>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9633

ሀተታ ዘ-ህወሀት (መሳይ መኮንን)

እንኳን ተነቦ፡ ገጹን ለመቁጠር የሚያደክመውን፡ በዝባዝንኬ የታጨቀውን፡ በፍሬከርሲኪ ወሬዎች የተጠቀጠቀውን፡ እንደቢንቢ ጆሮ ላይ በሚጮሁ ቃላት የተሞላውን፡ የህወሀትን ሃተታ በኢህአዴግ በኩል ወጥቶ አየሁት። አንብቤ ለመጨረስ ስንት ጊዜ አልጋ ላይ ወጣሁ፡ ስንት ጊዜ ወንበር ቀየርኩ፡ እንዴት ይሰለቻል?! መቼም እንዲህ ዓይነት ኋላቀርና ዘመኑን የማይመጥን ድርጅት የጫነብን ፈጣሪ ምን ሀጢያት ብንሰራ ይሆን? ከመርዘሙ መንዛዛቱ።

የህዝብን ቁጣ ይበልጥ የሚያቀጣጥል በመሆኑ ግን ወደድክኩት። በባዶ ተስፋና ልምምጥ የተወሰኑ ወገኖችን ሊያዘናጋ የሚችል መግለጫ ያወጣል ብዬ ገምቼ ነበር። ጭራሽ ዕድሜውን የሚያሳጥር፡ በተጀመረው ህዝባዊ አመጽ ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፍ ሀተታ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ህወሀት መንደር በዚህ በመጨረሻው ወቅት እንኳን የሚያስብ አንድ ሰው መጥፋቱ የሚያስገርም ነው።

ሀተታ ዘ-ህወሀት በአጭሩ አምስት ዋና ዋና መልዕክቶችን ማስተላለፍ ፈልጓል።
1ኛ- ቢደክመንም፡ ብናጠፋም፡ ብንበሰብስም፡ ብንገለማም፡ ብንዘርፍም፡ ብንባልግም፡ ስልጣን ግን አንለቅም።
2ኛ-የትግራይ የበላይነት የለም ያልናቸሁን ተቀበሉን። ሁላችንም እኩል ነን ተብሎ ተጽፏል። የመሬቱን ዕውነት ተዉትና የተጻፈውን ብቻ ተቀበሉ።
3ኛ-ከስልጣን በታች ባሉት በማንኛውም ጉዳዮች ላይ ልንወያይ ይቻላል። መወያየት ጥሩ ነው። ስልጣኗን መመኘት ግን ያስቀስፋል።
4ኛ-የእኛን ጉዞ ሊያደናቅፉ ከውስጣችን የተነሱት ላይ በቅርቡ እርምጃ ይወሰዳል። ይመነጠራሉ። ይጠራረጋሉ።
5ኛ-ከእንግዲህ ከመንገዳችን ላይ እንቅፋት የሚሆን፡ የሚያሰናክል ነገር ካለ አንታገስም።

የሀተታው ጭማቂ ከዚህ አያልፍም። ህወሀት ተጃጅሏል። ነዳጅ በተነከረ የሳር ጎጆ ቤት ውስጥ ሆኖ ክብሪት እየጫረ ይጫወታል። የመሳሪያ አፈሙዝ ላይ ቁጭ ብሎ ይፎክራል። ይሸልላል።

በአጭሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሀት የጠበቀው ነገር የለም። ሀተታው ጉዳዩ አይደለም። ኳሷ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች፡ በቄሮዎችና ፋኖዎች እግር ስር እንጂ በህወሀት አይደለችም። በህግ የተፈቀደ አመጽ የለም። የህወሀትን ዕውቅና የሚጠብቅ ተቃውሞ አይኖርም። ትግሉ ይቀጥላል። መዳረሻው ግልጽ ነው። ከህወሀት አገዛዝ ነጻ የሆነ የኢትዮጵያ ምድር ለኢትዮጵያውያን ዕውን ይሆናል። ሀተታው የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ ይህ እንደሚሆን ደግሞ አልጠራጠርም።

Filed in: Amharic