>

ሳሎኑ ሳለ ቁም ሳጥኑ ውስጥ ለመኖር መወሰን ምን ይጠቅማል? (በዕውቀቱ ስዩም)

ከአምስት ዓመት በፊት ይመስለኛል፣ በደቡብ የሚገኝ የግብርና ዩንቨርሲቲ የብሔር ብሔረሰቦቸን ቀን ምክንያት በማደረግ የክብር አንግዳ አድርጎ ጠራኝ፡፡ትንሽ ካቅማማሁ በኋላ ማየት አይከፋም ብየ ሚኒባስ ተሣፈርሁ፡፡ካምፓስ እንደ ደረስሁ የምግብ ትርኢት ወደ ሚካሄድበት ትልቅ አዳራሽ መሩኝ፡፡ባዳራሹ ትልቅ የግብር ማብያ ጠረጴዛ ላይ ብሔሮችን የሚወክሉ መብሎችና መጠጦች ተደርድረዋል፡፡ሁሉንም ብሔር ላለማስከፋት ሰማንያ ጉርሻ መጉረስ ይጠበቅብኝ ይሆን በማለት በልቤ እያጉረመረምሁ ለቅምሻ ተሰናዳሁ፡፡ ሥጋና ወተት የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ተወዳጅ ምግቦች መሆናቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋልሁ፡፡ያም ሆኖ፣ ተማሪ ሁላ የራሱን ብሔር ምግብ ልዩ ግኝት አድርጎ ሊያሳይ ይጥራል፡፡አንዱ በተለጎመ ቅል ያቀረበውን ወተት፣ሌላው በሸክላ ጥዋ ያቀርበዋል፡፡አልተሸወድሁም፡፡ወተቱም የላሚቱ ፣ ቅሉም የተፈጥሮ ግኝት እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
ቀጣዩ ፕሮግራም፤የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ትርኢት ማየት ነበር፡፡በዩንቨርሲቲው አነስተኛ ስቴድየም ውስጥ በተዘጋጀልኝ ቦታ ላይ ጉብ አልሁ፡፡ስቴድየሙ የተለያዩ የብሔረሰብ ዩኒፎርሞች በለበሱ ተማሪዎች ተሞልቷል፡፡ተሜ ፣እዚም እዚያም ትንንሽ የሰው ደሴት ሰርታ ፣ ወልመጥ ወልመጥ እያለች ጭፈራውን ታስነካዋለች፡፡ብሔረሰብ ይወክላል ተብሎ የሚታሰብ ጥንታዊ እቃ የቀረ አይመስልም፡፡መንሽ፣ጎፈር፣አጎዛ፣አንቀልባ፣አገልግል፣ ሞፈርና ቀንበር፣ጦርና ጋሻ፣ቆልማማ ጩቤ፣መውዚር ጠመንጃ በየተማሪው እጅ አለ፡፡እንድያውም፣ትንሽ ብጠብቅ የድሮ መድፍ ከነመንኮራኩሩ ሲገባ ማየቴ አይቀርም ነበር፡፡
ዝግጅቱ ተጀመረ፡፡አራት ጎረምሳ ተማሪዎች ርቃን ሰውነታቸውን እንደ ጥምቀት ሽመል አዝጎርጉረው እንጣጥ እንጣጥ እያሉ ባጠገቤ አለፉ፡፡የያዙት አርማ የኦሞ ሸለቆ ብሄሮች ይላል፡፡አንዱን አተኩሬ ሳየው ሸገር የማውቀው መሰለኝ፡፡ መጠራጠሬን የታዘበ አጠገቤ የተቀመጠ ተማሪ ምስጢሩን ተነፈሰልኝ፤‹‹የሰውነታቸውን ቅርጽ ለሴቶች ለማሳየት ብለው፣እንደ ኦሞ ለብሰው ነው እንጂ አራቱም የቦሌ ልጆች ናቸው›› አለኝ ፡፡
በነገሩ የሌሉበት ሌሎች ተማሪዎች በስቴድየሙ ዙርያ ተበትነው፣የባለንጀሮቻቸውን ጫንቃ ተደግፈው ከፊታቸው የሚካሄደውን በጥርጣሬ ይመለከታሉ፡፡እኔም መመልከቴን ቀጠልሁ፡፡ከጥቂት ሰላም በሁዋላ አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡የትኛው ብሔር ቀድሞ ይለፍ የሚለው ጥያቄ በሁለት ብሔሮች መሀል ውጥረት ለኮሰ፡፡አንዱ ተማሪ የሌላውን ተማሪ ባህላዊ ኮሌታ ጨምድዶ ይዞ ሲተናነቅ አየሁት፡፡ ሌሎች ተማሪዎች ለማገላገል ሙከራ ያደርጉ ጀመር፡፡አቧራው መጠብደል ሲጀምር ስጋት ሰቅዞ ያዘኝ፡፡የግቢውን ውበት የማደንቅ መስየ ድብድቡ ሲጀመር ወጥቼ ማመልጥበትን ቀዳዳ መፈለግ ጀመርሁ፡፡በዚህ ዓይነት፣ለብሔረሰብ በአል መጥቼ፣ለታላቁ ሩጫ ራሴን ሳሟሙቅ፣ ሽማግሌ ገባና ነገሩን አበረደው፡፡
ሰሞኑን ባንድ ዩንቨርሲቲ ግቢ ብሔር መራሽ አምባጓሮ ተቀሰቀሰ ሲሉኝ ትዝ ያለኝ ይሄ ነው፡፡እንደምታውቁት የብሔርና የእግዚአብሔር ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ፣ለወሬ አይመቹም፡፡Taboo ናቸው ለማለት ነው፡፡ለደንበኛ ውይይት ሲቀርቡ ሰዎች ይቆጣሉ፡፡ግን ዝምታ፣ የችግሮቻችንን ጥፍርና ክራንቻ ከማሳደግ በቀር ጥቅም የለውም፡፡ወደድንም ጠላንም አገርን ከሥር የሚነቅል ጠብ የሚያስነሡ ሁለቱ ነገሮች ናቸው፡፡
መፍትሄው ምሁራዊ አይናፋርነትን ትቶ መወያየት ነው፡፡ለምሳሌ በዩንቨርሲቲዎች በተደጋጋሚ የብሔር ጠብ መነሻ ሚሆነው ሰብብ ፣ አንዱ እእምሮቢስ ተደብቆ ሚጽፈው ስድብ ነው፡፡ይህ ሲሆን ተሳዳቢውን ለብቻው ነጥሎ በሕግ ማስጠየቅ ያባት ነበር፡፡ግን በተደጋጋሚ እንደምናየው፣ ባንዱ ኃጢያት ሌላው ይሙት የሚል ብሉያዊ እስተሳሰብ የካምፓስ ልማድ የሆነ ይመስላል፡፡ ብዙ የተማሩ፣ የተመራመሩ ሰዎችን እንዴት አንድ ተንኳሽ ሊያተራምሳቸው ይችላል ? ነገሩ በዚህ ከቀጠለ እኮ ወደፊት የውጭ ጠላት አገራችንን ለማጥቃት ፣ጦር ማዝመት ሚሳኢል መተኮስ አያስፈልገውም፡፡በካምፓስ ሽንት ቤት በር ላይ የሚያስቆጣ ስድብ የሚጽፍ ዱርየ ማስረግ ብቻ ይበቃዋል፡፡
ምን ይሻላል?
ከሁሉም በፊት፣ አንድ ችግር ሲፈጠር፣ተማሪዎች፣ የማን ብሄረሰብ ተወላጅ ነው ይሄን ያደረገው ከማለት ይልቅ ማነው ይሄን ያደረገው ብሎ መጠየቅን ቢለምዱ ጥሩ ነው፡፡
ዘላቂው መፍትሄ ግን ከጠባብነት ለመውጣት መታገል ይመስለኛል፡፡ሳሎኑ ሳለ ቁም ሳጥኑ ውስጥ ለመኖር መወሰን ምን ይጠቅማል?ዘመናዊ ባዮሎጂስቶች ከዶልፊን ጋር እንኳ እንደምንዛመድ እያሳዩን ባሉበት ዘመን፣ የወንዛችንን ልጅ እንደ ባእድ መመልከት ትርጉም አይኖረውም፡፡

Filed in: Amharic