>

ከአፋችን ይልቅ ተግባራችን ለለውጥ ያለንን ፍላጎት ያሳይልን! (ዮናስ ሃጎስ)

የዘገየም ቢሆን እንኳን አደረሳችሁ ማለት ነወር አይሆንም። የሚካዔል ታቦታ ባቅራቢያችሁ ላለ ምዕመናን ደግሞ በዓሉ ገና አላለቀም። ባህር ዳር ላላችሁና 350 ብር የመግቢያ ትኬት afford ማድረግ ለምትችሉ ደግሞ በዓሉ ገና አልጀመረም። ማታ ቴዲ አፍሮ «ኢትዮጵያዬ!» ሲል ነውና የሚጀምረው ለሁላችሁም እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን!

•°•
ወደ ፖለቲካው ዓለም መለስ ስንል ሁለት ነጥቦችን ለማንሳት እፈልጋለሁኝ…
•°•
1) ትዕግስት መንግስቱ ሐይለማርያም ሰሞኑን በለቀቀችው ቪድዮ ላይ የአባይን ግድብ አስመልክቶ የሆነ ሐሳብ አንፀባርቃለች። ሐሳቧን ባልጋራውም ቅሉ ሐሳቧን እንደኔው የተቃወሙ ኢትዮጵያውያን በመንግስቱ ሐይለማርያም ልጅነቷ ብቻ ተመርኩዘው የሰነዘሩትን ስድብ አዘል ምላሽም አብሬ እቃወማለሁኝ። የመንግስቱ ሐይለማርያም ልጅ ሆነችም አልሆነችም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የራሷን ሐሳብ የማንፀባረቅ መብቷ ሊከበርላት የግድ ነው። እንዲህ የሰውን ማንነት፣ ብሔር፣ የመጣበትን አካባቢ፣ ምናምን እየተንተራስን የሰውን ሐሳብ ለማጣጣል መሞከር እንታገልለታለን ከምንለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ከማስፈን ሂደት ጋር ምን ያህል ተቃርኖ እንዳለው መረዳት ለምን እንደሚከብደን አላውቅም። አይደለምና ትዕግስት መንግስቱ፤ ራሱ መንግስቱ ሐይለማርያም ሐሳቡን ቢሰነዝር ሐሳቡ ከየት መጣ ሳንል ሐሳቡን ብቻ ተንተርሰን ውድቅ ማድረግ መቻልን ካልለመድን ዴሞክራሲ እያልን አስር ጊዜ መለፍለፉ ምንም ዋጋ አይኖረውም።
•°•
ወደ ሐሳቧ ስመጣ አጠቃላይ ስሜቱ አባይ ለግብፅ ሕልውናዋ ስለሆነ እንተውላት… የሚል ነገር ነው። ያ ደግሞ የሚያስኬድ ሐሳብ አይደለም። ግድቡ ሲታሰብ ብዙ ያልተጠኑ ነገሮች አሉ ምናምን ሁሉ ተብሏል። እኔ በዚያ ዙርያ ባለሙያ ባልሆንም በግል አስተያየቴ የአባይ ግድብ በግብፅ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችለው ግድቡ ውኃ እስኪሞላ ባለው ጊዜ ብቻ መሆኑን አሳምሬ አውቃለሁኝ። አንድ ጊዜ ግድቡ ውኃ ከሞላ በኋላና ሐይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ ግን ወደ ግብፅ የሚኖረው የአባይ ፍሰት ዛሬ እንደሚፈስሰው መሆኑ ይታወቃል። እንዲያውም ከግብፅ በላይ የአባይ ግድብ ስጋት ሊሆንባት የሚገባው ሱዳን ናት። የአባይ ግድብ ውኃውን ተሞልቶ ስራ ከጀመረ በኋላ በማንኛውም አጋጣሚ ግድቡ የያዘውን ውኃ ቢለቅቀው በአርባዎቹ ኪሎሜትሮች ርቀት የምትገኘው ሱዳን ከአቅሟ በላይ የሆነ መጥለቅለቅ ሊገጥማት ይችል ይሆናል። (ልብ በሉ ግምት እንጂ ባለሙያዊ አስተያየት አይደለምና ልታረም እችላለሁኝ) ከዛ ውጭ ግድቡ እስከሚሞላ ድረስ ያለውን የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ግብፅ ራስ ወዳድነት ካልታየባት በቀር መስማማት የሚያቅት አይመስለኝም።
ከዛ ውጭ ግን አባይ ለሶስቱም ሐገራት የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ግብፅ የአባይ ሙሉ ተጠቃሚ በመሆኗ ስልጣኔን ከኢትዮጵያና ሱዳን አስቀድማ ልትይዝ በቅታለች። እነ ሱዳንና ኢትዮጵያ ግን በዚህ «የሕልውና» ወሬ ታስረው አባይን በጭልፋ ለእርሻ ስራ መስኖ ብቻ እየተጠቀሙ ሲኖሩ ዘመናት ተቆጥረዋል። ወያኔ የአባይን ግድብ ለፕሮፖጋንዳነት የሚያውልበት ጉዳይ አስቂኝ ይሁን እንጂ የአባይ ግድብ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ትቶት የሄደው ሌጋሲ መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም። አፄ ሐይለስላሴ የአባይን ግድብ ስራ አስጠንተው የተዉበት ምክንያት ትዕግስት እንዳለችው «ጠቃሚ ስላልነበረ» ሳይሆን የወቅቱ አጠቃላይ ሁኔታችን ግብፅ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያስችለን አቅም ስላልነበረን ብቻ ነው። መለስ ዜናዊ የተጠቀመው ያቺን ግብፅ በአብዮት የተተራመሰችበትን ቅፅበትና ክፍተት ነው። ከዛ ውጭ ከኛው ሐገር የሚመነጨው የአባይ ወንዝ ላይ ሌሎቹ ስልጣኔ እየገነቡ «ለኛ ጠቃሚ አልነበረም…» ብሎ ማጣጣል ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ ነው።
ከዛ በተረፈ የአባይ ግድብ የወያኔ/ኢህአዴግ ሳይሆን የኢትዮጵያ ካርታ መሆኑን አጥብቀን ልንገነዘብ ይገባል። የአባይ ግድብ በቦንድ ስም የብዙ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ያረፈበት፤ ይሄ መንግስት ወድቆ ቀጣዩም መንግስት ሲወድቅ በቦታው ፀንቶ ሐገሪቱን ማገልገሉን የሚቀጥል የኢትዮጵያ ሐብት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን የፈለገ የሐገር ውስጥ ልዩነቶች ቢኖሩንም ቅሉ የውጭ ወራሪን በተመለከተ ስብጥር አቋም እንደሌለን ግልፅ ነው። የውጭ ወራሪ የሚወርረው መንግስትን ሳይሆን ሕዝብን መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ከውጭ የመጣ ወራሪ ሐይል መንግስት ይጥልልናል የሚል ቀቢፀ ተስፋ የሚኖረን ሰዎች ልንኖር ብንችልም ቅሉ ከገዢው መንግስት ውድቀት በኋላ ልትኖረን ስለሚገባው ሐገር ላይ የጋራ እይታችን አንድ ዓይነት ከሆነ ይህ ዕይታ በውጭ ወራሪ ሐይል መቼም ሊመጣ እንደማይችል ልናውቀው ይገባልና በአባይ ጉዳይ ከማንኛውም የውጭ ሐይል ጋር የተለየ ስምምነት ማድረግ በዚህም ሆነ በሚመጣው አዲስ መንግስት በሐገር ክህደት ሊያስጠይቅ የሚገባው አቋም መሆኑ ቢታወቅ መልካም ነው።
•°•
ትዕግስትን ስንቋጭ የምናገኘው ብዓዴንን ነው። ብዓዴን በዛሬው ምሽት በባህር ዳር የሚካሄደውን የብላቴናውን የሙዚቃ ድግስ መፍቀዱ አንድ ትልቅ እመርታ መሆኑን ለመናገር እወዳለሁኝ። አዎ ዴሞክራሲ ማለት ልንሰማው የማንፈልገውን ነገር ሰዎች የማሰማት መብታቸውን እስከ መጨረሻው መታገል ነውና አዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች አንሰማም አናሰማም ብለው የከለከሉትን ነገር ብዓዴን እንሰማለን እናሰማለን ብለው መፍቀዳቸው ጥሩ ጅምር መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁኝ። በዚያ ላይ ቴዲ ፍቅር የሆነ ልጅ ነው። ስለ ፍቅር ሲባል ስለ ፀብ ካወራን ተሳስተናል እንዳለው በትልቁም በትንሹም ፀብ ፀብ የሚሸተው መንግስት መጨረሻው እንደማያምር ገዢዎቻችን ሊረዱት ይገባል። ብዓዴኖች አስቀድማችሁ ስለተረዳችሁት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
ታድያ ምስጋናውንና ደስታችንን ምሉዕ ማድረግ ከፈለጋችሁ በዛሬው ዕለት በሚጀምረው አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባችሁ እርስ በራሳችሁ እንደ ሕወሐት ወጥራችሁ በመገማገም ለለውጥ ዝግጁ ያልሆኑ ሕዝቡን ከመሳደብ ሌላ ፋይዳ የሌላቸው፣ ዥዋዥዌ የሚጫወቱትን እንደነ በረከት ስምዖን፣ አለምነው መኮንን መሰል አመራሮችን አሽቀንጥራችሁ በማስወገድ ለቀጣዩ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የበለጠ ተጠናክራችሁ ለለውጥ ቅረቡ። ለቴዲ ሙዚቃ መሰማት ያደረጋችሁት ትግል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ሕዝቡ ግን በትክክል ለለውጥ መነሳታችሁን ሊቀበለው የሚችለው እንደዚህ ዓይነት irriversable የሆኑ ለውጦችን ስታስመዘግቡ ነውና «ይህን አሉ…» ሳይሆን «ይህን ሰሩ…» ተብሎ የሚወራላችሁ ለመሆን እንድትሞክሩ እመክራለሁኝ።
•°•
ከአፋችን ይልቅ ተግባራችን ለለውጥ ያለንን ፍላጎት ያሳይልን! አለበለዚያ ያው ጨው ነው ተብሎ መጣል ይመጣል…

Filed in: Amharic