>

የትግራይ የበላይነት አለ? የለም? የሚለው ቀልድ መቆም አለበት። የትግራይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ ( አፓርታይድ ) ነዉ ያለዉ!!! (ሃራ አብዲ)

ሶስት ባልንጀራሞች ሲሄዱ ሲሄዱ ውለው ደክሞአቸው ከዛፍ ስር ጋደም እንዳሉ እንቅልፍ ይዋስዳቸዋል።ለሊት ላይ አንደኛዉ «ቆርጠም፣ቆርጠም» የሚል ድምጽ ሲሰማ ፣ከጎኑ የተኛዉን «ወንድሜ ሆይ፣ የምሰማዉ ድምጽ ምንድን ይሆን»? ሲል ይጠይቀዋል።ሰዉየዉም ወደ ጆሮዉ ተጠግቶ «እረ ዝም በል! ጅቡ የኔን እግር እየበላ ነዉ» ብሎ መለሰለት ይባላል። ከዚያ በላይ ምን እንደሚጠብቅ ሲገርመኝ የሚኖረዉ፤ የዚያ መንገደኛ ነገር፤ እኛም ህወሃት ምን እስኪያደርገን ድረስ እንደምንጠብቅ ሲገርመኝ ይኖራል።

የህወሃት የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ፣ ሃያ ሰባተኛ አመቱን፣ ባገባደደበት ባሁኑ ወቅት እንኩዋን ሳይቀር፣ ስለ ትግራይ የበላይነት መኖር ፣አለመኖር ገና የጦፈ ክርክር ስንጋጠም ምን ነካን? ያሰኛል። የአፓርታይዱ ተባባሪዎች፣ ደጋፊዎች እና የዋሆች ደግሞ፣ የበላይነቱ፣ ካለም፣ የህወሃት የበላይነት ነው እንጂ፤ የትግራይ የበላይነት የለም ብለዉ ያደናግራሉ።በእውነቱ የህዝባችንና ያገራችን ነገር እንዲህ ውሉ እንደጠፋበት ክር ውስብስብ ባለበት
ጊዜ መፍትሄው ቀርቶብን፣ የችግራችንን ምንጭ በቅጡ አለመረዳታችን በእጅጉ ያሳዝናል።

እስኪ የህወሃት አፓርታይድ ስርአት በሃገራችን መኖር እንዴት ይገለጣል? ከአንድ ጎሳ የበላይነት በዘለለ መልኩ፣ አንድ ስርአት ፣የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ፣(internal colonialisim) ነዉ የሚያስብለዉ አለም አቀፍ ትንታኔስ ምን ይመስላል? የሚሉትን እንመልከት።

ለብዙ ጊዜ፣ይህን ርእስ ሳብሰለስል፣ ባጋጣሚ ትኩረቴን ስቦት ያነበብኩትን ግሩም የምርምር ጽሁፍ ምንጭ መጥቀስ ፣ግዴታየም ፣ ደስታየም ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
A Quiet Case of Ethnic Apartheid in Ethiopia  ‘Internal Colonialism and Uneven Effects of Political, Social, and Economic Development on a Regional Basis’

በሚል ርእስ ፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑ በኢትዮ ሚዲያ ላይ ጃንዋሪ 10, 2018 ያሰፈሩት ጽሁፍ፣ በሀገራችን ስለተንሰራፋዉ የአንድ ጎሳ የበላይነት፣ብሎም፣የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ፣ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በዚህ አጋጣሚ ለፕሮፌሰር  ግርማ ብርሃኑ ያደረብኝን አክብሮትና ፣ ለስራቸዉ ያለኝን አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ። «የህወሃት አፓርታይድ አገዛዝ ነዉ ፣ያለዉ»፣ ስንል በቅድምያ የአፓርታይድ ስርአት መስፈርቶችን ማሳየት ይገባል።

ከፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑ የእንግሊዝኛ ጽሁፍ ቀንጭብ አድርጌ እንደሚከተለዉ ላካፍላችሁ።

«to explain how persistent and pervasive inequality and domination in
all aspects of life are maintained in a society when there is not necessarily a foreign power ruling. An internal colony — in this case the rest of Ethiopia excluding Tigrean region — produces wealth for the benefit of those areas most closely associated with the regime, its allies, and the ethnic constituency the rulers claim to represent. So it is a form of colonialism originating from within a country»

የፕሮፌሰር ግርማን ጽሁፍ ያላነበባችሁ ሙሉ ጽሁፉን ኢትዮ ሚዲያ ላይ ማግኘት ትችላላችሁ። የጽሁፉን የአማርኛ ትርጉም ወደፊት ከጸሃፊው የምንጠብቅ ሲሆን ፣ ለአሁኑ፣ ባጠቃላይ ካገኘሁት ግንዛቤ በመነሳት የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ እንግዲህ፤የዉጭ ወራሪ ሳይመጣ፣ የሀገር ተወላጅ በሆነ ጎሳ ወይንም ቡድን በመላዉ ሀገር ላይ የሚሰፍን ስርአት ነዉ። ማለትም፤ ከሀገሪቱ ህዝብ መካከል ፣ ሃይል ያለው ፣ገዢ ቡድን (ጎሳ)ለኢኮኖሚ የበላይነት ፣ሌሎቹን አናሳ ቡድኖች የሚበዘብዝበት ሲስተም ወይንም ስርአት ነዉ፣ ማለት ነዉ። በዚህ መሰረት፤ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)በያዘዉ የፖለቲካ፤ የሀገር መከላከያ ፤ የደህንነትና የስለላ መዋቅር የበላይነት የተነሳ፣ መላዉን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቁጥጥሩ ስር በማድረግ «እወክለዋለሁ» የሚለዉን ትግራይንና የትግራይን ህዝብ ለማበልጸግ ሌላዉን የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጥሮ ሃብት (resource)
የሰዉ ጉልበት እና ማንኛዉንም ለሀገር ጥቅም፣ በእኩልነት ሊዉል የሚገባዉን መዋእለ-ንዋይ አለአግባብ ትግራይን በከፍተኛ ደረጃ እያበለጸገበት ይገኛል ማለት ነዉ።የዚህም የመጨረሻ ግብ ታላቁዋን ትግራይን መመስረት ነዉ።

የትግራይን አጠቃላይ ገጽታ ለመለወጥ፣ የትግራይን ህዝብ ከድህነት አረንቑዋ ለማዉጣት፤ትግራይ ከሌላዉ የኢትዮጵያ ክልሎች ተለይታ በማናቸዉም የኢኮኖሚ መስክ እመርታ እንድታሳይ፤ ህወሃት ሌት ተቀን በትጋት እየሰራ ያለዉ፣ እንዲሁ በዘፈቀደ፣ እግሬ ቤተ-መንግስት ካስገባኝ አይቀር ፣ለትውልድ ሀገሬ ለትግራይ ዉለታ ልስራላት ብሎ አይደለም።ይልቁንም፤ ገና ህወሃት በጫካ ትግል ላይ በነበረበት ጊዜ እቅድ ነድፎ ፤በእቅዱ መሰረትም የትግራይ ህዝብ ጠላት ነዉ የሚለዉን ነገድ (ጎሳ)እና ሃይማኖት በስም ጠርቶ ፣እነዚህን ጠላት ናቸዉ ያላቸዉን የህብረተ-ሰብ ክፍልና ሃይማኖት እንዴት ሊያጠፋቸዉ እንደሚችል ፣በደንብ አስቦበት፣መርሃ-ግብሩንም በማኒፌስቶ ቀርጾ ነዉ በሻእቢያ መሪነት አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት የገባዉ።

እዚህ ላይ ልብ ልንለዉ የሚገባን ጉዳይ፤ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ ስርአት የሚንሰራፋዉ፤ ዶሚናንት የሆነዉ የህብረተሰብ ክፍል አናሳዉን የህብረተሰብ ክፍል በመበዝበዝ ሲሆን፤ በሀገራችን ግን አናሳዉ የትግሬ ነጻ አዉጭ ቡድን ነዉ መላዉን የኢትዮጵያ ህዝብ (የትግራይን ህዝብ ሳይጨምር ) በጉልበት ረግጦ የዉስጥ ቅኝ ግዛት የመሰረተዉ።
በዚህም ምክንያት፤ የዉስጥ ቅኝ ግዛትን ትርጉም ቀይሮታል ባይ ነኝ። ይሁን እንጂ፤ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን ከነባራዊዉ የሀገራችን እዉነታ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠን የትግራይን አፓርታይድ፣ ገለጥለጥ አድርገን እያየነዉ ስለሆነ በተባበረዉ ትግላችን ይህን የዉስጥ ቅኝ ገዢ አንኮታኩተን ስንጥል ፣ያን ጊዜ፣ የአፓርታይድን ትርጉም አሻሽለን ለአለም እናስተወዉቃለን። ለአሁኑ ያረረብንን እናማስል!!

ይህን ጽሁፍ ገታ አድርጌ ዶክተር በያን አሶባ ለገበታ ሚዲያ የሰጡትን ቃለ ምልልስ በቴሌቪዢን ስመለከት አንድ ነገር አስተዋልኩ። ዶክተር በያን በገለጻቸዉ መካከል በጣም ጥንቃቄ በተመላዉ ሁኔታ ፤የህወሃትን አገዛዝ፣ እንደ ባእድ እንደሚገዛ እንጂ፣ እንደ ሀገር ተወላጂ ሀገር እንደማያስተዳድር ገልጸዉ «በስሙ ልጥራዉ፤ ቅኝ ገዢ ነዉ» በማለት ሲገልጹ አዳመጥኩና ትንሽ አሰብ አደረግሁ። ምናልባት፤ የህወሃትን አገዛዝ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ መሆኑን አስረግጠንና፤ ከዳር እስከዳር ተነቃንቀን፤ በዚህ የዉስጥ ወራሪ ላይ ያልዘመትንበትና ያላስዘመትንበት ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? ስል አሰብኩ። የሚያስፈራ ነገር ይኖር ይሆን?

ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በዘመናችን ሙሉ ያስጠቃን ጊዜ ቢኖር የወያኔ I አፓርታይድ ዘመን ነዉ።

በግል እይታዬ ህወሃት የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ (አፓርታይድ) በሀገራችን እንዳሰፈነ በእርግጠኝነት እናገራለሁ። ከላይ እንደገለጽኩት ፣ የፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑን ጽሁፍ ለማንበብ መብቃቴ በእጂጉ ያስደሰተኝም ፣ለብዙ ጊዜ ሳሰላስለዉ የቆየሁት እዉነት ጥርት ባለ መልኩ ፤በብዙ ማስረጃ ተደግፎ ስለቀረበልንም ጭምር ነዉ።

ወደ ማጠቃለያዉ ስመጣ፣ «የትግራይ የበላይነት አለ? የለም ?የሚለው ቀልድ ታዲያ መቆም አለበት።» የትግራይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ( አፓርታይድ ) ነዉ ያለዉ»ያልኩትም የአፓርታይድ መገለጫዉ ወይንም  ትንታኔዉ የህወሃትን አገዛዝ ሙሉ ለሙሉ ስለሚገልጸዉ ነዉ!!

በሚቀጥለዉ ጽሁፌ የትግራይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ (አፓርታይድ ) ለመኖሩ አስረጂ ጭብጦችን ፤ለሃያ ሰባት አመታት የዚህን ስርአት ምንነት አጥርተን ለማወቅ ያልቻልንባቸዉን ምክንያቶች፤ ህወሃት የዘር ፖለቲካ ያራምዳል፤ የትግራይ የበላይነት አለ፣የህወሃት የበላይነት አለ፤ እያልን እንኩዋን በአንድ ድምጽ (unanimously) የስርአቱን በትክክል የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ መሆን መቀበል ያልቻልንበት የሚመስለኝን፤ ሃሳብ ይዤ እቀርባለሁ። እስከዚያዉ ግን ለረጂም ግዜያት የስርአቱን ምንነት ከመነሻዉ በደንብ ጨብጣችሁ ሃሳብ ስታስጨብጡ የነበራችሁ ወገኖቻችን በዚህ ላይ ሃሳባችሁን በስፋት እንድትገልጡና የትግራይ የበላይነት አለ? የለም? የሚለዉ ክርክር፤ በትግራይ አፓርታይድ መኖር ዙሪያ እንዲያጠነጥንና እዉነታዉ ስር እንዲሰድ እንድታደርጉ ጥሪ ላስተላልፍ እወዳለሁ። በዚህ ርእስ ላይ አስደማሚ ስራዉን ያካፈለን በእጅጉ የማደንቀዉና
የማከብረዉ፤ የመለስ ልቃቂት ደራሲ፤ ኤርምያስ ለገሰ ዋቅጅራ ነዉ። ኤርምያስ፤ ከቁጥር በላይ ዋቢ ባለዉ ስራዉ ፤ የስርአቱን ምንነት በትኖ ግንዛቤ አስጨብጦናል። ለወደፊትም በዚሁ እንደሚቀጥል ተስፋዬ ጽኑ ነዉ። የትግራይ አፓርታይድ መኖር፤ ፍርጥርጥ ፤ብሎ መነገሩ፤ መጻፉና በስፋት ለዉይይት መቅረቡ፤ ብዙ የሚቀይራቸዉ ጉዳዮችና የትግል ስልቶች መኖራቸዉ ሳይታለም የተፈታ ነዉ። ስለዚህ፤ የትግራይ የበላይነት
አለ? የለም የሚለዉ የጳጉሜ ዉሃ የሻረዉ አዚም ይልቀቀን። ይህ ነፍሰ-በላ ስርአት፤ እንደ ጅቡ እግራችንን ቆርጥሞ እየጨረሰን፤ በሹክሹክታ መነጋገሩ ፈጽሞ ያስበላናል እንጂ አይጠቅመንም።

ነጻነትዋና አንድነትዋ ተጠብቆ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

Filed in: Amharic