>

ንገረኝ…እስኪ ንገረኝ??? (ስዩም ተሾመ)

#የህወሓት ታጋዮች፥ አባላትና ደጋፊዎች የሚመሩ የፀጥታ ተቋማት በጋምቤላ፥ በቤንች ማጂ፥ በሶማሊ፥ በኦሮሚያና አማራ ክልል ነዋሪዎች በብሔር ግጭትና አሸባሪነት ሰበብ በፀረ-ሽብር ህጉ አማካኝነት በመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞች፥ የፖለቲካ መሪዎችን #ማዕከላዊ እስር ቤት በማስገባት በሰው ልጅ ላይ ለመፈፀም ቀርቶ ለማሰብ እንኳን የሚከብድ ግፍና በደል ሲፈፅሙ “ኧረ…ይሄ ነገር መጨረሻው የከፋ ይሆናል” ስልህ አልሰማህኝም!! እየደረሰብኝ ያለውን በደልና ጭቆና፥ ህመሜን መስማትና መረዳት፣ እንደ ሀገር ልጅ መከራዬን ተጋርተህ ይሄን ጨቋኝ ስርዓት አብረህኝ መታገል ቢያቅትህ፣…ሁሉም ነገር ቢቀር እንደው የሀገሬ ልጅ #ቁስሌን እየነካህ አታሹፍብኝ፣ ህመሜ ባይሰማህ ቁስሌን አትንካብኝ፣ “በተግባር ባትደግፈኝ በቃል እንኳን ተስፋን አበድረኝ”  ብዬ ስማፀንህ “እንኳን ለግንቦት ሃያ(20) አደረሰህ!” ብለህ አላገጥክብኝ፡፡ ህዝቤን በመከፋፈልና በመግደል የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፥ ለአንተ ለራስህ እንኳን የማይጠቅም፣ ህዝብህን መጠቀሚያ የሚያደርግ #አፓርታይድ ስርዓት ወደ ስልጣን የመጣበትን ዕለት በማሰብ ልክ እንደ ልደቴ “ሻማ ካላበራህ፥ ኬክ ቆርሰህ ካልጨፈርክ አሸባሪ ነህ” አልከኝ… ያለ ጥፋቴ ስቃይና መከራ ሲደርስብኝ “እሰይ… የእጅህን ነው ያገኘህው” አልከኝ! “ኧረ…በእጄ የማንም ሰው ህይወት ጠፍቶ አያቅም!” እያልኩ ስማፀንህ ያለ አንዳች ርህራሄ መከራዬን አጠናህብኝ፣ የስቃዬን አግባብነት ነገርከኝ፣ ያለ ፍርድ ሞቴን ተመኘህልኝ!!!…… ታዲያ ዛሬ ወዳጄ መከራ፥ በደል፥ ጭቆና፥ ሞት፥ እንደመጣብህ ሰማሁኝና “እሰይ…ቅመሰው!” አልኩኝ! ይህን በማለቴ አጠፋሁኝ…እስኪ ንገረኝ?? በምን ሞራል ልትዳኘኝ? ከየት፥ መቼ፥ ለምን፥ እንዴት ባመጣህው ስብዕና ልትፈርደኝ??… ንገረኝ…እስኪ ንገረኝ???

Filed in: Amharic