>
5:13 pm - Wednesday April 19, 0175

“የሃይማኖት አባቶች” የሰላም ጥሪ - የዳንኤል ክብረት መልእክት (ክንፉ አሰፋ)

በትናንት ምሽቱ የ”ሰላም ዋጋ” ዲስኩር አፈሙዝ ሳይሆን “ዘመናዊ መገናኛ ብዙሃን” ተወግዟል። የሃገሪቱ እድገት እና ትራንስፎርሜሽንም ተወድሷል።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዻዻስ፣  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቴያስ ፓትሪያሪክ፣  ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአክሱም ወጨጌ፣  ዘመንበረ ተክለሐይማኖት….  ወዘተ  “… (ሃገሪቱ) ለሁሉም ልጆችዋ የምታበላው ከሌላት ከየት ታምጣ?” ብለውናል።
“ሕዝቡ ቢያገኝም አይረካም” የሚሉን አቡነ ማቴያስ እዚያች ቦታ ላይ እንዴት እንደተቀመጡ የታወቀ ነውና ከእርሳቸው ከዚህ የተለየ ነገር ፈጽሞ አንጠብቅም።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሃጂ ከድር ሁሴንም እንደ ገለልተኛ ሰው ተሰይመዋል። የአብያተክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ እና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉም በቀጥታ ስርጭት ቀርበው ሰለ ትርጉም አልባዋ “ሰላም”  ያልተነገሩት ነገር የለም።
ዳቦ እና መብት ለጠየቀ፣ ጥይት ሲርከፈከፍበት ግድያውን የማውገዝ ድፍረት እና ሞራል ሳይኖራቸው በብሄራዊ ቴሌቭዥን ቀርበው ስለ ሰላም መደስኮር ምንም ትርጉም የለውም።
የንጹሃን ዜጎች መገደልን ለማውገዝ የሃይማኖት ሰው ወይንም የተቋም መሪ መሆን አያሻም። ይህንን ለማድረግ  ልብ እና አንጀት ያለው፣ አእምሮው ማሰብ የሚችል ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው።
አጋዚ መግደል ሲሰለቸው፤ እነዚህን  “የሃይማኖት አባቶች” በቴሌቭዢን እያቀረበ የ”ሰላም” ጥሪ ሲያስተላልፍ ነበር። ከተወያዮቹ የምንረዳው አንድ ነገር አለ።  ግድያ መፍትሄ ሳይሆን ይልቁንም ቤንዚን ሆኖ ችግሩን እንዳባባሰው የተረዱት አርፍደው ነው።  ሕዝብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ ጀርባ ሰጥተው የነበሩ “አባቶች”፤ ወያኔ  ጭንቅ ሲይዛት  ብቅ ብለው ስለ ሰላም ዋጋ ተናገሩ።   ማንን ሊያሳምኑ እንደሚሞክሩ ግን አልተገነዘቡም።
ስለክቡር ህይወት ዋጋ አንዳች ያልተነፈሱ ሰዎች ስለ ሰላም ዋጋ ለመደስኮር መነሳታቸው ምን ያህል እንደሚፋጅ የሚገነዘቡት ግን የቆሰሉት ብቻ ናቸው።
ስለ ሞራል እሴቶች ለማስተማር”፤  በመጀመርያ ሞራል ያስፈልጋል። ስለ ሰላም ለመናገርም ድፍረት ይሻል።  “ግድያው ይቁም”  ለማለት ድፍረቱ ሳይኖር በገዳዮቹ አንደበት የሚወጣውን  የሰላም ዜማ ማስተጋባት ሲበዛ ግብዝነት ነው።
አራቱ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በመሃሙድ አህመድ “ሰላም ባለም ዙርያ ሁሉ” መዝሙር ታጅበው ኢቢሲ ላይ የተሰየሙት በእርግጥ የ 100 ሚሊዮን ሕዝብን ብሶት ለማስተጋባት ሳይሆን፣  ወጌሻ  ሆኖ ወያኔን ለመጠጋገን ነው። “አፈሙዙ ይውረድ” ብለው ወያኔን ያወግዛሉ ብለን ስንጠብቅ “ለሰላም ዋጋ እንስጥ” ይሉናል።  ለሞቱ ወገኖች የተሰማቸውን ሃዘን ይገልጻሉ ስንል ከጀርባቸው  “የውጭ ሃይሎች አሉ” ይላሉ።    ከምስላቸው ጀርባ የነጭ እርግብ ምስል አለ። “ሰላም” የሚል ጽሁፍም ጎልቶ ይታያል።  ሰላም እነሱ ሲፈልጉ ብቻ የሚመጣ፣ ሳይፈልጉት ደግሞ የሚሄድ ግዑዝ ነገር ያደረጉት ነው የሚመስለው። “የሰላም ዋጋ ስንት ነው?” ይሉናል።  የህይወትስ ዋጋስ ስንት ነው?
የሃይማኖት አባት ተብለው፣  አልባሳቱን ለብሰው፣  ቆብ አጥልቀው ከመቀመጣቸው ውጪ ንግግራቸው ከማጽናት ይልቅ የሚያበግን፣  ከማቅናት ይልቅ የሚያቃጥል፣  ቋንቋቸውም ኢሃዴግኛ ነው። ብዝህነት፣ እድገት ፣ ጸረ-ሰላም፣ የውጭ ሃይሎች፣ ወዘተ የሚሉ ወያኔ እንኳ ሰልችቶት የተዋቸውን ቃላት ይጠቀማሉ።  እነ ደብረጽዮን፣ “ለችግሩ ጠተያቂዎች እኛ ነን”  ማለት በጀመሩበት ሰዓት አባ ቆባቸውን አጥልቀው – መስቀላችውን እንደጨበጡ “ቀስቃሾቹ ሰላማችንን እና ልማታችንን የማይሹ የውጭ ሃይሎች እንደሆኑ”  ሊነግሩን ሞከሩ።  ፓስተር ጻድቁ   ሰለ አካባቢው ጂኦ ፖለቲካም ሁኔታና ስለ ውጭ ሃይሎች ተጽእኖም ይተነትኑ ነበር።
የፖለቲካ እውቀታቸው ይህን ያህል ከጠለቀ በነካ እጃቸው ስለ አንቀጽ 39 ጀባ ቢሉን ምን ይላቸዋል?  የህዝብ ድምጽ ዘርፎ ፓርላማውን  100 እጅ የለያዘው ቡድንስ ጽድቅ ነው?   የእምነት መጻህፍት በሙስና የበለጸጉ ሰዎችን አውግዙ አይልም?  ዝሙትስ ነውር አይደል?  በዚህ  ተግባር ስለተሰማሩት መሪዎች ለመናገር ለምን አልደፈሩም?
እነዚህን ጥያቄዎች ለህሊናቸው ትተን ወደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መልእክት እንሂድ።
“ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?” በሚል ርዕስ  በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተለቀቀውን ጽሁፍ አነበብኩ።  መልዕክቱን በአንድ ትንፋሽ አንብቤ እንደጨረስኩ፤ የጀርመኑ ቄስ ማርቲን ኒሞለር ንግግር ታወሰኝ።
ናዚ ጀርመኖች 6 ሚሊየን የሚሆኑ አይሁዶችን የጨረሱት በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ፤ በየተራ ነበር። መጨረሻ ላይ  የተያዘው ፓስተር ማርቲን ኒሞለር ሊታረድ ከገባበት የማጎርያ ካምፕ ሆኖ እንዲህ አለ።
“ናዚዎቹ በመጀመሪያ ወደ ኮሚንስቶች መጡ፥ እኔ ኮሚንስት ስላልነበርኩ ዝም አልኩ። ቀጥሎ ወደ ሠራተኛ ማኅበራት መጡ። እኔ የሠራተኛ ማኅበራት አባል ስላልነበርኩ ዝም አልኩ። ከዚያ ወደ አይሁዶች መጡ። እኔ አይሁድ ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። በመጨረሻ ወደ እኔ መጡ። በዚህን ግዜ ስለ እኔ የሚናገርልኝ አንድም ሰው አልነበረም። ”
ወገናችን በአጋዚ እንስሶች ጭንቅላቱ እና ደረቱ ላይ እየተተኮሰ መውደቅ ከጀመረ እነሆ 27 ዓማታት አለፉ።  የወልድያው ግድያ ቃላት ባይገልጸውም ከጎንደሩ ግድያ፣ ከባህርዳሩ ጭፍጨፋ፣ ከአምቦው እና  ከእሬቻው እልቂት የተለየ አይደለም። ጨለንቆ ላይም ይፈስስ የነበረው የእንስ ሳይሆን የሰብአዊ ፍጡር ደም ነው።… እንዲህ እያለን የ27 ዓመቱን የግፍ ግድያ ብንዘረዝር መሽቶ ይነጋል።  ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ቄሱም ዝም! መጽሃፉም ዝም እንዲሉ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሲቃወሙ አልሰማንም።
ሲኖዶሱም ቢሆን  ከ”ጥልቅ ተሃድሶ” በኋላ  ሁለት ወይንም ሶስት ትግርኛ ተናጋሪዎች  ሲገደሉ ብቻ ጩኸት ሲያሰሙ ብቻ ነው የምናስታውሰው።
ከዲያቆን ዳንኤል ጽሁፍ ያስደመመችኝ ነገር “መንግስትም ወደ ልቡናው ይመለስ” የምትለዋ ቁልፍ ሃሳብ ናት።  አባባልዋ ዘይትን ከውሃ እንደመቀየጥ ሆነችብኝ።  እምነቱ እንደሚለው  “ፈጣሪ ፍርዱን ይስጣችሁ”  ብሎ ማለፍ አንድ ነገር ነው። በፖለቲካ መነጽር ካየነው ግን እየገዛ ያለው መንግስት ሳይሆን አንድ ትውልድን የበላ አውሬ ነው።  በሕጻናት፣ በካህናትና  በጽላት ላይ ይተኩስ የነበረ አውሬ ላፈሰሰው ደም ተጠያቂ  ይሆናል እንጂ ምክር ያሻዋል?
Filed in: Amharic