>
5:13 pm - Friday April 19, 9326

ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ! (ያሬድ ጥበቡ)

የትግራይ ህዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ/ወያኔ) መለስተኛ ጉባኤ ወይም ኮንፈረንስ ማጠቃለያ ላይ አቶ ስዩም መስፍን ባደረገው ማሳረጊያ ንግግር ላይ “እያንዳንዱን የአመራር አባል እርቃኑን አቁመን ገምግመነዋል፣ ቆዳውን ገፈን ውስጡን ማየት እንጂ ነው የቀረን” ብሎ ሲናገር ሰማሁት ። ስዩም በመቀጠልም ቻይናዎች እንኳ ወሰን አላቸው፣ ዳራ አላቸው፣ ኮንፊዩሻኒዝም የሚባል ፍልስፍና ። ግለሰቡ ክብሩ ከተነካ ራሱን ያጠፋል ብለው ስለሚፈሩ የማይሻገሩት ወንዝ አለ ፣ እኛ ግን ያንንም ተሻግረናል የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ነው ያሰማው ። ይህን ስሰማም ነው ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስን ያስታወሰኝ ።

እውን ወያኔ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን የሂስና ግለሂስ ዳራ አልፎ በሰራቸው ስህተቶችና ምናልባትም ወንጀሎች ላይ በግልፅ መወያየትና እርማት ማድረግ ችሏልን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ትናንት ወደተጠናቀቀው የወያኔ መለስተኛ ጉባኤ መድረክና ዝግጅት መመለስ እንገደዳለን። በራሳቸው እምነት ቃል እንኳ 43 ዓመታት በስብሰን ነበር ካሉና ፣ የመበስበሱም ዋነኛ ሞተር ከማእከላዊ ኮሚቴውም አልፎ  የበላይ አመራር የሆነው ሥራአስፈፃሚ ኮሚቴ ነው ብለው ለዓለም ካወጁ፣ እንዴት ነው እንዲህ አይነት አረንቋ ውስጥ የሰመጠ የፖለቲካ ስብስብ በመለስተኛ ጉባኤ ለችግሩ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው? ጠቅላላ  የድርጅቱን አባላት ለጉባኤ ከመጥራት ይልቅ ለምን መለስተኛ ጉባኤ መጥራተ ተመረጠ? ወያኔ ጉባኤ ለመጥራት ለምን አልደፈረም?

የወያኔ አመራር የትግራይ ክልልን ህገመንግስት በመጣስና የክልሉን ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ወይም ህዝባዊ ባይቶ ፈቃድ ሳያገኝ፣ የክልሉን ፕሬዚዳንትና ምክትሉን ከሥልጣን በማውረድ በምትካቸው የክልሉ ተመራጭ ያልሆነውን ዶክተር ደብረፅዮንን ጎልቷል። በተጨባጭ መንግስታዊ የሥልጣን ግልበጣ አካሂዷል። የወያኔ አመራር 37 ቀናት የፈጀ ስብሰባ አካሂዶ ከፍተኛ አመራሩ ጉልህ ስህተቶች ፈፅሟል፣ ክልሉንና ሃገሪቷን ለአደጋ አጋልጧል ብሎ ከገመገመ በኋላ ፣ ተገቢው ምላሽ ጠቅላላ አባላቱን ያሳተፈ ድርጅታዊ ጉባኤ ጠርቶ የተፈፀሙትን ስህተቶች መመርመርና ከእርማቱም ጋር የሚጎዳኝ አዲስ አመራር ማፍለቅ ሲገባው፣ ስጋት አደረበት ፣ ብርክ ያዘው ። መውጫ መንገድም ፈለገ ። ኮንፈረንስ ማካሄዱም የተሻለ አማራጭ እንደሚሆን አሰላ።

ከአጠቃላይ ጉባኤ ይልቅ ኮንፈረንስ ማድረግ በአመዛኙ ነባሩን አመራር የሚጠቅም ነው ። ከአባላት በነፃነት በተቋቋመ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የሚካሄድ ባለመሆኑ፣ የኮንፈረንስ ተሳታፊዎቹንም ሆነ አጀንዳዎቹን የሚቆጣጠረው አመራሩ ነው ። ኮንፈረንስ ከካድሬ ስብሰባ ምንም ልዩነት የለውም፣ ከስፋቱ በቀር። የፖሊትቢሮው የወሰነውን በካድሬዎቹ ጉሮሮ በጉልበት ከመጠቅጠቅ ውጪ ፣ ለአዲስ ሃሳብና ክርክር ለአዲስ አጀንዳ ዝግ የሆነ መድረክ ነው። ስለሆነም ውጤታማ ሊሆን አይችልም። በተለይ “ሃገሪቷን ለከፍተኛ አደጋ አጋልጠናታል” በሚባልበት ሰአት ። በእንዲህ ያለ የአደጋ ወቅት እንኳንስ የመላ ድርጅት አባላትን ቀርቶ የተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችን ብሎም የአጠቃላይ ህዝቡን ተሳትፎ የሚጠይቅ ወቅት ነው ። ሆኖም ወያኔ ለዚህ አልታደለም ። ከዚህ በፊት ተሞክሮ በከሸፈ አሠራር መሄድን መርጧል ።

ወያኔ የክልሉን ህዝባዊ ባይቶ አክብሮ አዲስ ፕሬዚዳንትና ምክትሉን ማስመረጥ እምቢኝ ብሎ ወደ ክልላዊ መንግስት ግልበጣ እንዳመራው ሁሉ፣ ከድርጅታዊ ጉባኤም ይልቅ ወደ ካድሬ ስብሰባ ዘቅጧል ። ይህ ደግሞ በ1993 የአመራር ክፍፍል ወቅት፣ እነገብሩ አሥራትና የቁጥጥር ኮሚሽኑ ድርጅታዊ ጉባኤ እንዲጠራ አየለመኑ፣ መለስ በመቀሌ የካድሬ ስብሰባ የበላይ ሆኖ የወጣበትን ህገወጥ አካሄድ የሚያስታውስ ነው ። የድርጅት ጉባኤን በካድሬ ስብሰባ መተካት ደግሞ ዛሬ ወያኔ ለሚገኝበት መሽመድመድና ደካማነት የራሱን ጠባሳ ትቶ እንዳለፈ መታወቅ ነበረበት። ሆኖም ከጥፋቱ መማር የማይችለው ወያኔ፣ ዛሬ ደግሞ እነ አዜብ መስፍንን፣ አባይ ወልዱንና አዲሰ ዓለምን ጠልፎ በመጣል ለመመረሽ ሲታትር ይታያል። እነዚህ ግለሰቦች ለባለጉበት ሥልጣን፣ ላባከኑት የህዝብ ሃብት፣ ወይም ለገቡበት ሙስና ተጠያቂ አይደረጉም፣ ህግ ፊትም አይቀርቡም። እንኳንስ እነዚህ ትናንሾቹ ቀርቶ፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ በ77 ቢሊዮን ብር የህዝብ ሃብት ብክነት ተጠያቂ የሆነው አባይ ፀሃዬ እንኳ ያለፍርሃትም ሆነ ያለሃፍረት  የወያኔ ጎምቱ (party elder) ተብሎ አዳራሹ ውስጥ ተቀምጧል ። የጉድ ፓርቲ፣ የጉድ ሃገር። በአንፃሩ ታናናሾቹ ወንጀለኞች ገለል እንዱሉ ተሹመው ይሸኛሉ ። ድንቄም ጥልቅ ተሃድሶ። ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ አሉ ሴት አያቶቻችን።

ስዩም መስፍን ሌላም የተናገረው አለ ። “የበሰበሰች ወያኔ ታሰፈልገናለች…የበሰበሰ ኢህአዴግም ቢሆን ያስፈልገናል” ብሏል ። በስንት አመታት ድካምና እምባ የተደራጁ ድርጅቶችን በማፍረስ ከሚገኝ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናልና፣ በተሳሳቱበት እያረምን እንቀጥል ይመስላል መልእክቱ ። ተገቢ ባልሆነ የቃላት ምርጫ የታጀለ ቢሆንም። ኢህአዴግንም ሆነ ወያኔን በማፍረስ የሚገኝ ጥቅም የለም በሚለው ላይ ከስዩም ጋር እስማማለሁ። ምን ዓይነት ኢህአዴግ በሚለው ላይ ነው ልዩነታችን። ኦህዴድ መሄድ በጀመረበት ህዝባዊ ጎዳና ለመሄድ የቆረጠ ኢህአዴግ መፍረስ የለበትም ። እንደ ለማ መገርሳ ህዝብ ህዝብና ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸት አመራር የያዘ ኢህአዴግ መፍረስ የለበትም ። ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ዶክተር አቢይ አህመድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር የሚያደርጉ፣ ስደተኞችን ወደሃገራቸው እንዲመለሱና ገላቸውን ሰደው በሃገራቸው የወደፊት እጣ  እንዲመክሩ የሚፈቅድ፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች የሚፈታና ወደሃገራዊ እርቅ የሚሄድ አመራር የጨበጠ ኢህአዴግ መፍረስ የለበትም ። ማእከላዊን ሙዚየም ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በማእከላዊ የተፈፀሙ ግፎችን የሚመረምር፣ ግፉን የፈፀሙትና አመራሩን የሰጡት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ፊት ቀርበው የተፈፀመው ወንጀል ሁሉ ለምንስና እንዴትስ እንደተፈፀመ የሚናገሩበትና ይቅርታም የሚጠይቁበት የፓርላማውን ነፃነት የሚያከብር ኢህአዴግ መፍረስ የለበትም። በእኔና በስዩም መስፍን ኢህአዴግ መሃል ያለው ልዩነት ይህ ነው ።

ደብረፅዮን በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ቀን ሲናገር ከተደመጠው፣ ስለቀጣዮቹ ተግባራት ሲያወሳ ተመሳሳይ ኮንፈረንሶች በእህት ድርጅቶች ውስጥ በማካሄድ ጥልቅ ተሃድሶውን መቀጠል የሚል ሃሳብ ሰንዝሯል ። “ደብረፂ” የሚያስበው፣ ልክ እርሱ በመንግስት ግልበጣ የትግራይ ፕሬዚዳንት እንደሆነው ሁሉ፣ በኦሮሚያም ጨፌ ኦሮሚያን ሳያማክር፣ በአማራ ክልልም ህዝባዊ ሸንጎውን ሳያማክር በካድሬዎች ስብሰባ ለማና ገዱን ማውረድ ሊሆን ይችላል። ይህ ግን የማይታሰብ ነው ። ኦህዴድና ብአዴን ወያኔን አልፈው ብዙ ተጉዘዋል። እነዚህን መስመሮች ስተይብ የፌስቡክ ገፄ ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፈረስ ላይ ተቀምጦ፣ በጎንደር ወጣቶች ዙሪያውን ተከቦ ይታየኛል ። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ዶክተር መረራ ከሙስሊም ኦሮሞ ምሁራን ጋር ሲመካከር የሚል ሌላ ምስል ይታየኛል። ወያኔ መቀሌ ላይ ሥልጣኑንና የዘር መድልኦ አገዛዙን እንዴት ማቆየት እንደሚችል ሲሸርብ ፣ ኦህዴድና ብአዴን ከህዝቡ ፍላጎት ጎን ለመቆም መምረጣቸውን የሚያሳዩ ምስሎች ናቸው ።

ኢህአዴግ ምርጫ አለው። መቀሌን መከተል ሊገደድ አይችልም። በአንፃሩ ኢህአዴግ የደብረፂ የሥልጣን አመጣጥ የትግራይን ህገመንግስት የሚጥስ በመሆኑ፣ በአስቸኳይ እርማት እንዲደረግ ማዘዝ ይችላል። ከዚህም አልፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውስጥ የትግራይ መንግስት ግልበጣ ጉዳይ አጀንዳ ተደርጎ ተይዞ በአፋጣኝ እርማት እንዲደረግ ግፊት ማድረግ ይቻላል ። እነዚህም እርምጃዎች በወያኔም ውስጥ ሆነ በትግራይ ውስጥ ያሉ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች አንገታቸውን እንዲያቀኑና “ከአናቴ በስብሻለሁ” ብሎ ያመነውን በሙስናና ዘረኝነት የተጨማለቀውን አመራራቸውን በአዲስና ወጣት አመራሮች እንዲተኩ መንገዱን ሊጠርግላቸው ይችላል። ይህም ለአስርት ዓመታት ለናፈቅነውና ለደከምንለት ሃገራዊ እርቅ መዳረሻ በመሆን፣ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር ያስችለናል ። እንዳሁኑ ዓመት ስለሃገሬ በጥልቅ ተስፋ ተመልቼ አላውቅም። ብርሃኑ ይታየኛል።

Filed in: Amharic