>
5:13 pm - Wednesday April 18, 4345

ህወሓት እና ፍርሃት: ከቀበሌ እስከ መቀሌ! (ስዩም ተሾመ)

ኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ እንዴት ደረሰ? በተለይ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በጥሞና ለታዘበ ሰው ምክንያቱንና ሂደቱን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል። በ1997 ዓ.ም በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩ። በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎት አልነበረኝም። በዚያ ዓመት በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በመራጭነት ከመሳተፍ የዘለለ ሚና አልነበረኝም። እስከ ግንቦት7/1997 ዓ.ም ዕለት ድረስ የነበረው አጠቃላይ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነፃና አሳታፊ ነበር።

በእርግጥ የ1997ቱ ምርጫ የኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ያካሄደው ሦስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነው። ታዲያ በወቅቱ “ይህ ምርጫ ለምን ከ1987ቱ እና 1992ቱ ምርጫዎች ተለየ ሆነ?” የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ ሲመላለስ ነበር። በ2002 እና 2007 ዓ.ም የተካሄደው “ማጭበርበር” – መቼም ያንን ቅሌት “ምርጫ” ብሎ መጥራት ይከብዳል – ከ1997ቱ ጋር ምንም የሚያመሳስለው ነገር የለም። የ1997ቱ ምርጫ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የገባኝ በ2004 ዓ.ም የ2ኛ ድግሪ ትምህርቴን ለመማር መቐለ ዩኒቨርሲቲ በሄድኩበት ወቅት ነው።

መቐለ እንደገባሁ በመጀመሪያ የታዘብኩት ነገር የቤት ኪራይ ርካሽነት ነው። ሻውርና ሽንት ቤት ያለው ፅድት ያለ ክፍል በ400 ብር ተከራየሁ። ዓዲ-ሃቂ እና ዓዲ-ሃውሲ የሚባሉ ሰፈሮችን ውስጥ ለውስጥ እየዞርኩ ስመለከት የመኖሪያ ቤቶቹ እንዳሉ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተገነቡ መሆናቸውን ታዘብኩ። የውስጥ-ለውስጥ መንገድ እንኳን ገና በአግባቡ አልተዘረጋም። ከ1997 ዓ.ም በፊት የከተማዋ ዳርቻ የነበረው የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ-ሃቂ ካምፓስ በአምስት አመት ውስጥ የከተማዋ መሃል ሆኗል። ከዓዲ-ሃቂ ካምፓስ ጎን ያለው ሰፈር ግን አሁንም “የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበር” ነው። እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ የከተማዋ ዳርቻ የነበረ የገጠር ቀበሌ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የከተማዋ መሃል ሆኗል።

በአጠቃላይ የመቐለ ከተማ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ባሉት አምስትና ስድስት አመታት ብቻ በእጥፍ ሰፍታለች። ሁለተኛ አብዛኞቹ መኖሪያ ቤቶች ባለ G+1 እና G+2 ዘመናዊ ቪላዎች ናቸው። ነገር ግን፣ በአብዛኞቹ ቪላዎች ውስጥ የሚኖሩት የግቢው ጠባቂ ዘበኛ እና “እርግቦች” ናቸው። ምክንያቱም የቪላዎቹ ባለቤቶች በአብዛኛው የሚኖሩት በዋናነት በአዲስ አበባ እና ሌሎች የመሃል ሀገር ከተሞች፣ እንዲሁም ውጪ ሀገር የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በጥሞና ለሚያጤን ሰው በ1997ቱ ምርጫ ወቅት አንዳንድ የቅንጅት ደጋፊዎች እንደዋዛ “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” በማለት ያሰሙት መፈክር በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ስነ-ልቦና ላይ ያሳረፈውን ጠባሳ መገንዘብ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ፍፁም አምባገነን የሆነበትን መሰረታዊ ምክንያት በግልፅ ለመረዳት ያስችላል።

የ1997ቱ ምርጫ ከእሱ በፊት እና በኋላ ከተካሄዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ፍፁም የተለየ ነው። በወቅቱ የነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ እንደ ልዩ አጋጣሚ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ከተወሰኑ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች በስተቀር በተቀሩት የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ የ1997ቱ ምርጫ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር ይጠቀሳል። ለተወሰኑ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮችና ደጋፊ ልሂቃን ግን በትጥቅ ትግል የያዙትን የፖለቲካ ስልጣን ለማጠናከር ያደረጉት ሙከራ ራሳቸውን ሊያጠፋቸው ተቃርቦ የነበረበት መጥፎ አጋጣሚ ነበር።

እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ የመንግስታዊ ስርዓቱን ሕልውና ለማረጋገጥ ያለመታከት ጥረት ሲያደርግ ነበር። የኦነግ ከሽግግሩ መንግስት ጥሎ መውጣት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ የህወሓት መሰንጠቅ፣… ወዘተ የመሳሰሉት ክስተቶች በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ ፈጥረዋል። ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንደ አዲስ ተቀርፀው ተግባራዊ ተደረጉ፣ በማህበራዊ ዘርፊ የኮንዶሚኒዬም ግንባታ መጀመር፣ በኦኮኖሚ ረገድ አንዳንድ እድገቶች መታየት ጀመሩ።

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ህወሓት/ኢህአዴግ በጦርነት የያዘውን ስልጣን በሕዝብ ምርጫ ለማጠናከር የ1997ቱም ምርጫ አቅዶ መንቀሳቀስ ጀመረ። የምርጫው ዕለት እየተቃረበ እስኪመጣ ድረስ ድርጅቱ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ እንደ ነበር ይታወሳል። በዚህ መሰረት፣ ከ1997ቱ ምርጫ በፊትና በኋላ የተካሄዱትን አራት ምርጫዎች በተመሳሳይ ነፃና ገለልተኛ ማድረግ ይችል ነበር።በአጠቃላይ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማድረግና አለማድረግ በህወሓት/ኢህአዴግ ምርጫና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መገንዘብ ይችላል።

በዚህ መሰረት፣ በ1987ና 1992 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ነፃና ገለልተኛ ያልሆነበት መሰረታዊ ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ስላልነበረው ነው። በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ የተረጋገጡ ሃቆች ምንድን ናቸው?

አንደኛ፡- በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት በብዙሃኑ የኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ፍፁም ተቀባይነትና ድጋፍ እንዳልነበረው፥ እንደሌለው፥ ወደፊትም እንደማይኖረው ነው። በመሆኑም የ1997ቱ ምርጫ ውጤት ህወሃት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚባል ነገር ከቶ እንዳያስብ አድርጎታል።በዚህ ፅሁፍ “የኢህአዴግ መንግስት” ከሚለው ይልቅ “ህወሓት/ኢህአዴግ” የሚለውን ቃል የምጠቀምበት ምክንያት መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። 

ሁለተኛ፡- ደግሞ ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ህወሓት/ኢህአዴግ እየደጋገመ ሲያራግባት የነበረችውን “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” የምትለዋ መፈክርና የፈጠረችው ተፅዕኖ ነው። በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተደናብሮ በመሃል ሀገር ያፈረናውን ሆነ የዘረፈውን ሃብት ይዘው ወደ መቐለ በመሄድ ዛሬ ላይ የእርግቦች መኖሪያ የሆኑ ቪላዎች የገነቡት የህወሓት ልሂቃን ናቸው። በእርግጥ እኔ “ንብረት ወደ ቀበሌ፣ ትግሬ ወደ መቀሌ” የሚለው አባባል ልክ “በባሌ ወይም በቦሌ…” እንደሚባለው ዓይነት ነው። የመጨረሻዎቹ ፊደላት “ሌ” ከመሆኑ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ትርጉም የለውም። ለህወሓት ልሂቃን ግን በጣም አስደንጋጭ አጋጣሚ ነበር። ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የደህዴንና ብአዴን ልሂቃን ወደ ባህር ዳር እና ሐዋሳ በመሄድ የወደፊት መሸሸጊያቸውን ሲገነቡ አልታየም። ኦህዴድ ደግሞ ጭርሽ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው።

የ1997ቱ ምርጫ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት በትጥቅ ትግል የተቆጣጠረውን የፖለቲካ ስልጣን በሕዝብ ምርጫ ለማጠናከር ያደረገው ሙከራ የፈጠረው ድንጋጤ መቼም ቢሆን ከህወሓቶች ውስጥ ሊወጣ አይችልም። ምክንያቱም ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ያደረጉት ሙከራ በኢትዮጲያ ሕዝብ ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነት እንደሌላቸው በግልፅ አሳያቸው። ከዚያን ግዜ በኋላ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚመራው፣ የወደፊት አቅጣጫቸውን የሚወሰነው፣ “የቀድሞው ስርዓት ተመልሶ ይመጣል” በሚል ፍርሃት ነው።

አንድ የፖለቲካ ቡድን ስለ ቀድሞ ስርዓት በደልና ጭቆና ብቻ እያሰበ፥ ወደኋላ እያየ የሚጓዝ ከሆነ ከፊት ለፊቱ ያለውን ነባራዊ እውነታን በቅጡ መገንዘብ አይችልም። በዚህ መልኩ፣ በድንጋጤና ፍርሃት የሚደረግ ነገር የብዙሃኑን መብትና ነፃነት ይገድባል። “የቀድሞ ስርዓት ተመልሶ እንዳይመጣ” በሚል ፍርሃት ሲታትሩ በሕዝብ ላይ ከቀድሞ ስርዓት የባሰ በደልና ጭቆና መፈፀም ጀመሩ።

በመሰረቱ ፍርሃት (fear) ጨቋኛ የሆነ አምባገነናዊ (Totalitarian) መንግስት የተግባር መርህና መመሪያ ነው። መንግስት ይፈጠራል። የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ አሁን ካለበት ደረጃ የደረሰው የ1997ቱ ምርጫ በህወሓቶች ላይ ባስከተለው ድንጋጤና ፍርሃት ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት ወደ ፍፁም አምባገነንነት በመቀየሩ ነው። በመሰረቱ “Totalitarian” ማለት “የአንድ ፓርቲ መንግስት” ማለት ነው። ኢህአዴግ በ2002 እና 2007 ዓ.ም ባካሄደው ሀገራዊ “ማጭበርበር” 99.6% እና 100% “አሸነፍኩ” ፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የመሆኑን ያረጋግጣል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ፍፁም አምባገነን የሆነበት ሁኔታ ከስርዓቱ አፈጣጠር ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። “በፍርሃት መርህ የሚመራ አምባገነናዊ መንግስት መቼና እንዴት ይፈጠራል?” ለሚለው፣ “Hanna Arendt” አብዮተዊ ደረጃውን (revolutionary phase) ጨርሶ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ስልጣኑን ለማጠናከር ጥረት በሚያደርግበት ወቅት እንደሆነ እንዲህ ትገልፃለች፡-

“Regimes become truly totalitarian only when they have left behind their revolutionary phase and the techniques needed for the seizure and the consolidation of power—without of course ever abandoning them, should the need arise again.” On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding: 329-360

ባለፉት አስር አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ፍፁም አምባገነን እየሆነ የመጣበት ሂደት ከላይ ከተጠቀሰው ጋር አንድና ተመሳሳይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። እንደ “Hanna Arendt” አገላለፅ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ አብዮታዊ ደረጃውን ጨርሶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣኑን ለማጠናከር ሙከራ ያደረገው ወደ ስልጣን የመጣበትን ዘዴ ይዞ ነው። ይህ የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን የመጣው በትጥቅ ትግል ሲሆን በምርጫው ማግስት ተመሳሳይ ስልት በመጠቀም ራሱን ከውድቀት ታድጓል። በዚህ ረገድ፣ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ “አጋዚ” የተባለውን ልዩ ኃይል በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያደረሰው የሞትና አካል ጉዳት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

እስካሁን ድረስ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በፍርሃት መርህ የሚመራ ፍፁም ጨካኝ የሆነ አምባገነናዊ ስርዓት እንደተፈጠረ ተመልክተናል። አሁን ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ የተፈጠረው ይህ ቡድን በፍርሃት እየተመራ በዜጎች ላይ በሚፈፅመው በደልና ጭቆና ምክንያት ነው። በዚህ ፅሁፍ፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ችግር ህወሓትና ፍርሃት እንደሆኑ ተመልክተናል። “ህወሓትና ፍርሃትን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?” የሚለውን በሌላ ፅሁፍ ይዘን እንቀርባለን።

Filed in: Amharic