>

ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈቶና ብሄራዊ እርቅ ፈጥሮ ወደማይቀረው ጦርነት ፊታችንን እናዙር 

ያሬድ ጥበቡ

በቀደም እለት ግብፅ ጦሯን ኤርትራ አስገባችን ስሰማ በቶሎ ነበር እውነት መስሎ የተሰማኝ። ዜናውን ስለተቀበልኩትም የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈቶና ብሄራዊ እርቅ ፈጥሮ ወደማይቀረው ጦርነት ፊታችንን እንድናዞር ለገዢው ፓርቲ ጥሪ አቅርቤ ነበር። ሆኖም በማግስቱ አንድ የፈረንጅ ጋዜጠኛ የቱሻ ዜና (fake news) ነው፣ ከሙሰሊም ወንድማማቾች ሰፈር የተፈበረከ ነው ሲል ልባችን መለስ ብሎ ነበር ።

ዛሬ ደግሞ የኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ግብፅ ገብተዋል። ዛሬ ከግብፅ መሪ አብዱል ፈታህ ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል። በኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሁለት ግብፃውያን ረዳት የጦር አብራሪዎች ተማርከው እንደነበረና አብዛኞቹ ቀላል የጦር መሳሪያዎች ከግብፅ የተሰጡ እንደነበሩ የወቅቱ የሪፖርተር ጋዜጣ መረጃ ያስታውሷል። ..ግብፅ ወደአሰብ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ስታስገባ ሰንብታለች። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ያነጣጠረ ለመሆኑ አያከራክርም። የኢሳያስ ዛሬ ካይሮ መገኘት ይበልጥ ጉዳዩን ግልፅ ያደርገዋል የሚል ዜና አሰማን ።

አል ሲሲ አሥመራ ቢመጣ እንጂ፣ ኢሳያስ ካይሮ ቢሄድ ያልተለመደ ስላልሆነ ዜናውን ንቆ መተው ይቻል ነበር ። ሆኖም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ኢትዮጵያችን ለገባችበት መቀመቅ ተጠያቂው እኔ ነኝ፣ ሆኖም ይህን አደጋ አስቀድመው አይተው ሊያርሙኝ የሞከሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች፣ የነፃ ሚዲያ ፊታውራሪዎችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችን በማእከላዊ እስርቤት የተለተልኳቸው አሸባሪ ስለሆኑ ነውና የፖለቲካ ጥቅሜን እያሰላሁ የፈለግኩትን ነው የምፈታው የሚል ተራ ቧልት ውስጥ ተዘፍቆ ይገኛል ። ይህ የአመራር ድቀት ነው።

በአመራሩ ውስጥ ያለው ክፍፍል ከተንታኞች ግምት አልፎ ኢህአዴግ ራሱ በ17 ቀናት ስብሰባው መግለጫው ይፋ እንዳደረገው ጥልቅ ነው። ከስብሰባውም ወዲህ ክፍፍሉ እንዳልቆመ የሚጠቁሙ የወያኔ የሶሻል ሚዲያ ፊታውራሪዎች በነለማ ላይ ያላባሩት ዘመቻቸው አንዱ መገለጫው ነው። ኢሳያስ ይህን እያየ ዝም ብሎ ይቀመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው ። ሻእቢያም ከወያኔ ትምህርት ይቀስማል ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው።

ወያኔ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክአምድር ወይም ምህዳር የደመሰሳቸው ብዙ ፓርቲዎች የተደመሰሱት በአመራሩ ውስጥ የሃሳብ ልዩነትና መጠላለፍ በነበራቸው ወቅት ነው። የትግራይ ነፃነት ግንባር (TLF) ፣ ኢህአፓ፣ ጀብሃ የወያኔን አከርካሪ የሚሰብር ጡጫ የቀመሱትና የተደመሰሱት ድርጅታቸውና አመራራቸው በተከፋፈለበትና በተዳከመበት ወቅት ነው። ሻእቢያ ይህን ያውቃል፣ ኢሳያስ ይህ በደንብ ገብቶታል ። ባለፉት 18 አመታትም በአንክሮ ይጠብቅ የነበረው ይህን ቅፅበት ነው። ሻእቢያ ከወያኔ ከተጣላባቸው አመታት ወዲህ ፣ ፊት ወያኔን ላለማስቀየም ይርቃቸው የነበራቸውን ኢትዮጵያውያን ከምርጫ 97 ማግስት ወዲህ ባሉት አመታት መቅረብ ጀምሯል። በነዚህ አመታት የአቶ ኢሳያስ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ የማነንና አምባሳደራቸውን ግርማይ አስመሮምን በተደጋጋሚ የማግኘት እድል ነበረኝ ። የኢሳት ቴሌቪዥን እርሾ የሆኑትን ጋዜጠኞች ከኬንያ አካባቢ ወስዶ ማሰልጠን ላይ ለመነጋገር እንገናኝ ነበር ። በነዚህ ግንኙነቶች አንድ የታዘብኩት ነገር ለወያኔ ያላቸው ጥላቻ ጥልቅ መሆኑን ነው። “እነዚህ ተካል አጋሜዎች አዋረዱን፣ ሱሪያችንን አስወለቁን” የሚል ጠንካራ የበቀል ስሜት አላቸው ። አድፍጠው የሚጠብቁት አመቺ ጊዜ ነበረ ። ያ ጊዜ አሁን የመጣላቸው ይመስለኛል።

ከሱዳን ፖርት ሱዳንና ገዳሪፍ አካባቢዎች እንደሚደርሱኝ መረጃዎች ከሆነ ግንቦት ሰባት ከፍተኛ የሆነ የሥልጠና ማእከል ምፅዋ ውስጥ ከፍቷል። ቲፒዲ ኤም ከነአስገዶም ክህደት የተረፈ አሁንም በአስር ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት አለው ። እነዚህ ኤርትራ ያሉ የኢትዮጵያ አማፂያን ታጋዮች ምንም እንኳ የውጊያ ልምድ ባይኖራቸውም ከፍተኛ የሆነ ሥልጠና እንዳላቸው ነው ከድርጅቶቹ በየጊዜው ከሚከዱ ሰዎች የተሰበሰበው መረጃ የሚጠቁመው። ስለሆነም ሻእቢያ የራሱን ታንከኛ ከማሰለፉ በፊት “ለመጨረሻው ግጥሚያ”የሚሰለፉ ኢትዮጵያውያን አማፂያን መኖራቸውን ግምት ማድረግ ተገቢ ነው። እነዚህ አማፂያንም ኢህአዴግ የገባበትን ቅርቃር ተረድተው ልንጥለው እንችላለን በሚል ብሩህ ስሜት ሊዋጉ ስለሚችሉ እንደከዚህ በፊቱ በቀላሉ የሚሸነፉ ላይሆኑ ይችላሉ። በአንፃሩ ኢህአዴግ ውስጥ የተንሰራፋው ድቀት ከአመራሩም አልፎ ድርጅቱን ተብትቦታል ። ከድርጅቱም አልፎ የመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በቀላሉ ሊንሰራፋ ይችላል ። በዚህ ሁኔታ ያለ ሠራዊትም እንኳንስ ሃገሩን ራሱን እንኳ መከላከል ሊሳነው ይችላል። ምን ይሻላል?

ኢህአዴግ ለደረሰው ድክመትና ድቀት ሁሉ ተጠያቂ ነኝ ይቅርታ አድርጉልኝ ማለቱ ካልቀረ፣ ጊዜ ሳያባክን ሃገራዊ አንድነት የሚያስገኙ ብልሃቶችን በፍጥነት ፈልፍሎ ማግኘት አለበት ። ሩቅ መሄድ አይኖርበትም። የገዱንና ለማን ቀናነት የገዢው ፓርቲ ልቦና ለማድረግ መወሰን ይችላል። ሁሉንም የህሊና እስረኞች አሁኑኑ በመፍታት መጀመር ይችላል። የፕሬስ ነፃነትን መልቀቅ ይችላል ። የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የጎማ ማህተሞች ሳይሆኑ የመረጣቸውን ህዝብ የሚወክሉ ዜጎች ሆነው በነፃነት የሃገር ጉዳይ ላይ እንዲወያዩ ክብራቸውን ሊጠብቅ ይችላል። ህገመንግስቱን የሚፃረሩ አዋጆችን እንዲያሻሽሉ ወይም እንዲሽሩ የአማካሪዎቹን ነፃነት ማክበርና ውሳኔያቸውንም ማስፈፀም ይችላል ወዘተ ወዘተ ። ብዙ አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ ። በአንዲት ቅፅበት የልቦና ለውጥ እነዚህ ሁሉ ተግባራት በአንዲት ጀምበርም ባይሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ መፈፀም ይችላሉ። ትልቁ እመርታ የልቦና ለውጥ ማድረጉ ላይ ነው ። ወዳጅ/ጠላት ከሚል አስተሳሰብ መፅዳት፣ በዜጎች ነፃነት ማመን፣ ሃገራችን የሁላችን ሃላፊነትና ተጠቃሚነት ያለባት መሆኗን መቀበል። አዎን እነዚህን ማድረግ እንችላለን።

Filed in: Amharic