>

ህወሓት/ኢህአዴግን ለማስወገድ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ ማድረግ! (ስዩም ተሾመ)

ባለፉት አስር አመታት የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስትን እንቅስቃሴ በጥሞና ሲከታተል ለነበረ ሰው መንግስታዊ ስርዓቱ አሁን ያለበትን ደረጃ በግልጽ መገንዘብ ይችላል። ባለፉት ሁለት ሀገራዊ ምርጫዎች ገዢው ፓርቲ 99.6% እና 100% “አሸነፍኩ” ብሎ ማጭበርበሩ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የሰፈነበት ፍፁም አምባገነን (totalitarian) የሆነ መንግስት መፈጠሩን ያረጋግጣል። በተለይ ባለፉት ሦስት አመታት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የታየውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ከወሰደው እርምጃ አንፃር ጨካኝ አምባገነን (tyrant) እንደሆነ በግልፅ መገንዘብ ይቻላል። ታዲያ እንዲህ ያለ ጨካኝና ጨቋኝ የሆነ አምባገነናዊ ስርዓት እንዴት መቀየር ወይም ማስወገድ ይቻላል?

“በስልጣን ላይ ያለ መንግስት እንዴት መቀየር ወይም ማስወገድ ይቻላል?” የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ በቅድሚያ የመንግስታዊ ስርዓቱን ልዩ ባህሪ በግልፅ መገንዘብ ያስፈልጋል። “ህወሓት እና ፍርሃት፡ ከቀበሌ እስከ መቀሌ” በሚለው ፅሁፍ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በተለይ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ ፍፁም ጨካኝና ጨቋኝ እንደሆነ ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በተሳሳተ ሃሳብና አመለካከት የሚመራው የፖለቲካ ቡድን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣኑን ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ ያስከተለው ያልተጠበቀ ሽንፈት ነው። የ1997ቱ ምርጫ ያስከተለው ያልተጠበቀ ሽንፈት ህወሓት/ኢህአዴግን ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም አሳጥቶታል።

በሕዝብ ምርጫ ከስልጣን የተወገደ የፖለቲካ ቡድን ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፥ ከነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች፥ ሲቪል ማህበራትና በጎ-አድራጎት ድርጅቶች፥ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች፥ ዓለም-አቀፍ ድርጅቶችና የውጪ ሀገር መንግስታት ጋር ትብብር መፍጠር አይችልም። ከሁሉም በላይ ደግሞ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት፥ ቅቡልነት (legitimacy) አይኖረውም። አንድ የፖለቲካ ቡድን ከእነዚህ አካላት ጋር ትብብር መፍጠር ካልቻለ የፖለቲካ ስልጣኑንና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሙን ያጣል። በዚህ መልኩ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በትብብር የመስራት አቅሙን የተገፈፈ የፖለቲካ ቡድን ሕልውናው ያከትማል። በመሆኑም የፖለቲካ ቡድኑ አቅመ-ቢስነት በአባላቱና ደጋፊዎቹ ላይ ፍርሃት ይፈጥራል። በተመሳሳይ “Hanna Arendt” ፍርሃት (fear) አቅመ-ቢስነት ያስከተለው ተስፋ መቁርጥ እንደሆነ ትገልፃለች፡-

“Virtue [or Equality] is happy to pay the price of limited power for the blessing of being together with other men; fear is the despair over the individual impotence of those who have refused to “act in concert.” Fear as a principle of action is in some sense a contradiction in terms, because fear is precisely despair over the impossibility of action.” On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስራ ሦስት አመታት ውስጥ በመጀመሪያ ወደ ፍፁም አምባገነንነት (Totalitarianism)፣ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ጨካኝ አምባገነንነት (Tyranny) የተቀየረው የ1997ቱ ምርጫ ሽንፈት ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ትብብር ለመፍጠር አቅመ-ቢስ ስላደረገው ነው። በዚህ መሰረት፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ወደ ጨካኝ አምባገነንነት የተቀየረው ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም በማጣቱ ምክንያት ነው። ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም ማጣት የሚያስከትለው ተስፋ መቁረጥ ደግሞ ፍርሃት ያስከትላል።

“ፍርሃት” (fear) ምንም ማድረግ አለመቻል፤ የተለየ፥ የተሻለ ወይም አዲስ ሃሳብ ማጣት፣ ፍፁም አቅም-ቢስ መሆን የሚፈጥረው ስጋት ወይም የ”Hanna Arendt” አገላለፅን በቀጥታ ለመጠቀም – “anxiety of utter helplessness, without recourse to action” ነው። በመሆኑም፣ በፍርሃት መርህ የሚመራ የፖለቲካ ቡድን የተለየና የተሻለ ነገር ለመስራት ወይም ደግሞ አዲስ ነገር ለመፍጠር የሚያስችል አቅም የለውም። ሆኖም ግን፣ በራሱ ምንም ነገር ማድረግ ወይም መፍጠር የማይችል የፖለቲካ ቡድን በስልጣን ላይ ለመቆየት የግድ አንድ ነገር ማድረግ አለበት። ይኸውም፣ የሌሎች ፖለቲካ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መግታትና በሕዝቡ ዘንድ ምንም ዓይነት የተለየ የፖለቲካ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖር ማድረግ አለበት።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የህወሓት/ኢህአዴግ በፀረ-ሽብር ሕጉ፣ የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ፣ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማስተጓጎል፣ ይዘቶቹን በመቆጣጠር፣… የተደራጁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ነፃና ተደራሽ ሚዲያዎች፥ ጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾችን ለእስር፥ ስደት፥ እንግልትና ሞት በማድረግ፣ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕብረት መመሪያ በማውጣት አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎችን አጥፍቷል፣ በዜጎች ዘንድ ምንም ዓይነት የተለየ የፖለቲካ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖር ለማድረግ ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል። በዚህ መሰረት፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በፍርሃት መርህ የሚመራ ጨካኝና ጨቋኝ አምባገነናዊ መንግስት መሆኑን በግልፅ መረዳት ይቻላል። ስለዚህ እንዲህ ያለውን መንግስት እንዴት መቀየር ወይም ማስወገድ ይቻላል?

በመንግስታዊ ስርዓት ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ፈረንሳዊው ምሁር “Baron de Montesquieu” እንደ ህወሓት/ኢህአዴግ ያሉ ጨካኝና ጨቋኝ መንግስታት የሚወድቁት በውስጣዊ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ዴሞክራሲያዊና ዘውዳዊ መንግስታት ውጫዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በሚፈጥሩት ጫና ምክንያት በምርጫ ወይም በአመፅ ከስልጣን ሊወገዱ ይችላሉ። በተቃራኒው፣ ጨካኝና ጨቋኝ የሆነ አምባገነናዊ መንግስትን ማስወገድ ወይም መቀየር የሚቻለው ከውስጥ ነው፡-

“External circumstances cause the decline of other forms of government; tyrannies, on the contrary, owe their existence and survival to such external circumstances as prevent their self-corruption.” L’Esprit des Lois, Book VIII, ch.lO.

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ዴሞክራሲያዊ እና ዘውዳዊ መንግስታት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፥ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች፥ ሲቪል ማህበራትና በጎ-አድራጎት ድርጅቶች፥ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች፥ ዓለም-አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም የውጪ ሀገር መንግስታት በሚፈጥሩት የፖለቲካ ጫናና ግፊት ምክንያት ከስልጣን ይወርዳሉ ወይም ይወገዳሉ። በተቃራኒው ጨቋኝና ጨካኝ የሆኑ አምባገነን መንግስታት ደግሞ በእነዚህ ውጫዊ ኃይሎች እንቅስቃሴ ምክንያት ሕልውናቸው ይረጋገጣል፣ በስልጣን ላይ ያላቸው ቆይታ ይራዘማል። ውጫዊ የሆኑ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አምባገነናዊ ስርዓትን ከውድቀት ይታደጉታል። በሌላ አነጋገር፣ ጨቋኝና ጨካኝ የሆነ መንግስት ለውድቀት የሚዳረገው እነዚህን ውጫዊ ኃይሎች ከፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ሲያስወግድ ነው።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ጨቋኝና ጨካኝ የሆኑ መንግስታት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራው በፍርሃት መርህ ነው። ፍርሃት ደግሞ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል አቅም ማጣት ያስለተለው ተስፋ መቁረጥ ነው። በፍርሃት የሚመራ የፖለቲካ ቡድን በራሱ ምንም የተለየ፥ የተሻለ ወይም አዲስ ነገር መፍጠርና መስራት አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የተለየ ወይም አዲስ ነገር መፍጠር፥ የመንግስትን ሥራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉ የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል። በሕዝቡ ዘንድ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳይንፀባረቅ ያግዳል።

በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋለውን ክፍተቶችን የሚጠቁሙ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፥ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች፥ ሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች፥ ዓለም-አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች እና የመሳሰሉት ውጫዊ የፖለቲካ ኃይሎች ከሀገሪቱ ይጠፋሉ። በፍርሃት መርህ የሚመራ ጨቋኝ የሆነ አምባገነናዊ መንግስት እነዚህን ውጫዊ ኃይሎች ከሀገሪቱ ጠራርጎ ከአጠፋ በኋላ በስተመጨረሻ ራሱን በራሱ ማጥፋት ይጀምራል።

በዚህ መሰረት መንግስት በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የለውጥና መሻሻል ማነቆ ይሆናል። ዜጎች የተሻለ ነገር ለመስራት፣ አዲስ ነገር ለመፍጠር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት ይሆናል። ነገር ግን፣ በእውን እየሆነ ያለውን መገንዘብ ሆነ እውነቱን ተገንዝቦ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል አቅም አይኖረውም። በመሆኑም የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ችግር ተገንዝቦ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ብቃት፥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ሊኖረው አይችልም። ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት ሲጀመር በውስጡ የተሸከመው የፍርሃት ተውሳክ መንግስታዊ ስርዓቱን ራሱ ማፍረስ ይጀምራል። በድጋሜ ከ“Hanna Arendt” ሥራ ውስጥ የሚከተለውን ቀንጭበን ወስደናል፡-

“Fear has no self-transcending power and is therefore truly anti-political. Fear as a principle of action can only be destructive or “self-corrupting.” Tyranny is therefore the only form of government which bears germs of its destruction within itself.” On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

ራሱን በራሱ ከማጥፋት አንፃር የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ራሱን በራሱ ማጥፋት የጀመረው ውጫዊ ፖለቲካዊ ኃይሎችን ከሀገሪቱ ውስጥ ጠራርጎ ሲያጠፋ ነው። በ2008 ዓ.ም የነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ “ኢህአዴግ ራሱን በራሱ ለማጥፋት ወሰነ!” የሚል ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በነሃሴ 2007 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በተካሄደው የግንባሩ 10ኛ ጉባዔ ላይ የቀረበው ሪፖርት ነው።

በሪፖርቱ መሰረት፣ የፓርቲው ጀማሪና መካከለኛ አመራሮች የጥገኝነት አስተሳሰቦች እና የተቃዋሚዎች አጀንዳዎች አራማጅ ሆነዋል በማለት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ መጀመሩን ይገለፃል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ጀማሪና መካከለኛ አመራሮቹን ሥልጠና አጠናቀው ወደ መደበኛ ሥራቸው ከተመለሱ በኋላ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ያመጡትን ለውጥና ያልተሻገሩዋቸውን ጉዳዮች ለመለየት የሚያስችል የመስክ ምልከታ በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ግብረ መልስ በመስጠት ለውጥ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡-

“ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ጊዜ በአራት ዙሮች 16 ሺህ 166 ጀማሪና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ተሰጥቷል። ለመካከለኛና ጀማሪ አመራሩ ከተሰጠው ሥልጠና ሒደት ለመገንዘብ እንደተቻለው በተለይ በጀማሪ አመራር ደረጃ የሚገኙ አባሎችን በፖሊሲዎቻችን ላይ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ከመሆኑም በላይ የሚያነሱዋቸው ጉዳዮችም አንዳንዶቹ ከኪራይ ስብሳቢ ተቃዋሚ ኃይሎች አጀንዳዎች ብዙም ያልተለዩ ናቸው።…ይህ ችግር የጎራ መደበላለቅን ሁሉ አስከትሏል። ጠባብነትን፣ ትምክህትን እንዲሁም በሃይማኖት ሽፋን የሚደረግ አክራሪነትን ለመታገል አላስቻለም።”

በአጠቃላይ ህወሓት/ኢህአዴግ ራሱን በራሱ ማጥፋት የጀመረው ገና በ2006/07 ዓ.ም ነው። ዛሬ ላይ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የሚታየው መከፋፈልና መፍረክረክ ዋና መንስዔው የድርጅቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። በመሰረቱ በፍርሃት መርህ የሚመራ የፖለቲካ ቡድን በመጨረሻ ራሱን ያጠፋል። በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት የሚንቀሳቀሰው በፍርሃት መርህ ነው። ስለዚህ ፍርሃት ህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራበት ነፍስ ነው። ከፍርሃት በሽታ ሊድን የሚችልበት ቅንጣት ያህል ተስፋ የለውም። ከፍርሃት የተፈጠረ የፖለቲካ ቡድን መፍራት ያቆመ ዕለት ሕልውናው እንዳከተመ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ህወሓት/ኢህአዴግ ራሱን እንዲያጠፋ በማድረግ ላይ ማዕከል ያደረገ ቢሆን የተሻለ ይመስለኛል። ስለዚህ ህወሓት/ኢህአዴግን ለማስወገድ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ ማድረግ ያስፈልጋል።

Filed in: Amharic