>

የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ሕግን በጨረፍታ፤ (ውብሸት ሙላት)

(ወልዲያ፣ቆቦና መርሳን በማሰብ የተጻፈ)

ከጥምቀት በዓል ማግስት ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ፣ቆቦና መርሳ ከተሞች ላይ ተከሥቶ በነበረው አለመረጋጋት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ የፖሊስ (ወታደር?) አባላትም የግለሰቦችም ሕይወት አልፏል፡፡ በዛሬው ዕለት (ጥር 23/2010 ዓ.ም.) የአማራ ክልል መንግሥት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ስለ እነዚህ ሁኔታዎች የክልሉን መንግሥት አቋም ይፋ አድርጓል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም እንዲሁ ስለሁኔታው እና ቀጣይ ተግባራት ማብራራያ ሰጥቷል፡፡

የኮሚኒኬሽን ቢሮውም የፖሊስ ኮሚሽኑም ዋና መልዕክት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለአመረጋጋቱ፣ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ለንብረት ውድመት፣አካላዊ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦችን እንደፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ በማድረግ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ብሎም ሰላም የማስፈን ሥራ እንደሚከናወን ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር በትብብር እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን ማስፈን ተገቢ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ወንጀል የፈጸመም ሰው ተጠያቂ መሆን ይገባዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ግን ሲቪል ዜጎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ወንጀል የፈጸሙ የፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላትንም መጨመር አለበት፡፡ ሕግን የተላለፉ፣ሕግ ከሚፈቅድላቸው ሥልጣን ውጭ ኃይል የተጠቀሙ ፖሊሶችን ሊያካትት ይገባል፡፡

የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮም ይሁን የፖሊስ ኮሚሽኑ የፖሊስ ኃይሉ ስለገደላቸው ሕጻናት፣የመከላከያ ሠራዊቱ የክልሉ መንግሥት ሳይጠራውና ሳይፈቅድለት ሕግን ጥሶ ስለመግባቱ ያነሱት ነገር የለም፡፡ ሕግ በሁሉም ዘንድ በእኩልነት ሊተገበርና ሊፈጸም ይገባል፡፡ በመሆኑም፣በተለይ ያልጠመጣጠነ ኃይል የተጠቀሙ የፖሊስ አባላትም ጭምር ከሕግ በታች ከሆኑ፣ የኃይል አጠቃቀምን በሚመለከት፣ ከእዚህ ቀደም የጻፍኩትን መጠነኛ ማሻሻያ ጨምሬ፣ ለክልሉ መንግሥት ለመነሻነት ይህንን ጽሑፍ ይመለከተው ዘንድ ጽፌያለሁ፡፡

የፖሊስ ሚና፤

ፖሊስ የአገር ውስጥ ሰላምና ጸጥታ የማስጠበቅ ሚና ሲኖረው መከላከያ ሠራዊቱ ደግሞ አገርን ከውጭ ጠላት የመከላከል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ፖሊስ ወንጀልን ይከላከላል፡፡ ፖሊስ፣ የሌሎች ግለሰቦችን ወይንም የወል ጠቀሜታ ያላቸውን እንደ አገር፣ መንግሥት፣ መሥሪያ ቤቶች የመሳሰሉት ተቋማትን ላይ ጉዳት ሲደርስ የጉዳት አድራሹን ማንነት እና የድርጊቱን አፈጻጸም የሚያሳይ ማስረጃ ያፈላልጋል፤ወይንም የወንጀል ምርመራ ያደርጋል፡፡ ፖሊስ፣ እንደ ተቋም ተልእኮዎቹ እነዚህ ሁለቱ፣ ወንጀል መከላከል እና ምርመራ፣ ናቸው፡፡

ወንጀልን የመከላከልም ይሁን የምርመራ ሥራ በባሕርይው የግለሰቦችን መብት ለመጣስ የተመቻቸ እና የተጋለጠ ነው፡፡ ስለሆነም የግል ነጻነታችንን ሊጋፋ የሚችል ተቋም ቢሆንም እንኳን የጋራ ደኅንነታችን ካልተጠበቀ መልሶ የግል ነጻነታችን ስለሚጣስ እኩይነት ቢጣባውም አማራጭ የሌለው አስፈላጊ ተቋም ነው፡፡

የፖሊሳዊ ሥራ፣ ከላይ እንደተገለጸው አስፈላጊ ቢሆንም የሰብኣዊ መብት ለመጣስ የተጋለጠ ስለሆነ፣ አገራት በተናጠል ለራሳቸው ብሎም በጋራ በዓለማቀፍ ደረጃ አሠራሩን ለማቅናት ሲሉ በርካታ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እና ሌሎች ሕጎች ላይ በተቀመጠው ሁኔታ የፖሊስ ተግባርን ለማከናውን የመከላከያ ሠራዊቱ በሚገባበት ጊዜ ኃላፊነቱም ተጠያቂነቱም ያው እንደፖሊስ ነው፡፡

የፖሊስ ምልመላ ለማድረግ ጥብቅ መሥፈርቶችን አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም ለምልመላ ያመለከተውን ሰው ባሕርዩን እና ስብእናውን በጥልቅ ለመረዳት የሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ምልመላው ላይ ይሳተፋሉ፡፡ እንዲህ ከሆነም በኋላ ወንጀል በመከላከልም ይሁን ምርመራ ወቅት የሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ በቂ ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ እንደ ሌሎች ሙያዎችም የፖሊስ የሥነ ምግባር ደንቦችም አሉ፡፡

በርካታ አገራት የሥነ ምግባር ደንቦቹ በትክክል መተግበራቸውን የሚከታተል በፖሊስ ተቋሙ ውሥጥ ሆነ ውጭ የሚገኙ ተቋማት እና አሠራር ዘርግተዋል፡፡ አንድ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ዳኛ ወይም ሌላ ባለሙያ የሙያውን ሥነ ምግባር የሚተላለፍ አድራጎት ከፈጸመ እንደሚጠየቀው ሁሉ ፖሊስም በወንጀል፣በዲስፕሊን እና በፍትሐ ብሔር ተጠያቂ እና ኃላፊነት ሊኖርበት ስለሚገባ ይኼው አካሔድ እየዳበረ ስለመሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ሲባል፤

ፖሊስ መደበኛ ተግባሩን በሚያከናውንበት ወቅት ኃይል የሚጠቀምባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ በዋናነት ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የተጠረጠረው ሰው ላለመያዝ ኃይል የሚጠቀም ከሆነ፣ ሊያዝ ሲልም ሆነ ከተያዘ በኋለ ለማምለጥ ሲሞክር፣ ወንጀሉ እየተፈጸመ ባለበት ወቅት ድርጊቱን ካላቆመ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ የሚያስችለውን ያህል ኃይል መጠቀም የተለመደ ነው፡፡ ላለመያዝ ያልሞከረን፣ የማምለጥ ድርጊት ውስጥ ያልገባን፣ የተያዘ ተጠርጣሪ ላይ ኃይል መጠቀም የፖሊሳዊ ሥራን ግብ ለማሳካት ጥቅም የለውም፡፡

አሜሪካን አገር የሚገኝ ስለ ፖሊስ ጥናት በማድረግ የሚታወቅ አንድ ተቋም በያዝነው ዓመት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት ፖሊስ እንደ ተቋምም ሆነ እንደ ግለሰብ መከተል ያለባቸውን 30 መርሆች አሠባስቦ አሳውቋል፡፡ እነዚህን መርሆች የተለያዩ ስለዘርፉ ከተዘጋጁ ድርሳናትም ከሚጠቅሷቸው ንድፈ ሐሳቦች ጋር በማጣጣም ለአራት በመክፈል እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የመጀመሪያ የሰውን ልጅ ሕይወት ክቡርነት መቼም ቢሆን መቼ ማእከል ማድረግ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም፣ ፖሊስ በወንጀል መከላከል ሰበብ ሕይወት እንዳያጠፋ፣ የአካል ጉዳት እንዳያደርስ ጥብቅ እና የዳበሩ ተቋማዊ የኃይል አጠቃቀም መሥፈርቶችን ማበጀት ይመለከታል፡፡ እነዚህ መሥፈርቶችም በትክክል መተግበራቸውን መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ፖሊስ ኃይል ሲጠቀም ሁልጊዜም ተመጣጣኝነት መሆን አለበት፡፡

የተወሰኑት መርሆች የሚያጠነጥኑት ደግሞ፣ ፖሊስ ኃይል ከመጠቀሙ በፊት እና በኋላ ማድረግ ባለበት ዙሪያ ነው፡፡ ፖሊስ ኃይል ከመጠቀሙ በፊት አንድ ነገር እርግጠኛ መሆን አለበት፡፡ ይሄውም፣ ኃይል መጠቀሙ ግጭትን የማያባብስ ስለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ሕዝባዊ ተቃውሞችና እና ሰልፍ በሚኖርበት ወቅት በጥብቅ መፈጸም ያለበት አሠራር እንደሆነ ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም ፖሊስ የሚወስደው የኃይል ርምጃ መረጃ ላይ የተመሠረተ፣ በቦታው ላይ የተከሠቱ ሁኔታዎችን፣ስጋቶችን እና አደጋዎችን በመገምገም ሌሎች አማራጮችን አለመኖራቸውን አረጋግጦ ነው፡፡ ፖሊስ በተጠቀመው ኃይል ምክንያት ጉዳት ከደረሰም የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ዕርዳታ መሥጠት ብሎም፣ በአፋጣኝ ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ከእዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ፖሊስ ተገቢ ያልሆነ ኃይል ሲጠቀም ሌላ ፖሊስ ካለ ጣልቃ የመግባት አሠራርን አገራት ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ጣልቃ ሳይገባ፣ ምን አገባኝ የሚልን ፖሊስ ተጠያቂ የሚያደርግ ሕግ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡

በሦስተኛነት የሚገኙት ፖሊስ የሚጠቀማቸው መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ፖሊስ ሥራውን በአግባቡ እንዲወጣ ብሎም ተጠርጣሪን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ መሣሪዎችን መጠቀም አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ ተሸከርካሪም (ከተሸከርካሪው ውስጥ ተኩስ የሚከፈት ካልሆነ በስተቀር) ይሁን ተሸከርካሪ ላይ ሆኖ መተኮስ ተገቢ አይደለም፡፡

ዘመናዊ እና በተቻለ መጠን ጉዳታቸው ዝቅተኛ የሆኑ መሣሪያዎችን፤ ለአብነት ወደ ሰው ግንባር ሲረጩ ተጠርጣሪዎችን ለተወሰኑ ደቂቃ ራሱን እንዳይቆጣጠር የሚያደርጉ ኬሚካሎች መጠቀም አለባቸው፡፡እነዚህ በብዙ አገራት በየሱቁ የሚገኙ ርካሽና እና በኪስ የሚያዙ፣ በተለይ ሴቶች ከአስገድዶ መደፈር ሙከራ የሚከላከሉባቸው ናቸው፡፡ ሰልፍ እና ተቃውሞ በሚኖርበት ወቅት የሚሠማሩት ፖሊሶች ራሳቸውን መከላከያ ጋሻ ሊጠቀሙ ግድ ነው፡፡

የኃይል አጠቃቀሙም መለካት ያለበት ከዚህ አንጻርም ጭምር መሆን አለበት፡፡ ጋሻ ላልያዘ ፖሊስ፣ ሰልፈኛ ድንጋይ ቢወረውርበት ሊገድለው ስለሚችል ፖሊስ ሽጉጥ ወይንም ሌላ የሚተኮስ መሣሪያ ሊጠቀም ስለሚችል ጉዳቱ ይጨምራል፡፡ ጋሻ ከያዘ ግን የድንጋይ ውርወራውን ለመከላከል ዱላ (baton) በመጠቀም ጉዳቱን መቀነስ ይችላል፡፡ በሠልፍና በሌሎች ሁኔታዎች ወታደርን በከተማ ውስጥ ማሰማራት እንደነዚህ ዓይነት መሣሪያዎችን ስለማይጠቀሙ ወይንም የመጠቀም ልምድ ስለሌላቸው የሚደርሡት ጉዳቶች መናራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

የመጨረሻዎቹ፣ ፖሊስ ኃይል ከተጠቀመ በኋላ በሌሎች አካላት የሚደረጉ ተግባራት ናቸው፡፡ ፖሊስ የወሰዳቸውን የኃይል ርምጃዎች፣ መመዝገብና መሰነድ፣ የመተንተን ብሎም ሪፖርት የማድረግ አሠራር ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል፡፡ ፖሊስ እንደ ተቋም በአፋጣኝ መረጃን ለሕዝብ የማሳወቅ እና ለሚዲያዎችም የመስጠት ግዴታ ሊኖርበት ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እና ሞት በልዩ ሁኔታ በሠለጠኑ ገለልተኛ ባለሙያዎች ምርመራ እንዲደረግባቸው በማድረግ፣ ፍጥነት የተሞላበት ቁጥጥር በማስፈን ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ሥርዓት ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

የኃይል አጠቃቀም ፈርጆች፤
አንድ ፖሊስ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ሳለ ሥራዉ የሚጠይቀውን እና በሕግ የተፈቀደውን ኃይል ሊጠቀም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ነገር ግን ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይልም ሊጠቀም ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው የተመጣጣኝነትን ልኬት የዘለለ ኃይል ነው፡፡ አለመመጣጠኑን በአስተዳደራዊ መንገድ ወይም በፍርድ ቤት ሊረጋገጥ ይችላል፡፡

ሌላው ደግሞ ኃይል መጠቀም በማያስፈልግበት ሁኔታ ኃይል ሲጠቀም፣ ወይንም የሕግ ክልከላን በመተላለፍ ኃይል መጠቀም፤ ሕገ ወጥ የኃይል አጠቃቀም ይባላል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ደግሞ፣ ፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል ርምጃ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ለአብነት፣ አንድ ተጠርጣሪ ከተያዘ በኋላ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች በዚህ ምድብ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ፖሊስ ግዴታውን በሚያከናውንበት ጊዜ፣ ኃይል መጠቀም ሊፈቀድ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች በመለኪያነት እዲያገለግሉ፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአንድ ወቅት የሚከተሉትን መሥፈርቶች አስቀምጦኣል፡፡ እነዚህም፣ የወንጀሉ አደገኝነት፣ ተጠርጣሪው ፖሊስ ወይንም ሌላ ሰው ላይ ቅርብ የሆነ አደጋ የሚያደርስ መሆኑ፣ ተጠርጣሪው ላለመያዝ በግልጽና በአካላዊ እንቅስቃሴ ከተቃወመ፣ ከተያዘ በኋላ ለማምለጥ ከሞከረ፤ የሚሉት ናቸው፡፡

በመሆኑም፣ በሕጋዊ መከላከል (አልሞት ባይ ተጋዳይ) እና የሌሎችን መብት ለማስጠበቅ ሲባል እንኳንስ ፖሊስ ሌላም ግለሰብ ኃይል ሊጠቀም ይችላል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ የወንጀሉ ድርጊት ቀረቤታ እና አደገኛነት፣ በሌላ መንገድ ሊቀለበስ የማይችል መሆኑን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች እና መለኪያዎች በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 78 እና 79 ላይ ተገልጸዋል፡፡

ኃይል መጠቀምን የሚገሩ ሕጎች፤

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ እንደተገለጸው ማንኛውም የሰው ልጅ የማይደፈር በሕይወት የመኖር እና የአካል ደኅንነት መብት አለው፡፡ በሕይወት የመኖር መብቱ በሕግ በተፈቀደው ሁኔታ (ለምሳሌ በሞት ፍርድ፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት) ሊገድብ ቢችልም ፣ በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 16 መሠረት ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ገደብ ሳይደረግበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ልንል የሚገባን የሰው ልጅ አካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ዕውቅና የተሰጠው መብቱ ፍጹማዊ መሆኑን ነው፡፡ ሌላው አንድ ሰው በወንጅል ተጠርጥሮም ይሁን ተፈርዶበት በእስር ላይ በሚገኝበት ጊዜ ኢሰብኣዊ ከሆኑ አያያዞች የመጠበቅ ፍጹም መብት አለው፡፡ በተለይ ይህ መብት በአስቸኳይ ጊዜ እንኳን የሚገደብ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዓለማቀፍ የሰብኣዊ መብት ሰነዶች ማንኛውም የሰው ልጅ በሕይወት የመኖር፣የአካል ደኅንነት መጠበቅ እና ከኢሰብአዊ አያያዝ የመጠበቅ መብቶችን ጥበቃ አድርገዋል፡፡

ከላይ የተገለጹትን መብቶች ሥራ ላይ ለማዋል የበለጠ እንዲረዳ፣ እነዚህን መብቶች የጣሰ ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ፣ ፖሊስንም ጨምሮ፣ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 422(2) መሠረት ከተገቢው በላይ ኃይል ከተጠቀመ እና በ424 መሠረት ደግሞ ጭካኔ የተሞላበት እና ለሰብኣዊ ክብር ተቃራኒ የሆኑ አድራጎት ከተፈጸሙ በወንጀል የሚጠየቁበት ሕግ አለ፡፡

ከእዚህ በተጨማሪም የደረሰው የአካል ጉዳትንም በተመለከተ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 555 በከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ ወይንም በ556 መሠረት በቀላል የአካል ጉዳት ወንጀል ፖሊሱን መክሰስ ይቻላል፡፡ ከሞተ ደግሞ እንደ ግዲያው ዓይነት ከ539-541 ድረስ ባሉት አንቀጾች ሊከሰስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ያልተገባ ኃይልን ይከለክላል፡፡ ሕጉ በእንዲህ እንዳለ ፖሊስ ያልተገባ ኃይል እንዲጠቀም የሚገፋፉ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የተወሰኑትን ብቻ እንመለከት፡፡

የወንጀል የፍትህ ሥርዓት በፖሊስ የኃይል አጠቃቀም ላይ ያለው አንድምታ፤

በወንጀል መከላከል፣ ምርመራ፣ ክስ፣ የፍርድ ሒደት እና ዕርማት ውስጥ የሚሳተፉ ተቋማት፣ አወቃቀራቸው፣ አሠራራቸው እና የሚተገብሩትን ሕግ ጨምሮ በአንድነት የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ይባላል፡፡ የተለያዩ አገራት የፍትሕ ባህላቸውን እና ማሳካት የሚፈልጉት ማኅበራዊ ግብ መሠረት በማድረግ የተለያዩ አካሔዶችን ተልመዋል፡፡ የዘርፉ ምሑራንም አገራት የሚከተሏቸውን አካሔዶች በማጤን እና የራሳቸውን በመጨመር በርካታ ሞደሎችን አስቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህ ውሥጥ ኸርበርት ፓከር የወንጀል ቁጥጥር (Crime Control) እና በሕጉ መሠረት (Due Process) የተሰኙ ሞደሎችን አስተዋውቋል፡፡

‘የወንጀል ቁጥጥር’ ሞደል፣ ግቡ ወንጀልን መቆጣጠር እና ወንጀለኞችን የሚይዝበት፣የሚመረምርበት፣የሚከስበት እና ውሳኔ የሚሠጡት ተቋማት የሚከተላቸው አሠራር ወጥነት፣ቀልጣፋነት፣ብቃት ላይ ትኩረት ማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ሒደት ውስጥ ፍትሕ የሚያዛቡ ውሳኔዎች ቢፈጸሙ እንኳን በይግባኝ ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ታሳቢ ያደርጋል፡፡

‘በሕጉ መሠረት’ የሚባለው አሠራር ደግሞ ዋና ትኩረቱ የተጠርጣሪዎች መብት ስለሆነ አጽንኦት የሚሰጠው በወንጀል የተጠረጠረው ሰው ከምርመራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ባለው ሒደት ውስጥ መብቱን እንዲጠበቅለት ማድረግ ነው፡፡ የመጀመሪያውን፣ በርካታ የአውሮፓ አገራት የሚከተሉት ሲሆን ሁለተኛውን እንግሊዝና አሜሪካ በዋናነት ይከተሉታል፡፡

የሕግ ሥርዓታችንም እና ሕጎቻችን በዋናነት የተቀዱት ከአውሮፓው ሥርዓት በመሆኑ፤ የእኛም አገር የወንጀል ቁጥጥር ሞደልን ወደ ሚከተሉት ጎራ ልትካተት ትችላለች፡፡ ስለሆነም፣ ፖሊስን የሚመለከቱት አተገባበር በዚሁ የተቃኘ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ወንጀለኞችን የመያዝ፣የመመርመር፣ የማስቀጣት፣ እና የመሳሰሉት ተግባራት በወጥነት፣ በተቀላጠፈ፣ እና በብቃት መወጣት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በተቃራኒው በሕጉ መሠረት የተሰኘውን ሞደል መርጧል፡፡ በተለይም፣ የአካል ደኅንነት ሊገደብ የሚችልበት ምንም ዓይነት ቀዳዳ አለመኖሩ እንዲሁም የተጠርጣረ፣የተያዘ እና የተከሰሰ ሰው መብቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

በፍትሕ ተቋማት ውስጥ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (Business Process Re-engineering )፣ ሲተገበር የተስተዋለው በዋናነት የወንጀል ቁጥጥር ሞደልን እና ተዋረዳዊ የውሳኔ አሠጣጥ የሚባለውን የመንግሥት ሥራ የማከናወን አዝማሚያ ነው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ልክ እንደ ኮሚኒስታዊ የፖለቲካ ፓርቲ አሠራር ከላይ ወደታች የሚሠጥ የውሳኔ መርህን ይከተላል፡፡

እነዚህ የወንጀል ቁጥጥር እና ተዋረዳዊ የውሳኔ አሰጣጥ ሞደሎች እንደ ማንኛውንም የፍትሕ ተቋማት ለፖሊስም ሰፊ ሥልጣን ይሠጣል፡፡ ትኩረቱም የግለሰቦችን መብት ከማስከበር ይልቅ ወንጀልን መቆጣጠር ነው፡፡ ስለሆነም፣ ከፖሊስ ኃይል አጠቃቀም አንጻር እንደ እንግሊዝ እና አሜሪካን የመቀየድ አዝማሚያ የለውም፡፡

የፖሊስ አወቃቀር እና የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም፤

ፌደራላዊም ይሁኑ አሃዳዊ አወቃቀር የሚከተሉ አገራት በአንድ እዝ ሥር ያለ ፖሊስ ወይንም ደግሞ በተለያዩ እዞች ሥር የሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ ተቋማት አሏቸው፡፡ በርካታ የፖሊስ ተቋማት ያሏቸው፣ በጥምረት እና በቅንጅት የሚሠሩበት መጠን የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ የእያንዳንዱ ፖሊስ ተቋማትም ተግባር እና ኃላፊነት ግልጽ ድንበር ከመኖር አንጻር የተለያዩ አሠራሮች አሏቸው፡፡የፖሊስ ተቋማት ብዛት እና የዳበረ ቅንጅታዊ አሠራር መኖር ወይንም አለመኖር፣ ከግለሰብ መብት መከበር፣ ከመልካም አስተዳደር እና ከተጠያቂነት ጋር ግንኙነት አለው፡፡

የኢትዮጵያን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ የክልሎች እና የፌደራል ፖሊስ አሉ፡፡ የክልሎች ደግሞ መደበኛ እና ልዩ ኃይል አላቸው፡፡ የአካባቢ ፖሊስም (ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) አለ፡፡ በፌደራልም፣ ከልዩ ኃይሉ በተጨማሪ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ፖሊስ አለ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የገቢዎችና ጉምሩ፣የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር እና ሌሎችም የፖሊስ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ሌላው ደግሞ የክልሎች እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ፖሊሶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃይል ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

በተለይ ሕዝብ ሰልፍ በሚያደርግበት እና ተቃውሞዎች በሚኖሩበት ወቅት፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በተለይም በወልዲያ (የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድርም እንደገለጹት) እንደሆነው፣ ሰልፉንና ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የፌደራል ፖሊስ፣የክልሎቹ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱም ጭምር በአንድ ጊዜ ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተለያዩ ችግሮችን ይፈጥራሉ፡፡ ተገቢ ያልሆነ ኃይል የተጠቀመውን ፖሊስ መለየት ያዳግታል፡፡ እንዲሁም ተጠያቂነት እንዳይሰፍን እንቅፋት ይሆናል፡፡

በመሆኑም፣ ቅንጅት የጎደለው የእዝ ሰንሰለቱ የተዘበራረቀ እና የተለያዩ ትዕዛዝ ሰጪዎች መብዛት ፖሊስ የሚጠቀመውን ኃይል መመዘን ይቅር እና ተጎጂዎች አቤቱታም ሆነ ክስ የሚያቀርቡበትን እና ምርመራው የሚከናወንበትን ፖሊስ ማንነቱንም ይሁን ተጠሪነቱን ስለማያውቁት ደመ ከልብ ይሆናሉ፡፡

ፖሊስ አገልግሎት መሥጠት ያለበት ተወልዶ ባደገበት ወይንም በመኖሪያ አድራሻው አካባቢ መሆን አለበት፡፡ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ጭካኔ የተሞለበት ኃይል እንዳይጠቀምም ይረዳል፡፡ እዚህ ላይ በጥንት ጊዜ የነበራው የፖሊስና እና ወታደራዊ አሠራራችን ትምህርት ሰጪ ስለሆነ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡ መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም፣ በ14ኛው እና 15ኛው ብሎም እስከ አጼ ልብነ- ድንግል የንግሥና አዝማናት ድረስ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች ሰፍረው የሚገኙ እንደ ወታደርም እንደ ፖሊስም የሚያገለግሉ የጨዋ ሠራዊት ነበሩ፡፡

እነዚህ የተለያዩ መጠሪያ የነበሯቸው የጨዋ ሠራዊት በዋናነት የሚመለመሉት ከአካባቢው ነበር፡፡ ለምሳሌ በአጼ በእደ ማርያም (1460-1470 ዓ.ም.)፣ የዶባ (አሁን ራያ የሚባለው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች) ሕዝብ እያመጸ ቢያስቸግር የንጉሡ ሰራዊት እና በጠለምት አካባቢ ሰፍረው ይኖሩ የነበሩ ጃን አሞራ ተብለው የሚጠሩት ከወጓቸው በኋላ ዐመጹ ተረጋጋ፡፡ ከዚያም ንጉሡ ከዶባ ሕዝቦች ከራሳቸው የጨዋ ሠራዊት እንደሠሩላቸው፣ እና ከመካከለቸው ለእነሱ የሚስማማቸውን ሰው አስተዳዳሪ እንዲሆናቸው እንደሾሙላቸው የዜና መዋዕላቸው ያስረዳል፡፡

ይህንን እንደ ማሳያ የተነሳው ምንም ዓይነት ሌላ ንድፈ ሐሳብ ዋቢ ማድረግ ሳያስፈልግ የታሪካችን አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ በተለይ የጭካኔ ተግባርን ለመቀነስ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንዲህ ዓይነቱን አሠራርን ማስፈን ተገቢ መሆኑን ጥናቶችም ያስረዳሉ፡፡

ማጠቃለያ፤
ከላይ በወፍ በረር እንዳየነው ሕገ መንግሥቱ፣ የሰብኣዊ መብት ሰነዶች እና የወንጀል ሕጉ ፖሊስ ያልተመጣጠነም ሆነ ሕገ ወጥ እና ጭካኔ የተሞላበት ኃይል እንዳይጠቀም ይከለክላል፡፡ በተቃራኒው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ቅኝት፣ የፖሊስ ተቋማት አወቃቀር እና ቅጥ ያጣው በየክልሉና በየከታማ አስተዳደሮቹ የስምሪት ሥርዓት ፖሊስ ኃይል እንዲጠቀም እንደ ማትጊያ ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪም፣ ከመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ አተገባበር እና ውጤት ተኮር የሥራ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ወንጀልን በማንኛውም መንገድ መከላከል እና ምርመራም እንዲሳካ ስለሚያበረታታ ሰብአዊ መብትን ከማክበር ይልቅ ወደ ተቃራኒው ለማዘንበል የተመቸ ነው፡፡

ፖሊሳዊ አሠራርን የሚያጎለብት፣ ባሕርይን የሚገራ ዝርዝር የሥነ ምግባር ደንብ እንዲኖር እና በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የፖሊስ ሕገ ወጥ ተግባር የሰብአዊ መብትን ከመጣሱም በተጨማሪ የመልካም አስተዳዳር እጦትንም ያስከትላል፡፡ ስለሆነም እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል ሕግ እንዲኖር እና የሚቆጣጠሩ ተቋማት ማስፈን ተገቢ ነው፡፡

የፖሊስን የኃይል አጠቃቀም፣ በመጀመሪያ ራሱ የፖሊስ ተቋሙ ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡ መረጃ በመያዝ፣ ዘመናዊ መሣሪያዎችን በማሟለት፣ እና እነዚህን መሣሪዎች ሳያስታጥቁ አድማ እና ሰልፍ በሚኖረበት ጊዜ ፖሊስን አለማሰማራት፣ የተቀናጀ የፖሊስ አሠራር ማስፈን የሕዝብን ብሶት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ እንደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ እና ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ እንደተባሉት ዓይነቶቹ የፖሊስ አድራጎት ሲኖሩ ዝርዝር እና ወቅታዊ መረጃን በፍጥነት ለሕዝብ የማድረስ አሠራር መተግበር ግድ ነው፡፡

በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ ከተጣሉበት ኃለፊነቶች አንዱ ፖሊስና እና ሌሎች የጸጥታ ተቋማት የሰብኣዊ መብት ሲጥሱ፣ ሕግን በጣሰ ሁኔታ የፌደራል ፖሊስ ክልሎች ውስጥ ሲገባ እና የመከላከያ ሠራዊቱ በአገር ውሥጥ የጸጥታ ጉዳይ ሲሰማራ ተገቢውን ማጣራት እና ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

የሰብአዊ መብት ኮሚሽንም፣ የፖሊስ የኃይል አጠቃቀም የሚለካው እያንዳንዱ ተናጠል ጉዳይ ላይ ተመሥርቶ መሆኑ እየታወቀ በጅምላ፣ በኦሮሚያ የተወሰደው ተመጣጣኝ፣ በአማራ የነበረው ያልተመጣጣነ በማለት የሚቀርበውን አሠራር ሳይንሳዊ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

በመሆኑም፣የአማራ ክልል መንግሥትም የፖሊስ ኃይላ የነበረውን ሚና በመለየት፣የማባባስ ተግባራት ውስጥ መግባት አለመግባቱን፣ወደ ቦታው በሚያቀናት ወቅት ይዞት የነበረውን መሣሪያ (ጋሻ፣አስለቃሽ ጋዝ ወዘተ)፣ክላሽንኮቭና ሌሎች የሚተኮሱ መሳሪያዎችን ከመጠቀሙ በፊት ምን ምን እርምጃ እንደወሰደ፣ወደ ከተሞቹ የገቡት ወታደሮችና የፌደራል ፖሊሶች (ካሉ) ስም ዝርዝራቸውን እንዲሁም በማን አመራርነት የጸጥታ ማስከበር ሥራ ይሠሩ እንደነበር፣የትኛው ፖሊስ ምን እርምጃ እንደወሰደ፣የትኛው ፖሊስ ማንን እንደገደለ እና የአካል ጉዳት እንዳደረሰ በመለየት የተጠቀሙት ኃይል ተመጣጣኝ መሆን አለመሆኑን በመለየት እና ሌሎች ተግባራትንም ጭምር በማከናወን በማጣራት ለሕግ የማቅረብ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ ይሄንኑም ለሕዝቡ በይፋ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡ የሕግ የበላይነት ሲቪል ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላትንም ይመለከታል፡፡

Filed in: Amharic