>
5:13 pm - Wednesday April 18, 7477

የፈረንጆቹ በገና በዓል ስጦታ የመሰጣጣት ባሕል ምንጩ እኛ እንደሆንን ያውቃሉ?

ሠዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን

እንኳን ለጌታችን፣ ለአምላካችን፣ ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሳቹህ!

ፈረንጆች በጌታ ልደት በዓል ስጦታ የመሰጣጣት ባሕል አላቸው፡፡ በዚህ በዓል ባል ለሚስቱ ሚስት ለባሏ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ልጆች ለወላጆቻቸው፣ ጎረቤት ለጎረቤቱ ዘመድ ለዘመዱ፣ ጓደኛ ለጓደኛው አሠሪ ለሠራተኛው ወዘተረፈ. ስጦታ ይሰጣጣሉ፡፡ ይሄንን በጌታ ልደት ቀን ስጦታ የመሰጣጣት ባሕልን የወሰዱትም ሰብአ ሰገል ጌታ በተወለደ ጊዜ ለጌታ ከሰጡት የወርቅ፣ የእጣን፣ የከርቤ እጅ መንሻ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ምዕራባውያኑ ይሄንን ባሕል ባሕል አድርገው እንዲይዙትም የቅዱስ ኒኮላዎስ (የሳንታ ክላውስ) አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው፡፡

“እንዴት ሆኖ ነው ታዲያ ይሄንን ባሕል ከእኛ ነው የወሰዱት ወይም ምንጩ እኛ ነን ሊባል የሚችለው?” ያላቹህ እንደሆነ የወርቅ፣ የእጣን፣ የከርቤን እጅመንሻ ለጌታ ያቀረቡት ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) የተባሉት ነገሥታት የኢትዮጵያ ነገሥታት በመሆናቸው ነው፡፡

ስለ ሰብአ ሰገል የጻፈው ወንጌላዊው ማቴዎስ እንዲህ ሲል ጽፏል “ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄዶድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ ዓይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ…!” ማቴ. 2፥1-12 ይላል፡፡

ብዙዎቹ ወንጌላዊው ማቴዎስ ሰብአ ሰገልን “…ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ!” ያለውን ይዘው ሰብአ ሰገልን የምሥራቅ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሩ ወይም የሚያስቡ አሉ፡፡ ነገር ግን ስሕተት ነው፡፡ ማቴዎስ ሰብአ ሰገል ወደ ኢየሩሳሌም ሲገቡ ለኢየሩሳሌም ምሥራቅ በሆነው መንገድ ስለነበረ የገቡት “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ!” አለ እንጅ ነገሥታቱ ወይም ሰብአ ሰገል የምሥራቅ ሀገራት ነገሥታት ናቸው አላለም፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ስለ እነዚህ ነገሥታት ወይም ሰብአ ሰገልና ለኢየሩሳሌም ስጦታ ያስገቡ ስለነበሩ ነገሥታት በመዝሙሩ ሲናገር “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ፡፡ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፣ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ!” መዝ. 71፥ 9-10 ብሏል፡፡ ይሄንን ሲልም ከታላቁ ባሕር በስተ ምዕራብ ያለችው ደሴት ተርሴስና በአካባቢዋ ያሉት ሌሎች ደሴቶች ኢየሩሳሌም ያመጡት የነበረውን ስጦታ ሲያመለክት ለጌታ ሰግደው እጅ መንሻን ያቀረቡለት ሰብአ ሰገል ደግሞ “የዓረብና የሳባ ነገሥታት!” እንደሆኑ ተናገረ፡፡ የዓረብና የሳባ ነገሥታት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ለዛም ነው ጥቅሱ ሲጀምር “ኢትዮጵያ በፊቱ ይሰግዳሉ!” ያለው፡፡

በዚያን ዘመን ደቡብ አረቢያና አካባቢው የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት እንደነበረ ከሀገራችን ታሪክ የምታውቁት ነው፡፡ የመናውያንም ይሄንን አምነው ይናገራሉ፡፡ በጌታ ዘመን ደቡብ ዓረቢያ የነበሩ የአይሁድ ማኅበረሰብን ለመጎብኘት አንድ የአይሁድ መምህርም (ራባይ፣ ረቢ) አካባቢውን በጎበኘ ጊዜ የዓረቦቹን ገዥዎች ንጉሡንና ንግሥቲቱን ሲያያቸው የአካባቢውን ሰው ወይም ዓረቦችን የማይመስሉ ጠያይሞች ሆነው እንዳገኛቸውና እንዴት እንዲህ ሊሆኑ እንደቻሉ ሲጠይቅም ኢትዮጵያውያን መሆናቸው እንደተነገረው የጻፈው የታሪክ ማስታወሻ አሁንም ድረስ በአይሁዶች ዘንድ ይታወቃል፡፡

ከንግሥተ ሳባ ጋር ተያይዞ ያለው ታሪክ ማለትም የቃል ኪዳኑ ታቦት፣ የብሉይ ኪዳን ሥርዓተ አምልኮ አሁንም ድረስ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑም ሰብአ ሰገል ወይም ነገሥታቱ ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ሌላው መረጃ ነው፡፡ ነቢያቱ እንደተነበዩት በብሉይ ኪዳን የጌታ የመሲሑ መወለድ በተስፋ ይጠበቅ ነበርና፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን ያመልኩ፣ እግዚአብሔርም ልጆቸ ሕዝቤ የሚላቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያንና እስራኤላውያን ወይም ኢትዮጵያና እስራኤልን ብቻ መሆኑም ሌላኛው አስተማማኝ መረጃ ነው፡፡ አሞ. 9፥7, ሶፎ. 3፥10, ሐዋ. 8፥26-40

እና ያለው ታሪክ ይሄ ነው፡፡ በመሆኑም ነው ለምዕራባውያኑ በጌታ ልደት ቀን ስጦታ የመሰጣጣት ባሕል ምንጩ እኛ ነን ስል የገለጽኩላቹህ፡፡ ስለሆነም የገና ስጦታ ስትሰጣጡ የገዛ ራሳቹህ ባሕል እንደሆነ አውቃቹህ አድርጉት እንጅ ከፈረንጅ ተውሳቹህ የምትፈጽሙት የተውሶ ባሕል እንደሆነ አስባቹህ አታድርጉት፡፡ ዛፉና ሌላው ነገር ግን የእኛ አይደለምና በዛ ላይ ደግሞ የጣዖት አምልኮ ውርስ ነውና ክርስቲያን ነን የምትሉ ከሆነ፣ ለክርስቶስም ታማኞች ነን የምትሉ ከሆነ፣ የተሟላ ማንነት ነው ያለን ወርደን የሌላውን ቆሻሻ ለቃቃሚ አይደለንም የምትሉ ከሆነ፣ ለሌላው የምንተርፍ ሆነን እያለን የማንነት ቀውስ በሽተኞች ሆነን የትም የምንልከሰከስ መሆን የለብንም የምትሉ ኩሩ ዜጎችና በሳል ሥነ ልቡና ነው ያለን የምትሉ ከሆነ ከዚያ ከዚያ ራቁ! ማንነታቹህን ጠብቁ! አክብሩትም!

ከላይ ስለ ሰብአ ሰገል የገለጽኩላቹህን ታሪክ የሚያውቁት ምዕራባውያኑ ይሄንን ከጽሑፉ ጋር አያይዠ የለጠፍኩትን የጌታን ልደት የሚያሳይ ጥንታዊ ሥዕላቸውን ሲሥሉ የስጦታን (የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት) ያመጡትን እና የእጅ መንሻን (የዓረብና የሳባ ነገሥታት) ያቀረቡትን ልዩነት ባለመረዳታቸው ወይም ደግሞ አውቀው ታሪክ ለመሻማትም ይሆናል ሰብአ ሰገልን ሲሥሉ አንደኛውን ብቻ ኢትዮጵያዊ ሲያደርጉት ሁለቱን ግን ነጮች አድርገዋቸዋል፡፡ ስጦታ ማለት አንድ ሰው ላለው ወይም ለሌለው ለሌላ ሰው ስለወደደው፣ ስላከበረው በገንዘብ ወይም በዓይነት የሚያበረክተው ሲሆን እጅ መንሻ ግን አንድ ሰው ከንጉሥ ወይም ከገዥ አንዳች ነገር በፈለገ ጊዜ በገንዘብ ወይም በዓይነት የሚያበረክተው ነው፡፡ ሰብአ ሰገል ስጦታ ሳይሆን ያበረከቱት እጅ መንሻ ነው ያቀረቡለት፡፡ የተወለደው አማኑኤል አምላክ እንደሆነ ያውቃሉና ምሕረቱን፣ ጸጋውን፣ በረከቱን…. ለመማፀን በማሰብ እጅ መንሻ አቀረቡ፡፡

ጌታችን፣ አምላካችን፣ መድኃኒታችን አማኑኤል ምሕረቱን፣ ጸጋና በረከቱን ይሰጠን ያሳድርብን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን! አሜን! መልካም በዓል!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Filed in: Amharic