>

ዝዋይ ደርሶ-መልስ (ዳንኤል ስለሺ)

 እንደ መግቢያ፦ ዕሁድ ጥር 6ቀን፡ 2010 ዓም ወደ ዝዋይ ፌዴራል እሥር ቤት ተጉዘን ነበር፡፡ ሰኞ ጥር 7ቀን፡ 2010 ዓም የጠ/ዐ/ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ በቁጥር 528 እሥረኞች እንደሚፈቱ መግለጫ ሰጡን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 115 ያህሉ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ወደ 413 የሚሆኑት ደሞ ከክልል (በተለይም ከደቡብ) እሥር ቤቶች መሆናቸው የተነገረን ሲሆን፤ ከደቡብ ክልል ተፈቺዎች ውስጥ አብዘኞቹ የደኢህዴን አባላት የነበሩ (በሚ/ሩ መግለጫቸው ባይጠቀስም) ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አንድም የፖለቲካ እሥረኛ የለም ስሉን የነበሩት የአገዛዙ መሪዎች ዛሬ ተከርብተው የፖለቲካ እሥረኛ አለ/የለም እያሉ እየተወዛገቡ ይገኛሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ስለ ሥርዓቱ ብዙ ዕውቀት ያለን እኛ! ኢህአዴግን ማመን እንደት ይቻለናል? ለፍቺዩ መሥፈርትና ቅደመ-ሁኔታ ማስቀመጥን አሁን አሁን፤ ቀስበቀስ ይፋ እየሆነ ነው፡፡ እች ዝቅ ዝቅ ዕቃ ለማንሳት አይነት ይሁን? ሌላም ነጥብ መዝግበናቸዋል፡፡

በሽብር፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ በህቡዕ በመደራጀት፣ አመጽ በማነሳሳት ድርጊት የተሳተፉ ወዘተ ብለው እየከሰሱ፤ ወደ ፍቺው ሲሜጣ ደግሞ በሽብር፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል ለመናድ ወዘተ ድርጊት ውስጥ “…ያልተሳተፉ” በማለት መሥፈርት ማውጣታቸው ጥርጣሪያችንን ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ አገላለፃቸውም እርሱ የሚጋጭ መሆን በራሱ ሌላ ሥጋትን የሚጭር ነው፡፡

ከሥርዓቱ ባሕርይ አንፃር ቢያደርጉት እንኳ የሰብዓዊ ፍጡር ክብርና የዴሞክራሲያዊ መብት ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ መሆኑን ለመረዳት የእነርሱ ያህል የተደናበረን አይደለንም፡፡ የመጣባቸውን ናዳ ለመከላከል እንጂ፡፡ ስለዚህ የተሰጠው መግለጫ በፍጹም አያዘነጋንም!! ከኢህአዴጉ ሚኒስትር መግለጫ እንደተረዳነው ከሆነ ሁሉን የፖለቲካ (የኀልና) እሥረኞችን የሚፈቱት አይመስለኝም፡፡ ቢፈቱ እንኳ የፖለቲካ ትኩሣቶችን እየተከተሉና እየመዘኑ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደሞ ፍቺው <የዘገየ ፍትህ ነው> የሚሆነው፡፡

ስለሆነም ሁሉም የኀልና እሥረኞች እስካልተፈቱ ድረስ ብሄራዊ መግባባት እንዲፈጠርም ሆነ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ የመነጋገር ዕድል በእጅጉ ጠባብ ነው፤ ወይም ጨርሶ የለም፡፡

ዝዋይ ደርሶ-መልስ ፦
ስለ እሥር ቤት፣ ስለ እሥረኞችና ቤተሰቦቻቸው ባሰብሁ ቁጥር ቀድሞ በፊቴ ድቅን የምለኝና ውስጤን የሚያደማው የእሥረኞች መጎዳት ሳይሆን የየቤተሰቦቻቸው መንከራተት፣ ድካምና መከራ ነው፡፡ የፈታሽ ወታደሮች ማመናጨቅ፣ ስድብና ንቀት፣ የመንገዱ ርቄት፣ የትራንስፓርቱ ችግር፣ ወዘተ በፈጣሪ ላይ እንዲማረሩ ያደርጋል፡፡ እኛም ዝዋይ ሄደን ስንመለስ ይህ ዕጣ ገጥሞናል፡፡ ፀሃዩ፣ አቧራው፤ ፍተሻው፣ የደርሶ-መልሱ ጉዞውን ከበድ አድርገውብናል፡፡
እኔ (ዳንኤል ሺበሺ)፤
አቶ የሽዋስ አሰፋ፤
ወጣት መኮንን ለገሰ፤
በቀድሞ ክሴ አባሪዬ የነበረው ወጣት አብርሃም ሰለሞን፤
በመሆን ነበር ወደ ዝዋይ ፌዴራል እሥር ቤት ዕሁድ ጥር 6 ቀን፡ 2010 ዓም የተጓዝነው፡፡ ከአብርሃም በስተቀር ሁላችም ከየቤቶቻችን የወጣነው ከንጋቱ 10:00 ጀምሮ ነበር፡፡

ፈጣሪ ረዳንና የጨካኞችን ዓይን ጋርዶልን ፦
➊ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረውን ወጣቱን ፖለቲከኛ ዮናታን ተስፋዬ (ዮኒ)፣
➋ ወጣት ዘላለም ወርቅአገኘሁ (ዞላ)፣
➌ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ (ውቤ)፣
➍ የአርባምንጩ በፍቃዱ አበበ፣
➎ ወጣት ቴዎድሮስ አያለው ፋንታው፣
➏ ኮ/ል አሳምነው ጽጌ (ባጋጣሚ) እና
➐ ሌሎችም በጠያቂዎቻቸው የተጠሩ እሥረኞችን አግኝተናቸዋል፡፡
➑ ብርሃኑ ተ/ያረድ ወደ ቃሊቲ መጥቶ ነበረና አላገኘነውም፡፡
በርግጥ እኛን ሲያገኙን ደስታቸው ታላቅ ነበር፡፡ የቀድሞ ሞራላቸው፣ ሞገሳቸውና የሀገር ፍቅራቸው ዛሬም አልተለያቸውም፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ አቻ የማይገኝለት አምባገነን አገዛዝ እሥረኛ እፈታለሁ፤ የሰው ዘርን የሚያሰቃይበትን ማዕከላዊ እዘገዋለሁ እስከማለት መድረሱ ትግሉ የት እንደደረሰ ሌላው ማሳያችን ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2006/07(?) ሥራ ጀመረ የተባለው የአአ-ሞጆ የክፍያ መንገድ ከ3ና4 ዓመታትን እንኳ ሳያገለግል ረዥም ኪ.ሜትሮችን በሸፈነ ጥገና ምክንያት ከሁለት ሰዓት በላይ በመንገድ ላይ አስቆሞናል፡፡ ማንኛውም ሰው ሰራሽ ነገር መጠገን እንዳለበት እንረዳለን፤ የጥገና ፕላን መኖር አለበት፡፡ የዚህ የክፊያ መንገድ ነገር ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡ አይ ጥራት!? ብለን መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡

ሌላው ደግሞ፦ በባለፈው ኦሮሚያ ክልል <በመብት ጥየቃ ምክንያት በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ ወቅት የተቃጠሉ ተሽከሪካርዎችን በየመንገዱ ግራና ቀኝ ሳይ 1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ጊዜን አስታወሰኝ፡፡ አሃ! ለካስ ታሪክ ራሱን ይደግም ኖሯል!?

በመጨረሻም ፦ ፍትህ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት እስኪሰፍን ድረስ እንታገላለን፤ እሥረኞችም በፈጣሪያችን እርዳታና በእኛም ትግል እናስፈታለን፤ ሰብዓዊነታችን ዋና ባህርያችን ነውና የታሰሩትንም ሳንሰለች እንጎበኛለን፤ ደንነታቸውንም እንከታተላለን ፡፡ ፓለቲካ ከሰብዓዊነት ሲርቅ ውጤቱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ውጤቱ እምቦጭ ነው፡፡ ሰላም!!

Filed in: Amharic