>

"አድዋ የዓለም ታሪክ እንጂ የሁለት ሀገራት የጦርነት ወሬ አይደለም" (ስንታየሁ ሀይሉ)

እ.ኤ.አ መጋቢት1 ቀን 1896 ዓ.ም በኢትዮጵያ፤ አድዋ አቅራቢያ አፍሪካዊ ጦር በነጭ አውሮፓዊ ጦር ላይ ደማቅ ድል ያስመዘገበበት ዕለት ነበር። ይህ ድል የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ህልም በማክሸፍ በአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት ተስፋፊነት ዘመን ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ነፃ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።

የአድዋ ድል የአውሮፓውያን አፍሪካን የመቆጣጠር እርግጠኝነት ላይ ትልቅ ጥያቄ ምልክት የጣለ ነበር። ለዚህም ድሉ የአፍሪካ ጦር የአውሮፓን ጦር የደመሰሱበት ብቻ ሳይሆን ጥቁሮች ከነጮች ጋር በመፋለም ታሪካዊ የበላይነትን ያስመዘገቡበት ጭምር ነው።

አድዋ የዓለምን ተለምዷዊ ስርዓት የቀየረ ታሪክ በመሆኑ የሁለት ሀገራት ጦርነት ብቻ አልነበረም። በአድዋ የተነሳ በአፍሪካ የነበረው የነጭ አገዛዝ ከ50 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በማክተሙ ድሉ ለጥቁር አፍሪካ መለያ የሆነ ድል ነበር።

የአድዋ ድል አውሮፓን የዓለም ፖለቲካ እና ዘረ ልዕለ-ኃያል ከመሆን ያስቆመ ብቸኛው አጋጣሚ ነበር። ከአድዋ በፊት ባሉ ዓመታት በርካታ የአውሮፓ እና አሜሪካ ጋዜጦች መላውን ጥቁር አፍሪካ በአውሮፓውያኑ ሙሉ ቁጥጥር ስር የሚሆንበት ቀን መቃረቡን ይፅፉ ነበር። የአሜሪካኑ አትላንታ ኮንስቲቲውሽን (Atlanta Constitution) ጋዜጣ የሚከተለውን ፅፎ ነበር።

“መላው አፍሪካ በአውሮፓ መንግስታት ቅርምት የምትጠናቀቅበት ቀን ቀርቧል። አውሮፓውያኑ በአሜሪካ ያሳኩትን የዘር የበላይነት በአፍሪካ ለመድገም ተዘጋጅተዋል። በአሜሪካ ቀይ ህንዶችን በማስወገድ ለራሳቸው ዝርያ መኖሪያ መፍጠር የቻሉበትን ብቃት በአፍሪካ ለመድገምም የጥቁር አፍሪካ ዝርያዎችን በቅርበ ማጥፋት ይጀምራሉ።”

ይህንን የመሳሰሉ የነጭ የዘር እና የፖለቲካ ስብከቶች በዝተው ነበር። ይህ የዘረኝነት እና የተስፋፋ በላይነት ህልም ያከተመው አድዋ ላይ ነው። በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ አክትሞ የጥቁር ዘር እኩልነት ከመረጋገጡ መቶ ዓመታት በፊት አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን የነጭ አውሮፓውያንን የበላይነት በመስበር የጥቁር እኩልነትን አረጋግጠዋል።
አድዋ አንዲት አፍሪካዊት ሀገር ከወራሪ ጋር በመታገል ነፃነቷን ያወጀችበት ታሪካዊ ሚስጥር ነው። ለበርካታ ቅኝ ተገዢዎች በራስ የመተማመን ጉልበትን በመስጠት የዘመናት ጥርጣሬያቸውን የገለጠላቸው እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የታሪክ ዑደትን በተለየ አቅጣጫ የሚቀጥልበትን የጨዋታ ህግ ለዓለም ያስተዋወቀ እውነታ ነው።

ዋቢ- አፄ ሚኒልክና የአድዋ ድል

Filed in: Amharic