያደርገውም ብሎ መቀበል ከባድ ይመስለኛል ።የኦህዴድ መሪዎች እነዚህን ጉዳዮች መርምረው በጥንቃቄ ይራመዳሉ ብሎ አለማሰብ ቢከብድም አማራጭ ማቅረቡም ቀላል አይደለም።

በኢህአዴግ ውስጥ የተጀመረው ውስጠ ዴሞክራሲያዊ ግፊት ኦህዴድ በቀደደው ፈር ከመሄድ ውጪ አማራጭ የለውም ። ይህ ፈር ግን ከነቀዘው የወያኔ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ማፊያ የሚደቀንበት አደጋ ቀላል አይደለም ። በትንሹ ደረጃ እንኳ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ለዓለም ካወጀ በኋላ አሁንም እነበቀለ ገርባንና እስክንድር ነጋን የመሰሉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የህሊና እስረኞችን በእስር በማማቀቅ ላይ ይገኛል። እንደ ኦህዴድ ፍላጎት ቢሆን እነዚህ እስረኞች ከዶክተር መረራ ጋር በተፈቱ ነበር ። ሆኖም ኦህዴድ ፍላጎቱን ማስፈፀም አልቻለም ። አሁንስ የወሰናቸውን መጠነሰፊ ዴሞክራሲያዊና ወቅታዊ ውሳኔዎች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻለዋል ። ለምሳሌ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ለኦህዴድ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል ። ዶክተር ዲማና አቶ ሌንጮ ለታ ለመነጋገር ወደ አዲስአበባ መምጣት ቢፈልጉ፣ ኦህዴድ በምን መንገድ ነው በሰላም ገብተው መወያየት እንዲችሉ ማድረግ የሚችለው? የአውሮፕላኑ ታርማክ ድረስ ቀይ ስጋጃ አንጥፎ በወያኔ ደህንነት ሳይፈተሹ በቪ አይ ፒ በር ያስገባቸዋልን? ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው። አንድ ጉዳይ ግን ግልፅ ነው ። የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሃይሎችና፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊስት ማፊያዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚፈልጉ ሃይሎች ለረጅም ጊዜ በሰላም ጎን ለጎን መኖር አይችሉም ። አንደኛቸው መሸነፍ ይኖርባቸዋል ። የዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሃይሎች እንዲያሸንፉ እንመኛለን፣ ግን እንዴት?

ለዚህኛው ስትራተጂካዊ ጥያቄ መልስ እስክናገኝለት ድረስ፣ የኦህዴድ አመራር ሁሉንም እንቁላሎቹን በአንድ ቅርጫት እንዳያስቀምጥ መምከር እንወዳለን ። በቀላሉ ተኪ የማይገኝላቸው እንደ ለማ መገርሳ ያሉ መሪዎች ወደ ኢህአዴግ ሥራአስፈፃሚ ስብሰባ እንዳይሄዱና የክልሉን ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች አቅም ግንባታ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ማድረግ አንድ ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው ። በተጨማሪም የህዝብ ተወካዮች ምክርቤትን የሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት የሚመከርበት ተቋም እንዲሆን፣ ደካማና ብቁ ያልሆኑ አባላት ባሉባቸው ወረዳዎች አዲስ ምርጫዎች በማካሄድ ፖርላማውን ማጠናከር ሌላው ይመስለኛል ። ከሁሉም በላይ ግን ወያኔ በደህንነቱ መዋቅር ላይ ያለው የበላይነት የሚናድበትንና፣ ወያኔ እወክለዋለሁ ከሚለው ህዝብ ቁመና ጋር የሚመጣጠን ሚና እንዲኖረው የሚያስገድዱ ርምጃዎች ላይ በልዩ ትኩረት መስራት አማራጭ የሌለው ነው ። አይዞን!

Filed in: Amharic