>
5:13 pm - Sunday April 19, 5018

ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር! (የታሪካዊው ሙዚቃ ድግስ ወፍ በረር ቅኝት)

ኤሊ ጃህ
.
እጅግ ከበዙ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ በማስታዋቂያ ብቻ ተገድቦ ያልቀረው ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር የተሰኘው የብላቴናው የሙዚቃ ኮንሰርት ወደ እውነትነት ተቀይሮ በስኬት ተጀምሮ በስኬት ተጠናቋል።የኮንሰርቱ አዘጋጆች /በተለይም ቴዲ አፍሮ/ ከሙዚቃ ኮንሰርቱ አንድ ቀን ቀደም ሲል በወልድያ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ እና እሱንም ተከትሎ በሞቱት ሰዎች ምክንያት ፕሮግራሙ እንዲሰርዝ ብዙ አላማ ካላቸው <አዛኝ ቅቤ አንጓቾች> በኩል የተከፈተውን ፕሮፖጋንዳ እንዳላየ ለማለፍ ተገደዋል።ሁሉን እሰማለሁ ካልክ ከሁሉም አትሆንም ወዳጄ።በዛሬ ጊዜ የላፕቶፓቸውን ኪቦርድ ለነገርና ለቦይኮት ያቀባበሉ የዘመናችን ተዋጋዊች ጋር አድመኝነት እንጂ ማስታዋል ብሎ ነገር የለም።ይህን የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት አርቲስቱና ተባባሪዎቹ ብዙ ድካምና መከራ ከፍለው ባህር ዳር በተገኙበት፣የመድረክና ተያያዥ ውድ ዝግጅቶች ባሉቁበት፣ብዙ የብላቴናው አድናቂዎች ከመላው ኢትዮጵያ ባህር ዳር በተገኙበት፣እጅግ ብዙ ትኬቶች ተሽጠው ባለቁበት አስራ አንደኛው ሰኣት ላይ የአባ ምን ገዴ ልጆች የራሳቸውን መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን አንድም ሳያዛንፉ እየከወኑና ጠቆር ያለ ማክያቶኣቸውን እየላፉ በሚነካኩት ሞባይላቸው በድፍረት የኮንሰርቱን መሰረዝ ጠይቀዋል።

ሁኔታው ወዳጄ ናቲ ማን ከወር አካባቢ በፊት ያጫወተኝን እንባ አስጨራሽ ገጠመኙን አስታወሰኝ።ናቲ መኪና አልባ ተከራይን ፈልጎ ማግኘት በሚቸግርበት አንድ የሸገር ኮንዶሚኒየም ብሎክ ነበር እሚኖረው።የኮንዶሚኒየሙ ግቢ ሁሌም በጊዜ በተከራዮቹ መኪና ጥቅጥቅ ብሎ ይሞላል።በሆነ ቀን ናቲ ወደ ጊቢው ሲገባ ከፊቱ ሌላ ባለ መኪና ቆሟል።የብሎኩ ዘበኛ ሰውየውን የጊቢው መኪና ማቆሚያ ስለሞላ ውጭ እንዲያሳድራት በማመናጨቅ እጁን እያወናጨፈ ነገረው።ይሄኔ ሰውየው መስኮቱን ዝቅ አድርጎ ዘበኛውን ጠርቶ የሚከተለውን ብሎታል።

<<እንደው የአስር ብር ኮንጎ ጫማህን ውጭ እማታሳድር ሰውዬ አፍህን ሞልተህ የሚሊየን ብር መኪናን <ውጭ አሳድር> ስትል አይቀፍህም?>>

ምን ለማለት እንደፈለግኩ ይገባችኋል እሚል ትልቅ ተስፋ አለኝ።
.
የሆነው ሁሉ ሆኖ ቴዲ አፍሮ እጅግ በበዛ መሬት አንቀጥቃጭ የህዝብ ፍቅር ታጅቦ ድግሱን ከውኗል።ድግሱም <ባህር ዳር Are you ready> ከሚለው ከብዙ ናፍቆት በኋላ ከተሰማው የብላቴናው ድምፅ ሶስት አራት ሰኣት ቀድሞ በኢትዮጵያዊነት ቀለማት እጅግ አሸብርቆ ቆይቷል።ከፍቅርና አንድነት ግምጃ ተራቁተን ባዶ በቀረንበት በዚ ዘመን እንደ ኢትዮጵያዊ የቀረን አስተሳሳሪ ምልክት አንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን ስታይ ሆድ ይብስሃል።እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖር እና እንደ ኢትዮጵያዊ መዘመርን ለተጠሙ ሁሉ ግን ምሽቱ በቀላሉ እሚረሳ ሆኖ አላለፈም።በተለይም ባንድ አጋጣሚ ወደ ስታዲየሙ በተወሰኑ ወጣቶች አማካኝነት የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ሲገባ የተሰማው የህዝብ ድጋፍና ጭፈራ ልብን አብዝቶ እሚያሞቅ ነበር።ጭብጨባና ድጋፉን ተከትሎም <<ኦሮሚያ ኦሮሚያ>> የሚለው የቀመር የሱፍ ዜማ በህዝቡ አንደበት በጋራ ተዚሟል።ወዲያውም ከመድረኩ የአሊ ቢራ ሙዚቃ ተከፍቶ በአንድነት ተጨፍሮበታል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው ኮንሰርት ወደ ሁለት ሰኣት አቅራቢያ ከብዙ ጥበቃ ትዕግስትና ፈተና በኋላ የተናፋቂውን <ሰው!> ድምፅ ማሰማቱ አልቀረም።

<<Bahir dar, are you ready?>>

ወዳጄ ልክ እንደኔ የመሬት መንቀጥቀጥን በህይወትህ አይተህ እማታውቅ ከሆነ በዚህች ሰአት በዚህች ቦታ ባለመገኘትህ ልታዝን ይገባሃል።ቃላት በማይገልፀው ጩኸት ሆታ ግፊያና አጀብ ብላቴናው እጅግ ያሸበረቀ ደማቅ መስቀል ከፊቱ ባተመ ቲሸርት ውስጥ ገብቶ አፍሪካዬ እያለ ወደ መድረኩ መጣ።እዚህ ጋር ዝም ልበል።ምክንያቱም የሆነውን የተሰማውን የነበረውን በቃላት መግለፅ አልችልማ።

አዝናለሁ!

ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች የብላቴናውን የሙዚቃ ድግሶች ታድሜኣለሁ።ሁሉም ጋር ከህዝቡ ለአርስቲቱ የሚሰጠው ድጋፍና ፍቅር ሌላ ነው።የትላንቱ ግን የተለየ ነበር።ቴዲ ወደፊትም ይሄን በመሰለ የህዝብ የፍቅር ባህር ውስጥ ሰምጦ መዝፈኑን እጠራጠራለሁ።እያንዳንዱ ሙዚቃ አልቆ ወደ ቀጣዩ የመሻገሪያ ፋታ መሃል <ቴዲ አንደኛ ቴዲ የአንድነት መንፈስ> እሚሉ የህዝብ መዝሙሮች ጥርት ብለው ይሰሙ ነበር።አርቲስቱም በመሽኮርመምና በመደነቅ ለሁሉም ድጋፍ እና ፍቅር ሲያመሰግን አምሽቷል።ባንድ አጋጣሚ ሞቅ ካለ <<እድሜና ጤና ለቴዲ>> ከሚል ጭፈራ በኋላ ቴዲ ራሱ ረጅም እድሜ ለሁላችን ሲል መርቋል።

የትላንቱ ኮንርሰት በሙዚቃ ጥራት በኩልም ሊመሰገን እሚገባው ነበር።አቡጊዳ ባንድ የሳክስፎን ትራምፔትና መሲንቆ ተጫዋቾችን እንደ አዲስ ጨምሮ ተገኝቷል።ከሮቤልና አበራ በተጨማሪም ሌላ ሶስተኛ የሊድ ጊታር ተጫዋች አክሏል።ሩፋኤል ያልተገኘበት ከበሮ በሁለት ወጣቶች ሲደለቅ አምሽቷል።ባንዱ የስቱዲዮን <ኢፌክት> ለማምጣት በተጠጋ ውጤታማ <አኪውሬሲ> ሙዚቃውን ሲጫወት አምሽቷል።ብላቴናው አፍሪካ ግርማዊነቶና ጥቁር ሰውን ካለፉት አልበሞች ላይ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሰምበሬ ማር እስከ ጧፍ አናኛቱ ያምራል ታሞልሻል እማ ዘንድ ይደር ቴዎድሮስና ማራኪዬን ካዲስ አልበሙ ተጫውቷል።በተለይ አርቲስቱ አናኛቱ ሰምበሬ ኢትዮጵያ ማር እስከ ጧፍና ቴዎድሮስን ሲጫወት የነበረው የህዝቡ የዝማሬ እና አንድነት መንፈስ ለጉድ ነበር።

/Some awkward moments  /

ኮንሰርቱ በሁለት ምዕራፍ የተከወነ ነበር።በመሃል ቴዲና ባንዱ ለእረፍት ሲውርዱና በድንገት የዲጄው የሙዚቃ ግብዣ በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሲቋረጥ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፅች ከተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች መደመጥ ጀመሩ።እንዲህ ያለውን የተቃውሞ መንፈስ ብዙም የፈለጉት እማይመስሉት የአርቲስቱ የቅርብ ሰዎች በተለይም ማኔጀሩ አቶ ጌታቸው ወደ መድረኩ ጫፍ ወጥቶ ዲጄውን ሲያመናጭቅ ተስተውሏል።በሙዚቃ ያዝልን አይነት ነው ነገሩ።ይህ ትዝብት ግን ፍፁም እውነት ሳይሆን ከመድረኩ በቅርብ ርቀት የተገኘ ያንድ ታዳሚ አረዳድ ነው።ያም ሆኖ የተቃውሞ ድምፆችን ማየል ከመድረክ ጀርባ /ባክ ስቴጅ ነው እምትሉት?/ ሆኖ የሰማው አርቲስቱ በተለመደ የሃይል መልዕክቱ እዛው ከመድረክ ጀርባ ሆኖ ትህትናን ባጀበ ድምፅ <<ፍቅር ያሸንፋል!!!>> ሲል አረጋግቷል።

ቴዲ ዘፋኝ ብቻ እንዳልሆነ ለመመስከር እንዲህ ባሉ አስጨናቂ ገጠመኞች መሃል መገኘትን ይጠይቃል።

ነገረ ጃ ያስተሰርያል

የጃ ጣጣ ልላ የመድረክ ላይ ድራማ አሳይቶን አልፏል።ህዝቡ ከመጀመርያው ጀምሮ በእያንዳንዱ የሙዚቃ ፋታ መሃል ጃ ያስተሰርያልን ሲጠይቅ ነበር ያመሸው።አርቲስቱ ወደ መጨረሻ ዝግጁቱን በጥቁር ሰው ሊዘጋ በሚሰናዳባት ሰኣት ግን የህዝቡ ጥያቄ አይሎ የሙዚቃው ግጥሞች ከፍ ባለ ድምፅ በዜማ ይሰሙ ጀመር።

ግርማዊነታቸው ከዚህ ሰረገላ
ወደ ዋገን ወርደው ሲተኩ በሌላ…

ከዚህ በኋላ የሆነው አስፈሪ አስደንጋጭ በተወሰነ መልኩም አስቂኝ ነበር።

ቴዲ ህዝቡን ጠየቀ።

<<ያስተሰርያል ይዘፈንላችሁ?>>

ህዝቡ ከባህር ዳር ጎንደር ድረስ በሚሰማ ሃይለኛ ድምፅ <<አዎ>> አለ።ብላቴናው ፊቱን አዙሮ ከጊታር ተጫዋቾቹ ጋር አጭር ምክክር ካደረገ በኋላ ወደ ህዝቡ ዞረና
<<እዘፍንላኋለሁ>> አለ።በዚ መሃል ሁኔታውን ከዳር ሆኖ ሲመለከት የነበረው በቁጣና ብስጭት አቅሉን የሳተው የአርቲስቱ ማኔጀር መድረክ ሰብሮ ገባ።<እናንተ ናችሁ አማክራችሁ ዝፈን ያላችሁት> በሚል ይመስላል በዛ ሁሉ ህዝብ ፊት የጊታር ተጫዋቾቹ ጋር ሃይለኛ ጭቅጭቅ ውስጥ ገባ።ቴዲም ፈገግ እያለ ጭቅጭቁን እንደኛው በዝምታ ታድሟል።መድረኩ ለሰኣታት ሰፍኖበት ከቆየው ሰምላና ፍቅር በቅፅበት በውጥረት ተሞላ።በዚ መሃል ህዝቡ <<ቴዲ አይፈራም>> እያለ መጮህ ጀመረ።ቴዲም ወደ ህዝቡ ዞሮ መለሰ።

<<እኔ ፈርቼ አላውቅም>>

ሌላ ሆታ ሌላ ጭፈራ።ጌታቸው ስድቡን እና ብስጭቱን አራግፎ ከመድረክ ወረደ።አርቲስቱም ጃ የፍቅር የይቅርታና የእርቅ መልዕክት መሆኑን ነግሮ ነገር ግን ማንም እንዲከፋው ስለማይፈልግ ድግሱን በጥቁር ሰው መዝጋቱ እንሚሻል በትህትና አስረድቶ ዝግጅቱን በባልቻ ከውኖ ህዝቡን አመስግኖ ከበዛ ድጋፍና ፍቅር ጋር ታጅቦ ከመድረክ ወርዷል።
.
ፍቅር ያሸንፋል!
#ሰላም_ለሰው_ልጆች_ሁሉ!

Filed in: Amharic